2018 ኤፕሪል 4, ረቡዕ

*©መዝሙር በእንተ ስቅለቱ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ©* . .

*©መዝሙር በእንተ ስቅለቱ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ©*
.
.

©ጌታ ሆይ

ጌታ ሆይ አይሁድ አማጽያን ሰቀሉህ ሆይ
የዓለም መድኃኒት የዓለም ሲሳይ ሰቀሉህ ሆይ /2/
የአዳም በደል አደረሰህ አንተን ለመስቀል
የሔዋን ስህተት አበቃህ ለሞት ቸሩ አባት /2/
ንጹሕ ክርስቶስ ሆንክ ወንጀለኛ ብለህ ስለኛ
መስቀል አሸክመው አሥረው ገረፉህ እያዳፉህ /2/
እጅና እግርህ በብረት ተመታ የዓለም ጌታ
የእሾህ አክሊል ደፍተህ ጐንህም ተወጋ አልፋ ፆሜጋ /2/
ግብዞች እንደራሳቸው መስሎአቸው
ምራቅ እየተፉ በፊትህ ቀለዱ አንተን ሊጐዱ /2/
በመስቀል ላይ ተጠማው ስትል ታላቅ በደል
ሐሞትና ከርቤ ሰጡህ ቀላቅለው ጠጣ ብለው /2/
ይቅር ባይ በደላችንን ሁሉን ሳታይ
አንተ ይቅር በለን በእኛ ሳትከፋ እንዳንጠፋ /2/

//////////////////////////////////
*©ኦ ዘጥዕመ*

ኦ ዘጥዕመ ሞተ በሥጋ(፫)
ሲጠማ ለኖረው በሲፆል በረሃ
ከጎኑ ሊያጠጣው የሕይወትን ውሃ
በክብር ሊመልሰው በኤዶም ለያኖረው

በመስቀል ተሰቅሎ ሊያድነው ከፍዳ
ከዙፋኑ ወርዶ ለብሶ ከለሜዳ
በሰው እጅ ተመትቶ በችንካር ተወግቶ

ግዕዛንን ለሰብክ ወደ ሲኦል ወርዶ
ምዉቱን ሊያድነው እራሱን አዋርዶ
ሊቀድስ በደሙ ሊያከብር በስሙ
////////////////


*©አልፍና ኦሜጋ*

አልፍና ኦሜጋ ፈጣሪ የሆንክ
በከሃዲዎች እጅ ተይዘህ ቀረብክ
         አዝ
ተገፍህ ተደፋህ በጥፊ ተመታህ
እየደበደቡ ክርስቶስ ሆይ አሉህ
ጽድቅን ስለሠራህ በወንጀል ከሰሱህ
ለአዳም ቤዛ ብለህ ብዙ ተንገላታህ
             አዝ
ቅዱሳን እጆችህ የፊጥኝ ታስረው
እንደበግ ጎተቱህ ልትምራቸው
የትም ቦታ ያለህ ሁሉን የምታውቅ
ፊትህን ሸፈኑህ በመመጻደቅ
      አዝ
በአውደ ምኩናን ከጲላጦስ ዘንድ
አሳልፈው ሰጡህ አጋልጠው ለፍርድ
ከሐና ቀያፋ ከመሳፍንት እጅ
ከነሄሮድስ ዘንድ አቀረቡህ በአዋጅ
         አዝ
ግርፋት ሕማሙ አልበቃም ብሎህ
በመስቀል ላይ ልትውል ተፈረደብህ
ሳዶርና አላዶር ዳናትና አዴራ
 ተፈልገው መጡ ሮዳስ ለችንካር
         አዝ
የሰላም ባለቤት ደረትህ ተወጋ
ሊያያዝ በችንካር እጅህ ተዘረጋ
ግፈኞች አይሁድ በአንተ ላይ ቀለዱ
ምራቅን ተፋብህ እራስክን ሊጎዱ

