2018 ጃንዋሪ 4, ሐሙስ

አፊያ ሁሴን ክፍል 11

#አፊያ ሁሴን

ክፍል 11

አፊያ ሁሴን (ክፍል ፲፩)

እንደ መደንገጥ የሚያደርግ ገጽታ ታየበትና "እንዴ.. ልጄ... አፊያ... ከየት መጣሽ? ቁጭ በይ እስቲ.. አረፍ በይ" አለ እየተደናገረው፡፡ እስኪረጋጋ ብዬ ጥቂት ሰከንዶች ፀጥ ብዬ ቆምኩ፡፡ ይዞት የነበረውን ፋይል ከቦታው ላይ መልሶ ሙሉ ለሙሉ ወደ እኔ ዞረና መቀመጫው ላይ ተደላደለ፡፡ ጥቂት በትኩረት አስተዋለኝና "ተቀመጭ እንጂ..?" አለኝ፡፡ "አልቀመጥም እቸኩላለሁ" አልኩት ኮስተር ብዬ፡፡ ለመናገር እየተሰናዳ ሳለ "ሁመይድ የነገረህን ነገር ላረጋግጥልህ ነው የመጣሁት፣ ከእርሱ ጋር መጋባት እፈልጋለሁ" አልኩት ፈርጠም ብዬ፡፡ የተሰማውን ነገር እንጃ ሰክቶት የነበረውንና አውልቆት ጠረጴዛው ላይ ያኖረውን መነጽሩን በእጆቹ እያሽከረከረ ለሰከንዶች ዝም አለ፡፡ የድምፅ አወጣጤ፣ ገጽታዬና ያንን ቃል ተናግሬ ለመውጣት የነበረኝ ጥድፊያ ብዙ ነገር የሚናገር ነበር፡፡ አሁን ከወላጅ አባቴ ይልቅ ፈፅሞ የማላውቀውን ሰው እየመረጥኩ ነው፡፡ አባቴ የነፈገኝን ሰብዐዊ ነፃነት እንኳን ሊዛመደኝ በዜግነትና በሀገር ሰውነት እንኳ ከማይመስለኝ ባዕድ ተሥፋ እያረኩ ነው፡፡ ከወለደኝና ካሳደገኝ ሰው ይልቅ ማንንም ቢሆን እስከምመርጥ ድረስ በአባቴ የተገፋሁ እንደሆንኩ ሁኔታዬ ሁሉ ያሳብቅ ነበር፡፡ ይህን ሁኔታ መቋቋም የተሳነው ይመስል ቀና ብሎ ሊያየኝ ድፍረት ያጣ መሰለ፡፡ በብዙ ጭንቅ ካቀረቀረበት ቀና ሳይል "ደግ...ካንቺው ከመጣ መልካም ነው፡፡ እኔ የምፈልገው ለወግ ማዕረግ እንድትበቂ ነው" አለ፡፡ ይህን ተናግሮ ሲያበቃ የተፈጠረውን የሰከንዶች ፀጥታ ለማጣራት ቀና ሲል ለቅጽበት ዓይኖቻችን ተጋጩ፡፡ ወዲያውም ቃል ሳልተነፈስ በሩን ከፍቼ ወጣሁ፡፡ ከእራሱ ሃሳብና ከገዛ ሕሊናው ሙግት ጋር ትቼው ወጣሁ፡፡ ቁጭ ብዬ ብዙ ባወራው፣ በእርሱ አስተሳሰብ ወደሚፈልገው መስመር ከመጣሁለት በኋላ ተፈጥሮ የነበረውን ነገር ሁሉ የሚያስተሰርይ የአባትና ልጅ ውይይት ብናደርግ ደስ ይለው እንደነበር አያጠያይቅም፡፡ በእኔ ውስጥ ግን እንዲህ ያለው ፍቅርና የመንፈስ ዝምድና ከሞቱ ቆይተዋል፡፡ በሐሰት የተገነባ ሽንገላንም ነፍሴ አጥብቃ ትፀየፋለች፡፡ ስለሆነም ጋብቻን የመሰለ ትልቅና የሚያወያይ አጀንዳ እንደ ልጅ ሳይሆን እንደ ቢሮ ጸሐፊ መረጃ ሰጥቼ ብቻ ውልቅ አልሁ፡፡

