2017 ዲሴምበር 28, ሐሙስ

አፊያ ሁሴን ክፍል ፱

#አፊያ ሁሴን ክፍል 9

#ፀሀፊ ማርያማዊት ገብረ መድህን

አፊያ ሁሴን (ክፍል ፱)
saramareyama.890@gmail.com
ሁመይድ የመላው ቤተሰብ ወዳጅና ቤተኛ ከሆነ ሰንበት ቢልም ከእኔ ጋር ለየት ያለ ቅርበት እንዳለው ሰራተኞቹ ሳይቀር ያስተዋሉ መሆናቸውን ከመልዕክቷ ተረዳን፡፡ ሆኖም መውጣት ስላልፈለኩ ፋይሰልን "ሂድ አጫውተው ራሷን አሟት ተኝታለች በለው" ብዬ ላኩት፡፡ መጀመሪያ ፋይሰል፣ ከዚያ ሰዓዳ ሄዱ፡፡ ከተኛሁ በኋላ ሰዓዳ መጥታ ከአንቺ ጋር ነው የምተኛው ብላ ምኑንም ምኑንም ስትለፈልፍ አመሸች፡፡ እንግዲህ በእርሷ ቤት እየጠበቀችኝ ነው ማለት ነው፡፡ ያን ሳምንት እንዲሁ ሲጠነቀቁኝና ሲፈሩኝ ሰነበቱ፡፡ እናቴ ወደ ሱቅ እንኳን ወጣ ለማለት በተነሳሁ ቁጥር "እባክሽ ልጄ ልጄ..እባክሽ የእኔ እናት.. እዚሁ ቁጭ በዪልኝ፣ የትም ቢሆን ሰራተኞቹን ላኪያቸው" እያለች ትለማመጠኛለች፡፡ እኔም የምችለው እርሷን ነውና "ሰው እኮ ነኝ፣ የቤቱ ውስጥ ዕቃ አረግሽኝ እንዴ? አየር ያስፈልገኛል፣ መንቀሳቀስ ያስፈልገኛል፣ ይሄ የእናንተ ቪላ ለእኔ መኖሪያ ቤቴ ነው ወይስ እስር ቤቴ ነው?" እያልኩ እጮህባታለሁ፡፡ የቱንም ያህል ብናገራት የእናቴን ልመና ረግጬ አልወጣም፡፡ እየተነጫነጭሁ መልሼ ቁጭ እላለሁ፡፡ ለአባቴ "ወይ ጥያችሁ እጠፋለሁ፣ አሊያ ራሴን አጠፋለሁ" ብላ በስንት ልመና በስንት ግልግል ነው የተረጋጋችው ተብሎ ተነግሮታል መሰለኝ ወደ ቤት በመጣ ቁጥር መኖሬን ጠይቆ ያረጋግጣል እንጂ ከእኔ ጋር መገናኘቱን አይፈልገውም ነበር፡፡ እኔም በርቀትም ቢሆን ባየሁትና ድምፁን በሰማሁ ቁጥር "ልጄ መሆኗን እጠራጠራለሁ" ያለው ነገር ትዝ እያለኝ እንደ አዲስ እናደዳለሁ፡፡ ከዚህ በፊት ያሳየኝ የነበረው የአባትነት ፍቅር ሁሉ ለማስመሰል ያደረገው ሽንገላ እየመሰለኝ በክፉ ሃሳብ እናጣለሁ፡፡ ሽማግሌዎቹ የተቀጠሩበት ቀን እየቀረበ ሲመጣ አባቴ ሃሳቤን ቀይሬ እንደሆነና ረጋ ብለውም ሊያሳምኑኝ እንዲጥሩ እናቴ፣ እህቴና ፋይሰል ላይ ጫና ማድረጉን ተያያዘው፡፡ እነርሱ ደግሞ እኔን ከመናገር እርሱኑ መጋፈጥ የተሻለ እንደሆነ የቆጠሩበት ሳምንት ነበር፡፡ አንድ ቀን እንደውም ከፋይሰል ጋር ኃይለ ቃል እስከመነጋገር ደረሱ፡፡ ወንድሜ አባቴን ከዚህ በላይ ሊያስጨንቀኝ እንደማይገባ ሲነግረው በጄ ስላላለው "አንተ ብዙ ሴት ልጆች ስላሉህ የአንዷ መጨነቅ አልተሰማህ ይሆናል፡፡ እኔ ግን እህቴን እፈልጋታለሁ" ሲል አምርሮ ተናገረው፡፡ በዚህ የተበሳጨው አባቴ ልክ አድማ የተደረገበት ያህል መላ ቤተሰቡን አኮረፈ፡፡