//////////////////////


*©በጌቴ ሴማኒ*

በጌቴ ሴማኒ በአትክልቱ ቦታ (፪)
ለእኛ ሲል ጌታችን በዓለም ተንገላታ (፪)
አዳምና ሔዋን ባጠፉት ጥፋት (፪)
ለእኛም ነበረብን የዘላለም ሞት (፪)
መስቀል ተሸክሞ ሲወጣ ተራራ(፪)
ይገርፉት ነበረ ሁሉም በየተራ(፪)
ድንግል አልቻለችም ዕንባዋን ልትገታ (፪)
እያየች በመስቀል ልጇ  (፪)
በአምላክነቱ ሳይፈርድባቸው(፪)
እንዲህ ሲል ጸለየ አባት ሆይ ሲንገላታማራቸው(፪)
በረቂቅ ሥልጣኑ ሁሉን የፈጠረ/፪/
በሰዎች ተገርፎ ሞቶ ተቀበረ(፪)
ፍቅሩን የገለጸው ተወልዶ በሥጋ(፪)
ኢየሱስ ጌታ ነው አልፋና ፆሜጋ(፪)

//////////////////////////


*©በዕፀ መስቀል ላይ*

   /ዘማሪት ማርታ ኃ/ሥላሴ ፩/

በዕፀ መስቀል ላይ በዚያ አደባባይ/2/
አምላክ ሆይ  ጌታ ሆይ መከራ አየህ ወይ
አምላክ ሆይ  ጌታ ሆይ ተንገላታህ  ወይ

መስቀል አስይዘው ኪርያላይሶን
ወደ ጎልጎታ              >>
ሲገርፉህ ሲያዳፉህ          >>
ስትንገላታ              >>

አዝ…

ያንን አቀበት       ኪርያላይሶን
ያንን ዳገት               >>
ጀርባህ ተገርፎ            >>
ስትቃትት                >>

አዝ…             

መስቀል አስይዘው  ኪርያላይሶን
እንዲያ ሲያዳፉህ          >>
የቀሬናው ሰዉ             >>
ስምዖን አገዘህ             >>

//////////////////////////


*©ሕማም የማታውቀው*

    /ዘማሪት አዳነች አስፋው ቁ.፪/

   ሕማም የማታውቀው ድካም የሌለብህ
   ስለኛ ተራብህ ደከምህ በእውነት
   የደም ላብ አላበህ ብዙም አስጨነቁህ
   እጅና እግርህን አስረውት አይሁድ አንገላቱህ/፪/

በቀርክሃ በጅራፍ አምላኬ ገረፉህ
በፈጠርከው ፍጥረት መወጋት መድማትህ
ምን ይሆን ምሥጢሩ ያንተ መንገላታት/፪/

     መንፈሳዊ አርበኛ ማርያም መግደላዊት
     ያንተ ሕማም ሞት ያንተ ስቃይ ጨንቋት
      በእኩለ ሌሊት ፅልመቱን ሳትፈራ
      አመጣት ጎትቶ የፍቅርህ አሻራ/፪/

ያ ሁሉ መከራ እንዴት ይግባ ልቤ
አልበጠስ አለኝ የኃጢአት መረቤ
መቼ ይሆን ፍቅርህ ለእኔ የሚገባኝ
ሕማም ጉስቁልናህ ልቤን የሚነካኝ/፪/

     ቃሉን ተናጋሪ ምግባር የሌለኝ

     ተገርፏል ተሰቅሏል የምል ብቻ ሆንኩኝ/፫/
ተው ልቤን ስበረው ልመንህ አጥብቄ
መቼ ሕይወት ሆነኝ ሕግህን ማወቄ
እባክህ የኔ ጌታ መንፈሴን ስበረው
የመስቀሉን ፍቅር በልቤ ላይ ሳለው/፪