ከዚህ በኋላ ነገሮች በፍጥነት መከናወን ቀጠሉ፡፡ እኔም ሁሉን ነገር ዓይኔን ጨፍኜ መጋፈጥ ጀመርኩ፡፡ ሁመይድ በሀገር ወግ መሰረት ሽማግሌ ላከ፡፡ በሽምግልናው ወቅት የእርሱ ሀብትና ብልፅግና፣ መማርና መመራመር፣ የዞረባቸው ሀገሮች ሳይቀር ተደሰኮረ፡፡ መለስተኛ ሰርግ የሚመስል የሁለት ጊዜ የሽምግልና ሥነ ሥርዓትና ድግስ በቤታችን ተካሄደ፡፡ አባቴ በቀድሞውና በአሁኑ የሽምግልና ሥርዓቶች ላይ ጽንፍ የረገጡ ሁኔታዎች አሳየ፡፡ ያኔ በንዴት አሁን በሳቅ ተርገፈገፈ፣ በመጀመሪያው እኔ ላይ በትር እንዳላነሳ አሁን ሽማግሌዎች ያመጡትን ውስኪ በእጁ ይዞ የምርቃት ናዳ አወረደብኝ፡፡ ከዚህ ግርግር ይልቅ የተሻለ እረፍት የሰጠኝ አባቴ ቤት ውስጥ የሚፈጥረውን ሁከት እርግፍ አድርጎ መተዉ ነው፡፡ ሁመይድን እንደማገባ ካሳወቅሁት ጊዜ ጀምሮ አስደናቂ የባህርይ ለውጥ አመጣ፡፡ ከችግሮች አስቀድሞ እንደነበረው ቀኑን እየጠበቀ ቤት ይመጣል፡፡ ከእናቴ ጋር የነበረው የትዳር ሕይወታቸውም እየተሻሻለ ሄደ፡፡ በሆነ ባልሆነ እንደማይጨቀጭቃት አሁን ቀልድና ልፊያም ይከጅላት ጀምሯል፡፡ ከልጆቹና ከግቢው ሰው ሁሉ ጋር ሰላማዊ መስተጋብር ለመመስረት ይጥራል፡፡ እኔና ወንድሜ ፋይሰል ብቻ በቁጥብነታችን ፀናን፡፡ ሁለታችንም እንደ አምባገነን ንጉሥ አጫዋቾች የሰው ፊት እያየን የምንገለፍጥና ፊታችንን የምናጨፈግግ አይደለንም ያልን እንመስል ነበር፡፡ አባቴ ከሽምግልናው ቀደም ብሎ ባለው ሳምንት ጥቂት ዘመዶች፣ ሁለት ሼኪዎች፣ ከጎረቤትም እማማ አፀደና አንድ ሌላ አዛውንት በተገኙበት ተፈጥሮ የነበረው ችግር ሁሉ መቀረፉን የሚገልፅና ቤተሰቡ ይቅርታ የሚጠያየቅበት የቤተሰብ ጉባዔ መሳይ ነገር ጠርቶ ነበር፡፡ እርሱ ፋና ወጊ በመሆን በዋናነት እኔን ቀጥሎም እናቴን ከዚያም ፋይሰልን ይቅርታ ጠየቀ፡፡ ሁላችንም እንዲሁ ይቅርታ ተጠያየቅን፡፡ ነገሩን ሳስተውለው ግን አባቴ ሁኔታውን የተጠቀመበት ባሳየው ፀባይ አጥቶት የነበረውን ሞገስ መልሶ ለማግኘትና ለእማማ አፀደም "በመጨረሻ ያሸነፍኩት እኔ ነኝ" የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ይመስላል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ እንኳ የእኔና የፋይሰል ልብ ያልተፈታው ይህን ሁኔታ በመረዳት ይሆን? እያልኩ አስባለሁ፡፡