ሽማግሌዎቹ እሑድ ሊመጡ ሐሙስ ከሰዐት ሾልኬ ወጣሁና ቤተክርስቲያን ቆይቼ ማምሻውን እህቴ ቤት ሄድኩኝ፡፡ ትንሽ ሲራበሹ ከቆዩ በኋላ እህቴ ደውላ እርሷ ጋር እንደሆነች ነገረቻቸው፡፡ እስከ እሑድ እዚያው እንደምቆይ ተናግሬ ይህንኑም ለእናቴ በስልክ አስረዳኋት፡፡ እርሷም "እሺ የእኔ ልጅ እንዲያውም እዚያ ብትሆኚ ይሻላል" አለችኝ፡፡ የእሑዱ ሽምግልና ቀዝቀዛ ድባብ እንደወረሰው መጠናቀቁን ሰማሁ፡፡ አባቴም "እነዚህ ሽማግሌዎች ምስክሮቼ ናቸው፣ በዱላም በምክርም በልመናም አልሸነፍም አለች፡፡ እንግዲህ ምን አድርግ ትሉኛላችሁ?...ልጄን አልገላት ነገር" በማለት ይቅርታ ጠየቀ፡፡ ሽምግልናው በአሉታ ከተደመደመ በኋላ ሽማግሌ የላከው መምህር "ድሮም ሐጂ ራሳቸው ልጄን ከካፊር ወጥመድ አድንልኝ፣ አግባትና እያስተማርክ ቀስ ብለህ ታቃናታለህ፡፡ እኔ ራሴ ድል አድርጌ ደግሼ እድራችኋለው ብለውኝ እንጂ በሃሳቤም አልነበረች" እያለ ማስወራቱ ተሰማ፡፡ ይህን የሰሙ ቤተሰቦቼ በአባቴ ተግባር አንጀታቸው ቢያርም ደፍሮ የተናገረው ግን አልነበረም፡፡ ለእኔ ግን "ልጄ መሆኗን እጠራጠራለሁ" ካለው ንግግሩ በተጨማሪ ይህን ድርጊቱን ስሰማ ይበልጥ እጠላውና እፈራው ጀመር፡፡ ፍላጎቱን ለመፈፀም አሁንም እንዳልተኛልኝና ማንኛውንም ነገር ከማድረግ እንደማይመለስ እንደ አዲስ ተገነዘብኩ፡፡