//////////////////////

*©ምንኛ ድንቅ ነው*

  /መንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ሰ/ት/ቤት/

ምንኛ ድንቅ ነው የአምላክ ሥራው/2/   አዝ
ዙፋኑን ትቶ/2/ቀራንዮ/2/የዋለው

ፈራጅ አምላክ ሲሆን ሊፈረድበት
በአደባባይ አቆሙት ሊሳለቁበት
በጅራፍ አካሉን ሲገርፉት
ዝም ማለቱ እንደሌለው አንደበት

አዝ…
መስቀል አሸክመው እስከ ቀራንዮ
ሲስቡት ሲገርፉት ሲጮሁ ሲሉ ወዮ
ሲጥሉት ሲያዳፉት  እየገፈተሩ
ይህ ሁሉ ትዕግስት ምን ይሆን ምሥጢሩ

አዝ…
እርቃነ ሥጋውን ከመስቀል አስተኝተው
በአምስቱ ችንካሮች አካሉን ቸንክረው
ያለ ርኅራሄ ደሙን ሲያፈሱት
የእሾህ አክሊል ሰርተው እያቀዳጁት

አዝ…
የግፍ ግፍ ሲሠሩ በገዛ ግዛቱ
ኧረ ለምን ይሆን ዝም ብሎ ማየቱ
አዳምን ሊያወጣው ከባርነቱ
ሊመልሰው ወዶ ከገነት ከቤቱ

///////////////////////////


*©እስመ ለዓለም ምሕረቱ*

እስመ ለዓለም ምሕረቱ
                 እስመ ለዓለም ምሕረቱ  /4/
               አያልቅም ብዙ ነው የአምላክ ቸርነቱ

አመስግኑት ጌታን ሁላችሁ በአንድነት /2/
መሐሪ ነውና ለሰው ልጆች ሕይወት  /2/

                          አዝ
የማይሞተው ሞቶ የተቀበረው /2/
ከገሃነም እሳት እኛን ሊያድን ነው /2/

                        አዝ
ከማርያም የነሣው ያ ቅዱስ ሥጋው
ቀራንዮ ሲውል የሚያሳዝን ነው 

                      አዝ
በፈጠረው ፍጥረት እጅግ ተሰቃይቶ
ነፍሳትን አወጣ ከሲኦል ለይቶ  /2/

/////////////////////

*©ምድረ ቀራንዮ*

ምድረ ቀራንዮ ከጠዋት እስከ ሰርክ/2/
የእሾህ አክሊል ደፍተህ በመስቀል ላይ ዋልክ 

በቀራንዮ ጎልጎታ ጌታ በችንካር ተመታህ
ለዓለም ቤዛ ልትሆን ራስህን ለሞት ሰጠህ

እንደ ወንበዴ ታስረህ ሲቸንክሩህ እጅህና እግርህን
ለጠላቶችህ ክፉ አላሰብክም ይቅር በላቸው ነው ያልህ

ይሁዳ ሞኙ ተላላ ጌታውን ሽጦ ሊበላ
ገንዘብን ብቻ በመውደድ ገመድ ሆነችው ዘመድ

በዕለተ ዓርብ ስድስት ሰዓት ጌታን በመስቀል አውለውት
በግራ በቀኝ ፈያት መካከል እሱን ሰቀሉት

በኪሩቤል ላይ የሚኖር በቀራንዮ ተሰቀለ ለአዳም ክብር
እንደ ወንበዴ ተገረፈ ሥጋው አለቀ ተገፈፈ

አገኘን ብለው ልዩ ልብስ ተከፋፍለዋል ቀሚስህን
እሱን ሲሰቅሉት ጎልጎታ ወንበዴው በርባን ተፈታ

//////////////////////////


*©ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን*

ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን አባት ሆይ
በመስቀል ሆነህ አባት ሆይ
ድምጽህን በማሰማት አባት ሆይ
ነፍስህን ሰጠህ አባት ሆይ