የሰርጉ ዝግጅት ላይ ሥልታዊ የሚመስሉ የተንኮል አካሄዶች ይመጡ ጀመር፡፡ ለምሳሌ የጋብቻው ሥርዓት እስላማዊ ለዛ እንዲኖረው አልባሳትና እጀባ ሃይማኖታዊ መልክ እንዲይዝ፣ የጋብቻው ቀን በክርስቲያኖች አቢይ ፆም አጋማሽ ላይ እንዲሆንንና የሚዜ ጥቆማ ሳይቀር በመስጠት የሚፈታተኑኝ ነበሩ፡፡ በአብዛኛው እንዲህ ያለውን ነገር የሚያደርጉት ከአባቴ ሥር ሥር የሚሉ ደርሶ ራሳቸውን የእስልምና ጠበቃ አድርገው የሚሾሙ ምናምንቴዎች ናቸው፡፡ እነርሱም የቤተሰብ ጉዳይ ውስጥ ገብተው ያላግባብ የሚፈተፍቱት የአባቴን ፊት እያዩ ነበር፡፡ ይህ ነገር ሲያበሳጨኝ ቆይቶ ሳለ አንድ ምሽት ስፈልገው የነበረ ጥሩ አጋጣሚ አገኘሁ፡፡ ቤት ውስጥ አባቴ ከሁለት ወጣት ሙስሊሞች ጋር ምግብ እየተመገበ ነበር፡፡ አንድ ጠና ያሉ ሰውም ነበሩ፡፡ እኔና ሄለን የቬሎና የሚዜ ልብስ ካታሎግ ይዛ የምትመጣ አንዲት ሴትን እየጠበቅን ሳለ ሴቲቱ የተለያዩ መጽሔቶች ይዛ ከተፍ አለች፡፡ ብዙም ሳይቆይ ፋይሰልም ከዋለበት መጣና ተቀላቀለን፡፡ የቀረበላቸውን ምግብ ተመግበው እንደጨረሱ አንዱ ሙስሊም ድምፁን ዘለግ አርጎ "አፊያ ጀሚላን ታውቂያታለሽ አይደል?" ሲል ጠየቀኝ፡፡ "አይ አላውቃትም" አልኩት፡፡ የጠራት ልጅ በወጣት ሙስሊም ሴቶች አንዳንድ እንቅስቃሴ ላይ በመሪነት የምትሳተፍ ናት፡፡ እርሱም ይህንኑ በማብራራት ሊያስታውሰኝ ደከመ፡፡ የሚላትን ልጅ ባስታውሳትም "አላወቅኋትም...ምንድነው?" አልኩት፡፡ እርሱም "በቂ ልምድና የማስተባበር ችሎታ ስላላት ሚዜሽ ብታረጊያት መልካም ነው፡፡ አልባሳትና ሌሎች ነገሮች ላይ ታግዝሻለች" አለኝ፡፡ ቀስ ብዬ አጠገቤ ላሉ ሰዎች "እነዚህ ሰዎች ከባል መረጣ ወደ ሚዜ መረጣ ተሸጋገሩ እንዴ?" ስል ሄለንና ሴቲቱ ሳቅ አፍኗቸው ጮኸው እንዳይስቁም ችግር ሆኖባቸው "ቡፍ...ቡፍ..." እያሉ ጎንበስ ጎንበስ አሉ፡፡ ፋይሰልም አንገቱን ቀብሮ የፈገገ ጥርሱን ለመከለል እየጣረ መጽሔቱን ማገላበጥ ያዘ፡፡ እኔም ወደ እርሱ እንኳ ሳልዞር ድምፄን እንዲሰማው አድርጌ "ስለ ሃሳብህ አመሰግናለሁ፣ ሆኖም በቂ ሚዜዎች አሉኝ" አልኩት፡፡ ልጁ ግን ሞዛዛ ቢጤ ኖሮ ይበልጥ ወደ እኛ እየተጠጋ ስለ ልጅቷ ችሎታና ቅልጥፍና፣ በእስልምና ትምህርትና ሥርዓት ስለመታነጿ ሲደሰኩር ብሽቅ አረገኝና "እባክህ ለምን ታሰለቸናለህ? እኛ ብዙ ሥራ አለብን..አታድክመን፡፡ ልጅቷ ይህን ያህል ከገዘፈችብህ ለራስህ ወዳጅ አድርገህ ያዛት" ብዬ ኩም አረኩት፡፡ በንግግሬ የተሸማቀቀው ወጣት "እኔ ላንቺ ብዬ እንጂ.." እያለ በማጉተምተም ወደመጣበት ተመለሰ፡፡ አባቴም ጠጋ ብሎ በልመናም በቁጣም መልክ "አፊያ እንደዚህ ሰው አታስቀይሚ እንጂ፣ ማንም ሰው አስተያየት የሚሰጠው አንቺን ለማገዝ ብሎ እኮ ነው" አለ፡፡ "ለእኔ አስቦ ከሆነ ምን ችክ ያረገዋል? ነገርኩት አይደል እንዴ፣ እዚህ እየመጡ ለምንድነው ያልበላቸውን የሚያኩት? ሰው ቤት ገብቶ መፈትፈት ምንድነው?" ብዬ አባቴ ላይ አፈጠጥኩበት፡፡ ንግግሬ ለአባቴ ብቻ ሳይሆን ራቅ ያለው ሶፋ ላይ ለተቀመጡት ወጣቶችም በመሆኑ ድምፄን ከፍ አድርጌው ነበር፡፡ እንደሰሙኝም እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ አባቴም ልጆቹ እንዲያዩት ራሱን ግራና ቀኝ እየነቀነቀ ወደ እነርሱው ሄደና መሃላቸው ሆኖ በወዳጅነት እጁን ትከሻቸው ላይ በማኖር ይዟቸው ወጣ፡፡ 