የሽምግልናው ዕለት ሁመይድ ሰዓዳን ይዟት መጣና ምሳ ካልጋበዝኳችሁ ብሎ ተያይዘን ወጣን፡፡ ስለ ሁሉ ነገር በቂ መረጃ የነበረው ሁመይድ "አንቺ ብትደብቂኝም ሁሉን ነገር ሰማሁት" ብሎ ወቀሳ መሳይ ነገር አቀረበ፡፡ "ይህ ምን ተብሎ ይነገራል?" አልኩና "ከየት ሰማህ? ሰዓዳ ናት የነገረችህ?" ብዬ ጠየኩት፡፡ እርሱ ግን "ምን ይሄ የተሰወረ ነገር ነው እንዴ? ሁሉ የሚያወራው አይደል...ዛሬ ራሱ ሽማግሌዎች ስምሽን በእምቢታ ሲያነሱ ብቻሽን ሆነሽ ስቅ ከሚልሽ እኔና ሰዓዳ እናዳብርሽ ብለን ነው የመጣነው" አለና "አይደል እንዴ ሰዓዳ..?" እያለ እርሷን መኮርኮርና አዎንታዋን መፈለግ ጀመረ፡፡ ሰዓዳም በኩርኮራው እየተቁነጠነጠች "አዎ ሃሳቡን እርሱ ነው ያቀረበው፣ እኔ ደግሞ አፀደቅሁት" ብላ መፍለቅለቅ ጀመረች፡፡ ሰዓዳ ባለችበት ቦታ ሁልጊዜም ቁዘማና ድብርት ቦታ አይኖራቸውም፡፡ ተፈጥሮዋ ሆኖ ነው መሰል ተረጋግታ መቀመጥም ሆነ ዝም ማለት አይሆንላትም፡፡ በዚያ ላይ የማታመጣው ወሬና ጨዋታ የለም፡፡ ኃይለኛ የመረጃ ሰውም ናት፡፡ ንግግሯ በፈሊጥ ከመሆኑም በላይ ጊዜውንና ሁኔታውን ያገናዘበ ቀልድ መፍጠር፣ አዋዝታም ማቅረብ ትችልበታለች፡፡ አንዳንድ ጊዜ መንቀዥቀዧን ብታበዛውም በሰሚም ሆነ በተመልካች ዘንድ አትሰለችም፡፡ በተወሰነ መልኩም ቢሆን አደብ የማሲዛት እኔ ነኝ፡፡ ከአባቴ ጋር በፈጠርኩት ፀብና ቤታችን በገባው ያለመረጋጋት ይቺ ብልህና ተጫዋች እህቴ ቤታችን ውስጥ ባትኖር ኖሮ ሕይወት ለሁላችንም ከባድ በሆነ ነበር፡፡ አሁንም በዚሁ ጨዋታዋ እኔና ሁመይድን በሳቅ ስታፈርሰን ቆየች፡፡ በዚህ መሐል ሁመይድ ቁም ነገር መሳይ ጨዋታ ለማምጣት ደጋግሞ ቢሞክርም መሃላችን ሰዓዳ መኖሯን እየጠቆምኩ በዓይኔ ስገስፀውና ስከላከለው ቆየሁ፡፡ የዕለቱ ውሎአችን ሁመይድ እንዲሁ ከእኔ ጋር ለማውራት እንዳሰፈሰፈ እኔም እንደተከላከልሁ ተጠናቀቀ፡፡ በሁኔታዬ ስለተከፋም በታዛቢ ዓይኖቹ እየሸነቆጠኝ እታባ ቤት ካደረሱኝ በኋላ ወደመጡበት ተመለሱ፡፡