ከዋክብተ ሰማይ በሙሉ ረገፉ
ጨረቃና ፀሐይ ደምን አጎረፉ
ብርሃናት ጨለሙ ጠፍተው ተለያዩ
ሥጋህን በመስቀል ተገልጦ ስላዩ

ጌታችን ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ
አሰምቶ ጮኸ ተጠማሁ እያለ
ማርና ወተትን ለሚመግበው
ሐሞት አመጡለት ይቅመሰው ብለው

አካሉ ሲወጋ ውኃ ደም ፈሰሰ
በምድር ተረጭቶ ዓለምን ቀደሰ
የእሥራኤል ሴቶች ዋይ ዋይ ሲሉልህ
ለእነርሱ አዘንክ እንጂ ለአንተስ አላሰብክም

እናትህ ስታለቅስ በመስቃል ሥር ሆና
ዮሐንስን ሰጠህ ጠብቆ እንዲያፅናና
መላእክትም ታዩ አጋንንትም ሸሹ
የአይሁድ ሠራዊት ፈርተው ተረበሹ

/////////////////////

*©ሕሙም ስላዳነ*

   /ዲ/ን ዳዊት ቁ.፩/

ሕሙም ስላዳነ በእጆቹ ዳስሶ
ሙትን ስላስነሣ በእጆቹ ዳስሶ
ይህም በደል ሆኖበት ለአምላክ ኖላዊ ሔር
በዕፀ መስቀሉ ላይ ዘርግቶ በፍቅር
ቀኝ እጁን በሳዶር ግራውን በአላዶር
ተቸነከረልን ጌታ በሁለት ችንካር

*አምንስቲቲ ሙኬርያ አንቲ ፋሲልያሱ*

ቤተ መቅደስ ምኩራብ በተመላለሱ
ባሕር ላይ በሔዱ ልክ እንደ በየብሱ
ለአምላክ ቤዛ ኵሉ ይህ ወንጀል ሆኖበት
በዕፀ መስቀሉ ላይ ተላልፎ ለመሞት
ሁለቱን በአንድ ላይ እግሮቹን በዳናት
ተቸነከረልን አምላክ የእኛ ሕይወት

*አምንስቲቲ ሙዓግያ አንቲ ፋሲልያሱ*

በልቡ አስቦ ድኅነት የሚያመጣ
ከበጎ ልቦናው በጎ የሚያወጣ
ይህ ወንጀል ሆኖበት ለአምላክ መድኅን ዓለም
በዕፀ መስቀሉ ላይ ተዘርግቶ ለዓለም
ልቡን በአዴራ ደረቱን በሮዳስ
ተቸነከረልን ወልደ አምላክ ክርስቶስ