አባቴና ወጣቶቹ ከወጡ በኋላ ሄለን ሶፋው ላይ በጎኗ እንደመተኛት እያለች በሳቅ መንከትከት ያዘች፡፡ "ኤፊ ነፍስሽ አይማርም...እንደዚህ ልጁን ዕጢውን ዱብ ታረጊው? ውይ የእኔ ምስኪን...እንዴት እንደደነገጠ" እያለች ታጋንን ጀመር፡፡ ከተወሰነ ሳቅና ቀልድ በኋላ ሁመይድ ጋር ደወልኩና ኮስተር ብዬ "የሰርጉን ሥርዓት በተመለከተ የተነጋገርካቸው ሰዎች አሉ እንዴ?" በማለት ጠየኩት፡፡ "ኧረ ከማንም ጋር አልተነጋገርኩም" አለ እየተርበተበተ፡፡ "ታዲያ ምንድነው እዚህ እየመጡ ምክርና መመሪያ የሚሰጡኝ?" አልኩ አጠገቤ ያለ ይመስል፡፡ በዕለቱ የተፈጠረውን ነገር ነገርኩት፡፡ በእርግጥ ወጣቶቹ አባቴን ተከትለው የመጡ መሆናቸውን ይህም የቆየ ልማድ እንደሆነ ብረዳም ሁኔታውን ግን ሁመይድን ለማስጠንቀቅ ተጠቀምኩበት፡፡ ስለሆነም ሰርጉ ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ይዘት እንደማይኖረው፣ የጋብቻው ቀንም የክርስቲያኖች ዋና ፆም ከተፈታ በኋላ በሚያዝያ ወር እንደሚደረግ፣ አልባሳቱም እኔና ሚዜዎቼ በምንመርጠው ቬሎና ከለር እንደሚሆን ረገጥ አድርጌ አሳወቅሁት፡፡ ይህንንም በራሱ መንገድና ተፅዕኖ እንዲያሳምን የቤት ሥራ ሰጠሁት፡፡ "አሊያ ግን ሰርግና ጋብቻ የሚባል ነገር ሕልም ነው... እኔ እንደሆነ ለምንም ነገር ግድ የለኝ" ስል አስፈራራሁ፡፡ እርሱም "አይዞሽ ኤፊ...ይሄ አያሳስብም፣ ሁሉ ነገር አንቺ በፈለግሽውና እኛ በወሰንነው ነው የሚሆነው፡፡ ሙሽራ ክቡር ነው፣ ያለው ሁሉ ይፈፀማል" ሲል ሳቀ፡፡

ሚዜዎቼን አብሮ አደጌ ሄለንን፣ ልዕልና የምትባል አንዲት የሄለን ጓደኛና እንደኔው ሂጃብና አባያ ላይ የምታምፅ ሰሚራ የምትባል የአባቴ ልጅ እህቴን አደረግሁ፡፡ የተጠበቀው ሰርግ እጅግ በደመቀ ሁኔታ በካፒታል ሆቴል ተደረገ፡፡ አክራሪ ነን የሚሉ ሙስሊሞች ሳይቀሩ መጠጥ ቀማምሰው ይሁን በመድረክ ሞቅታ ተስበው አንዳንዶቹ ሲወዘወዙ ሌሎቹም ጭፈራውን ሲያስነኩት አመሹ፡፡ የእኔ የጋብቻ ሕልም በእንዲህ ያለው አስረሽ ምችው ባይሆንም ተገፍቼ ተገፍቼ እዚህኛው ጽንፍ ላይ ወደቅሁ፡፡ የሚዜዎች ጭፈራ ላይ እህቴ ሰሚራ የሚችላት አልተገኘም፡፡ ብዙ የአባቴ ወገኖች የጎሪጥ እስኪያይዋት ድረስ የውዝዋዜው መሪ ሆነች፡፡ "ይህን ሁሉ የጭፈራ ዓይነት ከየት አገኘችው?" ብለው እስኪደነቁ ድረስ ድብቅ ልምዷን ይፋ አወጣች፡፡ የሰርጉ ዕለትም ሆነ ካለፈ በኋላ ጭፈራዋን ለሚያነሱባት ሁሉ "እህቴ እኮ ነች ያገባችው... ማን መሰለቻችሁ?" እያለች ትመልስ ነበር፡፡ በሰርጉ የታደሙ ብዙዎች "ባሏ ፈረንጅ ነው፣ አፊያን ለመሰለ ቆንጆ የሚመጥን ሰርግ ነው፣ ከተጋቡ በኋላ ውጭ ሀገር ነው የሚኖሩት..." የሚል ግምት ወለድ አስተያየት ይሰነዝሩ ነበር፡፡ አባቴ የሙዚቃው ብዛት እንደረበሸው የሚያስመስል ፊት አልፎ አልፎ ቢያሳይም የክት ልብሱን ለብሶ በድል አድራጊነት ይጎማለላል፡፡ እናቴ የሀበሻ ቀሚሷን አድርጋ እየተፍለቀለቀች ትታያለች፡፡ እታባ ከባሏ ጋር ከፊት ለፊት ተቀምጣ በየደቂቃው የተለያየ የደስታ ምልክት ታሳየኛለች፡፡ ፋይሰል ራሱን በመስተንግዶ ጠምዶ ሲዋከብ እንጂ ተረጋግቶ አይታይም፡፡ ሰዓዳ የአራተኛ ሚዜ የሚመስል ሚና ይዛ ከሦሥቱ ሚዜዎች ቀጥላ መድረክ ላይ ተሰይማለች፡፡ ትንሹ ወንድሜ ሙኒር ሻማ ያዥ ስለሆነ በልዩ ልብስ አጊጦ ከሴት ሚዜዎች ወደ ወንድ ሚዜዎች እየተመላለሰ መድረኩን በልጅነት ሥልጣኑ እንደ ልቡ ተቆጣጥሮታል፡፡