የአባቴ ኩርፊያ በቶሎ እንደሚበርድ ተገምቶ ነበር፣ እናቴ ራሷ "አሁን ሳምንት ሳይሞላው ይረሱታል" እያለች ለወንድሜም ለእኔም ለቤቱ ሰው ሁሉ ትናገር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አባቴ ወደ ቤት በመጣ ቁጥር በሆነው ባልሆነው እየተበሰጫጨ ቤተሰቡን ማመሱን ቀጠለበት፡፡ ለእኔ መልካም የሆነው ነገር "እዚህ ስመጣ ፊት ለፊቴ እንዳላያት በዚህ ከዘራ አናቷን ብዬ ነው የምገላግላት" ብሏል በመባሌ ከእርሱ ጋር መፋጠጤ መቅረቱ ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ከቤት እንዳልወጣና እንደፈለገኝ እንዳልሆን በእጅ አዙር ጥብቅ ቁጥጥር ያደርግብኛል፡፡ ሽምግልና ሲላክ የአባቴ ስውር እጅ ሊኖርበት ይችላል የሚል ጥርጣሬ ነበረኝ፡፡ እንደገመትኩትም መጨረሻው እንደዚያው ሆኗል፡፡ ይህንኑ ነገር ደግሞ ሽማግሌ ላኪው የራሱን ሞራል ለመገንባት በሚመስል መልኩ ለጀማው በማውራቱ አባቴ ኃፍረትና ንዴት ክፉኛ ተሰምቶታል፡፡ በዚያ ላይ ወንድሜ ፋይሰል ግፊቱን ተቃውሞ በኃይለ ቃል ስለተናገረውና እናቴም በአቅሟ ዘወትር እኔን ስለምትከላከል የብስጭቱ ተጨማሪ ግብዐት ሆኖታል፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋር የእኔ እንደ ልቡ አለመሆኔና የአባወራነት ሥልጣኑ ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል መላ ማምጣት ያለመቻሉ ሳያብከነክነው አልቀረም፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ ተወዳጁ አባቴን አመል ነሳው፡፡ ለወትሮው ታስቀው የነበረችው ሰዓዳን እንኳን ፊት ነስቷት በቀልዷ መዝናናቱን እርግፍ አድርጎ ትቶታል፡፡ ሲለውም ከአጠገቡ ውሻ አርጎ ያባራታል፡፡ ከፋይሰል ጋር በጣም አስፈላጊ የቢዝነስ ጉዳይ ካልሆነ በቀር መነጋገር አቁመዋል ማለት ይቻላል፡፡ እናቴንማ እንዴት ቁም ስቅሏን እንደሚያሳያት አትጠይቂኝ፡፡ ለተፈጠረው ምስቅልቅል ሁሉ እርሷን ተጠያቂ በማድረግ በነገር ይጠብሳታል፣ ሁላችንም ላይ ይዝታል፡፡ የእናቴ ሥጋት እርሱ እንዲህ ሲበሳጭ ደም ግፊቱ ጨምሮ የባለፈው ዓይነት ወይም ከዚያ የባሰ ጉዳት እንዳይደርስበት ነው፡፡ እርሱ ግን የእርሷን ዝምታ ከንቀት፣ ለልጆቿ የምታሳየውንም ፍቅር ከአድማ በመቁጠር ይብስ ይንጨረጨራል፡፡ ነገሮች በዚህ ሁኔታ እየባሱና ይበልጥ እየተወሳሰቡ ሄዱ፡፡