*አምንስቲቲ ሙዳሱጣ አንቲ ፋሲልያሱ*

///////////////////

*©ድንግል የዚያን ጊዜ*

   /ዘማሪት ማርታ ኃ/ሥላሴ ቁ.፩/

ድንግል የዚያን ጊዜ/2/ ሐዘንሽ በረታ /2/
በመስቀል ላይ ሆኖ ልጅሽ ሲንገላታ/2/

አዝ…

ሴቶች ሲያባርሩት የዚያን ጊዜ ራርቶ ሆድሽ
ለፍጡር በማዘን ውሃ ያጠጣሽ/2/

አዝ…

ተጠማሁ እያለ የዚያን ጊዜ ሲናገር ልጅሽ
ታድያ እንደምን ቻለ ድንግል አንጀትሽ/2/

አዝ…

እንደዚያ ስታለቅሽ የዚያን ጊዜ ሐዘን ሲውጥሽ
እነማን ነበሩ ያስተዛዘኑሽ/2/

አዝ…

ስታለቅሽ በማየት የዚያን ጊዜ ራርቶ ልጅሽ
ዮሐንስን አጽናኝ እንደ ልጅ ሰጠሽ/2/

አዝ…

///////////////////

*©ግሩም ነው* 

   /ዘማሪት ማርታ ኃ/ሥላሴ ቁ.፫/

ግሩም ነው ግሩም /2/ የአምላክ ሥራ ግሩም ነው         
ዕፁብ ድንቅ አዳምን ለማዳን ያደረገው እርቅ/2/


ለጊዜያዊ ጥቅም ልቡ ስለሳሳ
ይሁዳ ሕይወቱን ሸጠው በሠላሳ
ጠላትህን ውደድ ብሎ እንዳስተማረው
ያስያዘውን ይሁዳ ወዳጄ ሆይ አለው

አዝ…..
እውነተኛ ፍቅር ነውና እስከ ሞት
መስቀል ተሸክሞ ሄደ ወደ ስቅለት
አንቺ ቀራንዮ የመስቀል ተራራ
ለዓለም መስክሪ የወልድን መከራ

አዝ…
የመድኃኔዓለም ደም የፈሰሰበት
መስቀል ኃይላችን ነው ከሞት የዳንበት
አምላክ ከሠራቸው ድንቅ ዕፁብ ሥራዎች
ይበልጣል ያሳየው ፍቅርን ለሰው ልጆች

አዝ…
ቀድሞ የገባለት ቃል ኪዳን ስላለ
ዐርብ ለፈጠረው ዐርብ ተሰቀለ.

//////////////////

*©ሙታንን ያድን ዘንድ*

ሙታንን ያድን ዘንድ የሞት ሞትን ሽሮ /2/
ወልደ አምላክ ሄደ ወደ ኋላ ታሥሮ/2/
ግርማን ለኪሩቤል ያጐናጸፋቸው
ዘውድን ለሱራፌል የሚያቀዳጃቸው
ከለሜዳ ለብሶ ዋለ ከፊታቸው

ቅዱሳን እጆቹ አዳምን የሠሩት
ቅዱሳን እግሮቹ በገነት የዞሩት
ተቸንክረው ዋሉ በጠንካራው ብረት

በምን በበደለ ነው ምን ባደረገ ነው/2/
ወልድ እንደ ቀማኛ ሲገረፍ የዋለው

አዳም በበደለ የግፍ ግፍ በሠራ
ቸሩ ወልደ አምላክ ዋለ በመከራ

ሁሉንም ታገሰ ሁሉን ቻለ ሆድህ
ትልቁም ትንሹም ሲዘባበትብህ

//////////////////////


*© ሞት ስለእኛ*

     ሞተ ስለእኛ /2/ የነገስታት ንጉስ
     የኃያላን ዳኛ ሞተ ስለኛ /2/

     ጐለጐታ እስኪደርስ ሰቃይ ተቀበለ
     ሥጋው ተዳከመች በመከራ ዛለ
     በጅራፍ ተገርፎ ደም ነጠበ ገላው ሞተ ስለእኛ /2/
   
     የሚካኤል ዝም አለ ተገርሞ አስተዋለ
     ገብርኤል ሰይፉን ወደ ምድር ጣለ
     ከዋክብት ደንግጠው ረገፉ ዛሬ
     መላእክት አለቀሱ ቀረና  ዝማሬ
     ሞተ ስለእኛ /2/

     ዑራኤል አምላኩን በመስቀል ላይ አየ
     በብርሃን ጽዋ ደሙን ተቀበለ
     ዕንባው አላቆሙም ጌታው ሲንገላታ
     ተገርሞ አስተዋለ በጥፊ ሲመታ
     ሞተ ስለእኛ /2/saramareyama.890@gmail.com

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የምዕራፍ አምስት(፭)የ46 የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ

✝በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡ አሜን! ↪️የምዕራፍ አምስት(፭) 46ኛ ዙር የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ⤵️ 1⃣ ቅዱስ ያሬድ ከመላዕክት የተማራቸው ሦስቱ የዜማ ዓይነቶች ምን ምን ናቸው?ሞገር...