የአባቴ ልጆች የሆኑ ወንድሞቼና እህቶቼ ሌሎች ዘመዶችም በአጃቢነት ወግ በአዳራሹ የፊት መስመር ተገጥግጠዋል፡፡ ከእነርሱ ቀጥሎ እማማ አፀደ፣ ልጃቸው አስቻለው፣ ጓደኛው ኤርምያስና በጉርብትና ስም ከሰፈር የተጠሩ በርካታ ክርስቲያኖች አሉ፡፡ እማማ አፀደ ከጣራ በላይ የሚጮኸው የሙዚቃ ድምፅና ሁካታው ብዙም እንዳልተመቻቸው ያስታውቃሉ፡፡ ደርበብ ብለው እንደተቀመጡ ግንባራቸውን ቋጠር ፈታ ያደርጋሉ፣ አልፎ አልፎም ከሰዎች ጋር እያወሩ ፈገግ ይላሉ፡፡ ስሜታቸውን ለማጥናት ከትልቁ መድረክ ቁልቁል አሻግሬ ደጋግሜ ወደርሳቸው ባይም ልብ ያሉትም አይመስሉ፡፡ ይልቁኑ ወደርሳቸው ባተኮርኩ ቁጥር በዚያው አንፃር ያሉት ዘመዶች ወደ እነርሱ ያየሁ እየመሰላቸው የተለያየ ምልክት ይሰጡኛል፡፡ አስቻለውና ኤርምያስ በደማቅ ፈገግታ እጃቸውን ሲያውለበልቡልኝ በታመምኩ ጊዜ ያሳዩኝን አለሁ ባይነት አስታውሼ "በመከራና በደስታ የማይለወጥ እንዴት ያለ ወዳጅነት ነው?" ስል ለአፍታ አሰብኩ፡፡ ከመድረክ ሆኜ ወደታች ስመለከት ያለው ትዕይንት የማልረሳው ስዕል በውስጤ ፈጥሮብኝ አልፏል፡፡ በዚያው ድምቀት የኬክ ቆረሳው፣ እርሱን ተከትሎ የሚመጣው ጭፈራና የምሥጋና ካርድ ዕደላው ተካሄደ፡፡ ወደ በኋላ ላይ ከፍተኛ ድካም ስለተሰማኝ የስነ-ሥርዓቱን መጠናቀቅ እስከመመኘት ደረስሁ፡፡ ብመኝም ባልመኝም ተፈጥሯዊው የጊዜ ዑደት በራሱ የማይገሰስ ሕግ መሄዱ ስለማይቀር የሰርጉ ፍፃሜ ሆነ፡፡ አስቀድሞ በተያዘ ፕሮግራም መሰረት በሰርጉ ሳምንት የጫጉላ ሽርሽር ስለምንሄድ መልስና ቅልቅሉ በዚያው ሳምንት ውስጥ ተካሄደ፡፡ የገዛ እልሄ ይሁን የእግዚአብሔር ፈቃድ ባላውቅም ከአባቴ ጥብቅ ቁጥጥርና ተፅዕኖ ወደ ባል ቁጥጥር ተዛወርኩ፡፡ አሁን ያገባሁ ሴት ስለሆንኩ ከልጅነት የተሻለ ሙሉነትና ሃላፊነት ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ ሌላኛው የሕይወት ምዕራፌ ምን እንደሚመስል፣ የት እንደሚያደርሰኝና ምን ዓይነት አዳዲስ ተግዳሮቶች እንደሚኖሩት ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡

በሰርጌ ሳምንት እሑድ ምሽት ወደ ለንደን በረርን፡፡ የጫጉላው ሽርሽር የት የት ሀገርን እንዲያካትት እንደምፈልግ ሲጠይኝ የታሪክ ዝንባሌ እንዳለኝ በመጥቀስ ጣልያን፣ ግሪክና ግብፅ ቢካተቱ ደስ እንደሚለኝ ነግሬው ነበር፡፡ ሆኖም እርሱ በሥራ ምክንያት ብዙ ጊዜ እንግሊዝ ስለሚመላለስና እዚያም በርካታ ወዳጆችና የሥራ አጋሮች ስላሉት አስቀድመን ወደዚያው አመራን፡፡ እዚያ ከጠበኩት በላይ ወደ ሃያ ቀን የሚያህል ቆየን፡፡ በጣም ብዙ ሰው ስለሚያውቅ በየቀኑ አነስተኛ ግብዣዎች በየሬስቶራንቱ ሲደረግልን ሰነበተ፡፡ መልካም ምኞት የሚመኙልን፣ ቆንጆ ሚስት አለህ እያሉ የሚያደንቁ በርካቶች ነበሩ፡፡ የአበባና የፖስት ካርድ መዓት ክፍላችንን አጣቦት ነበር፡፡ በስልክ ሲተርክልኝ የነበረውን የእንግሊዝን ከተሞች፣ ዝነኛ ሙዚየሞችና ቤተመጻሕፍት፣ የጥበብ ማዕከላትና የቱሪስት መዳረሻዎች ተዟዙረን ጎበኘን፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ3000-1500 ዓ.ዓ. እንደቆሙ የሚገመቱትን ጥንታዊ የብሪታኒያ የድንጋይ ሐውልቶችን፣ ዝነኛውን የለንደን ታወር፣ ጥንታዊና ታሪካዊ ቤቶችን አቅፎ የያዘውን ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲን፣ የተለያዩ ጥንታዊ ግንቦችን፣ ፓርኮችንና የዱር አራዊት መጠበቂያ ቦታዎችን (zoo) ተዟዙረን ተመለከትን፡፡ ከሁሉ ያስደነቀኝ ኤደን ፕሮጀክት (Eden Project) ብለው የገነቡት የተለያዩ ዕፅዋት የሚበቅሉበት ሥፍራ ነው፡፡ ከመላው ዓለም የተሰበሰቡ በሺዎች የሚቆጠሩ የዕፅዋት ዓይነቶች የሚገኙበት ይህ ሥፍራ ኤደን ገነትን እንዲመስል ብዙ እንደተለፋበት ያስታውቃል፡፡ ቦታው ላይ የእስኪሞዎች የበረዶ ቤቶችን የሚመስሉ ትላልቅ ባለ ክብ ጉልላት መጠለያዎች ታንፀው በውስጣቸው የጸሐይ ቃጠሎ እምብዛም የማይስማማቸው የተክል ዓይነቶችን ይዘዋል፡፡ እኒህ ባለ ክብ ጉልላት ትላልቅ መጠለያዎች ከውጭ ሲያዩዋቸው የማር እንጀራ የሚመስል ቅርፅ አላቸው፡፡ ተክሎቹ የየመጡበትን አካባቢ የአየር ንብረት ለማስመሰል የተደረገው ሥራ የሚደንቅ ነበር፡፡

እንግሊዝ ያለን ቆይታ ሲጠናቀቅ የስዊዘርላንድን አስደናቂ መልክዐ ምድርና የተፈጥሮ ገጽታ እንይ ብሎኝ ወደዚያ ሄድን፡፡ የዕውቀትና የመረጃ ክፍተት ገድቦኝ እንጂ በእርግጥም ተፈጥሮን ለማድነቅ ስዊዘርላንድ ከአውሮፓ እጅግ ተመራጯ ሀገር ነች፡፡ አናታቸውን በበረዶ ብናኝ ሸፍነው ወገባቸውን ብሩህ ደመና ታጥቀው የሚታዩት የዓለት ተራራዎች ከርቀት ሲያዩዋቸው ለአምልኮ የተሰለፉ የሃይማኖት ሰዎች ይመስላሉ፡፡ እጅግ ጥርት ያሉ ሐይቆችና ወንዞች ያሉባት ይህች ሀገር ከአውሮፓ ትልቁና ማራኪው ፏፏቴም የሚገኝባት ናት፡፡ መላዋ ሀገሪቱ አረንጓዴ ሥጋጃ የተነጠፈባት ይመስል ሲበዛ ለምለም ነች፡፡ ይህን መሳዩን የተፈጥሮ ፀጋና ርዕሰ መዲናዋ ዙሪክን ጎብኝተን ወደ ጣሊያን አመራን፡፡ ሁመይድ እንግሊዝን በጥልቀት ስዊዘርላንድን በስሱ የሚያውቃቸው ቢሆንም ጣልያን ዋና ከተማዋ ሮም ሁለት ጊዜ ከመምጣት በቀር እኔ ማየት የፈለኳቸውን ታሪካዊ ሥፍራዎች እርሱም አያውቃቸውም፡፡ ግሪክንማ ጭራሽ ሄዶባት አያውቅም፡፡ ስለሆነም በሁለቱ ሀገሮች ያየናቸው አስደናቂ፣ ጥንታዊና ታሪካዊ ሥፍራዎች እንዳስገረሙት እየደጋገመ ሲገልጥ ነበር፡፡   ጣልያን ውስጥ ጥንታዊውንና ኃያሉን የሮማን ኢምፓየር የሚዘክሩ ቅርሶች ቁጥር ስፍር የላቸውም፡፡ ሙዚየሞቿ እጅግ በበዙ ጥንታዊ ቅርሶች የተጣበቡ ናቸው፡፡ ይህቺን ጥንታዊና ታሪካዊ ሀገር አብጠርጥሮ ለመጎብኘት አመት እንኳን የሚበቃ አይመስልም፡፡ እንደ እኛ ላለ ለቀናት ቆይታ ለመጣ ጎብኚ ዝርዝሩን ትቶ ጉልህ ጉልሁን በወፍ በረር ከመቃኘት የዘለለ ዕድል የለውም፡፡ ኮሎዝየም የሚሉት ጥንታዊ የሮማ መኳንንት ቲያትር ቤት ግማሽ ጎኑ ከመፍረስ ተርፎ አሁን ድረስ ተጀንኖ ቆሞ ይታያል፡፡ ለዘመናዊ ስታድየሞችና ግዙፍ ቲያትር ቤቶች ግንባታ ሞዴል መሆን የቻለ አስደናቂ የኪነ ሕንጻ ጥበብ የሚታይበት ይህ ጥንታዊ መዝናኛ ሳይጠቀስ የማይታለፍ ነው፡፡ ፖምፔይ ተብሎ የሚታወቅ ጥንታዊ የመዝናኛ ከተማም በውስጡ ካቀፋቸው የቤቶች፣ የገበያ፣ የመቅደሶች፣ የቲያትር ቤቶችና የመንገዶች ፍርስራሽና ቆመው ከሚታዩ አንዳንድ ግንቦች ጋር ይታያል፡፡ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታትን አልፈው ትርጉም ያለው ታሪካዊ ምስክርነትን የሚሰጡ የሮማ ሸንጎ የሕንጻው ምሶሶዎች (pillars) እና ከፊል መዋቅሮች፣ የጥንታዊ መቅደሶች መሰረቶች፣ የገበያ አዳራሽና የግብር መክፈያ ቤቶች ቅሪተ አካላት እንዲሁ ከሚጎበኙም ከሚደነቁም መካከል ናቸው፡፡ በጣልያን ውስጥ አጅግ በጣም ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ሲኖሩ ለጉብኝት የሚበቁት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ የሮም ካቶሊክ መንበር የሆነችውን ቫቲካንን፣ ግዙፉን የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራልና አስደናቂ የግንባታ ጥበብ የሚታይበት የቬነሱ ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያንን እዚህ ላይ ሳይጠቅሱ ማለፍ አይቻልም፡፡ ከመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን እስከ ሦሥተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ በጣኦት አምላኪዎችና በአህዛብ ነገሥታት ሲሳደዱ የነበሩት ክርስቲያኖች ይደበቁበት የነበረው ግበበ ምድር (ካታኮምብ፣ የውስጥ ለውስጥ ዋሻ) ሌላው አስደናቂ ትዕይንት ነው፡፡

በግሪክም እንዲሁ ለአንድ ሳምንት ያህል ስንጎበኝና ስንዘዋወር ቆየን፡፡ የጥንታውያኑ ፈላስፎችና አዋቂዎች የእነ ሆሜር፣ ሄሮዱትስ፣ ሶቅራጥስ፣ አርስጣጣሊስ፣ ሂፖክራተስ፣ ፓይታጎረስ... ሀገር ግሪክ እንዲሁ የበዛና የተወሳሰበ ቅርሶች ባለቤት ናት፡፡ በታዋቂው የአቴንስ ሙዝየም ውስጥ የሆሜር ኤሊያድና ኦዲሴን ጨምሮ የተለያዩ ፈላስፎች መጻሕፍት፣ የግሪክ ሚቶሎጂ የሰፈረባቸው ትርክቶችና ዘመን ተሻጋሪ ቅርሶች ሞልተዋል፡፡ የአቴንስ ከተማ ምልክት የሆነውና ከክርስቶስ ልደት በፊት በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደታነፀ የሚነገርለት አክሮፖሊስ (Acropolis) የተባለው ሕንጻ ከበርካታ አምዶቹ ጋር በኩራት ይታያል፡፡  በፓርናሰስ ተራሮች መካከል በጠባብ ሸለቆ ውስጥ ታንፆ የዘመኑ ጣኦት አምላኪዎች አፖሎ ለተባለ አምላካቸው አምልኮ የሚያቀርቡበትና አምላካዊ ምሪት የሚጠይቁበት ዴልፊ (Delphi) የሚባለው ሥፍራም ከጥንታዊነቱ የተነሳ አስጎብኚዎች እንዲጎበኝ የሚመክሩት የቱሪስቶች መዳረሻ ነው፡፡ እንደ ጥንታዊቷ ተሰሎንቄ ከተማና በአርኬኦሎጂ ቁፋሮ የተገኘው የስፓርታ ከተማ ፍርስራሽ በእርጋታ ለሚጎበኛቸው ብዙ የሚሉት ነገር፣ የሚያወሩት ታሪክ አላቸው፡፡

ልክ ጊዜ እንደሚወስድ ሥራና ለተከታታይ ቀናት እንደቀጠለ ድግስ በመጨረሻ ሁለታችንም ድካም ተሰማን፡፡ ስለሆነም የግብፅ ጉብኝታችንን ለሌላ ጊዜ አዛውረን ከአንድ ወር አስራ አምስት ቀን በኋላ በቀጥታ ወደ ሀገር ቤት መጣን፡፡ ለጊዜው የተሟላ ዕቃ ያለው አንድ ገስት ሀውስ ተከራይተን እዚያ ገባን፡፡ እጅግ የናፈቁኝ ቤተሰቦቼ ጋር ስሄድ እንደ ንግስት ተቀበሉኝ፡፡ ለሰርጌ የመጣለኝ ሥጦታ መኝታ ክፍሌን አጨናንቆታል፡፡ የቤት ዕቃው፣ ልብሱ፣ ጌጣጌጡ... ምኑ ቅጡ?! ያን ምሽት ሁመይድ በቤተሰቦቼ ፊት ሁለት ቁልፎች አምጥቶ "ለልዕልቲቱ አፊያ ይህ ቢያንስ እንጂ አይበዛባትም" አለና አስረከበኝ፡፡ አንዱ የአዲስ ያሪስ መኪና ቁልፍ ሲሆን ሌላው ደግሞ ጃክሮስ ኢትዮጵያ የሚባል ሪል ስቴት ካስገነባቸው ቪላዎች ውስጥ የአንዱ ቁልፍ ነበር፡፡ ለካ በጉዞ ሳለን በወንድሜ ፋይሰል አማካኝነት የሁለቱንም ግዢ ፈፅሞ ኖሯል፡፡ አባቴ ደግሞ ከሁመይድ ጋር ፉክክር የያዘ ይመስል ስላለፈው ችግር ኑዛዜ የሚመስል ዲስኩር አሰማና አሁን የተሰማውን ደስታ ገልፆ የቪትዝ መኪና ቁልፍ ሰጠኝ፡፡ መኪና መንዳት የማልችልና መንጃ ፈቃድ የሌለኝ ሴት በአንድ ጊዜ የሁለት መኪና ባለቤት ሆኜ አረፍኩት፡፡ በአንድ ወር  ጊዜ ውስጥ አዲሱ ቤታችን ዕቃ ገብቶበት፣ እንደሚገባ ተደራጅቶና ጥበቃና ሰራተኛ ተቀጥሮ አዲሱን የሕይወት ምዕራፍ "ሀ" ብዬ ጀመርኩት፡፡ ለካ አዲሱ ቤት የገባሁት እንደ ወትሮው ሌጣዬን አልነበረም፡፡ ቤቴ በገባሁ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ጥሩ ስሜት አልሰማኝ ሲል ሆስፒታል ሄድኩ፡፡ የምርመራ ውጤቴም የ2 ወር እርጉዝ እንደሆንኩ አበሰረኝ፡፡

                        (ይቀጥላል)

   ----------- ማርያማዊት ገብረመድኅን -----------sara.mareyama.890@gmail.com

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የምዕራፍ አምስት(፭)የ46 የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ

✝በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡ አሜን! ↪️የምዕራፍ አምስት(፭) 46ኛ ዙር የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ⤵️ 1⃣ ቅዱስ ያሬድ ከመላዕክት የተማራቸው ሦስቱ የዜማ ዓይነቶች ምን ምን ናቸው?ሞገር...