አባቴ አዲስ ባመጣው ዓመልና ቤተሰቡ ላይ በፈጠረው ጫና እኔ ከፍተኛ የሕሊና ስቃይ አተረፍኩ፡፡ ይህ ሁሉ ነገር በእኔ ምክንያት እንደመጣ በመቁጠር የጥፋተኝነት ስሜት ያንገላታኝ ጀመር፡፡ እኔን በገዛ እጁ ቢሰቅለኝ እንኳ በፀጋ ለመቀበል ብርቱ ነበርኩ፡፡ የእናቴ ሥቃይ፣ የወንድሜ በአባቴ ችላ መባል፣ የቤተሰቡን ሥጋት ግን መቋቋም እየተሳነኝ መጣ፡፡ ጊዜው የአዲሱ ዓመት ሁለተኛ ወር ቢሆንም አባቴ በገባው ቃል መሰረት ትምህርት መጀመሪያዬ ጊዜ ነበር፡፡ ነገር ግን የአባቴ ሁኔታ ዶክሜንቶቼን እንዲሰጠኝና ትምህርት እንድቀጥል መጠየቅ ይቅርና ጭራሽ የሚታሰብም አልነበረም፡፡ ይህ ሁሉ እየተደማመረ ራሴን እንደ ቤተሰቡ እንከን የመቁጠር ሃሳብ በአዕምርዬ እየገባ ያስጨንቀኝ ጀመር፡፡ ይህን ክፉ ሃሳብ ለመጋፈጥ አቅም ባላጣም ይህንን ችግር በሰይጣናዊ መንገድ አንዳርም ውስጤን የሚመክር ክፉ ሃሳብ እየደጋገመ በጭንቅላቴ ያቃጭልብኛል፡፡ ከዚህ በፊት ለማስፈራራትና ጫና ለማሳደር እናገረው የነበረው ራስን የማጥፋት ሃሳብ ሞገዱን ፀጥ የሚያደርግ ሁነኛ መፍትሔ ሆኖ በአዕምሮዬ ይሳልብኛል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አባቴ ጭራሽ ቤታችን የሚመጣበትን ጊዜ እየቀነሰ መጣ፡፡ ይህ እናቴ ላይ የሚፈፀም ግልፅ መድልኦና ትልቅ በደል ቢሆንም እርሱ ግን "እዚያ ስሄድ የማተርፈው ብስጭት ነው" እያለ ለቀሩት ሚስቶቹና ልጆቹ በማውራት የእኛን ቤተሰብ ማጥላላት ተያያዘው፡፡ በዚሁ ከቀጠለ እናቴን ሊፈታት ሁሉ እንደሚችል መገመት አያስቸግርም፡፡ እነዚህ ነገሮች የጦርነት አውድማውን ከውጭ ወደ ውስጥ አዞሩብኝ፡፡ ከአባቴና የእርሱን ሃሳብ ደግፈው እኔን ከሚያጠቁ ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥ የተሻለ ነበር፡፡ አሁን ግን በገዛ አዕምሮዬ ውስጥ ባለ አውደ ውጊያ ራሴ ከራሴ ጋር መፋለም ጀመርኩ፡፡ በጣም ሲጨንቀኝ ድንገት የዘነጋሁት ሃሳብ መጣልኝና ነጠቅ ብዬ ተነስቼ እማማ አፀደ ቤት ሄድኩ፡፡

የተቀጣጠርን ይመስል እማማ አፀደን ቤት ውስጥ ብቻቸውን ተቀምጠው አገኘኋቸው፡፡ የንባብ መነጽራቸውን ሰክተው የሆነ ደረሰኝ ነገር እየተመለከቱ ነበር፡፡ ሲያዩኝ ገና "ውይ አፊያ..ነይ ግቢ ልጄ" ብለው መነጽራቸው አውልቀው ከደረሰኙ ጋር ጠረጴዛ ላይ አኖሩትና አገላብጠው ሳሙኝ፡፡ አጠገባቸው ውሽቅ ብዬ ስቀመጥ እንደ ሕጻን ልጅ ራሴን ያሻሹኝ ጀመር፡፡ ይህን ሁኔታ መቋቋም የሚያስችል አቅም አልነበረኝምና ተንሰቅስቄ ማልቀሴን ቀጠልኩ፡፡ "እንኳን እናቴ ሞታብኝ እንዲሁም አልቅሽ አልቅሽ ይለኛል" እንደሚባለው ራሴን በእናትነት ወግ ሲደባብሱኝ ሆድ ባሰኝና መነፍረቄ በዛ፡፡ እማማ አፀደ የቅርብ ጎረቤትና የእናቴ ወዳጅ በመሆናቸው ብዙውን የቤታችንን ነገር ያውቁታል፡፡ ስለሆነም እኔ በውስጤ እየተሰማኝ ያለውን ክፉና አስጨናቂ ሃሳብ ስነግራቸው "ምነው ምነው ልጄ ምኑን አሰብሽው? ጠንካራም አልነበርሽ" ብለው አቅፈውና ራሴን ጭናቸው ላይ አስተኝተው አባበሉኝ፡፡ ለቅሶዬም እስኪወጣልኝ ጠበቁኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙ ነገር ስናወራ ቆየን፡፡ አባቴ በእልህና በጥላቻ ስሜት እኔን ብቻ ሳይሆን እናቴን፣ እህቴንና ወንድሜን በማጥቃት ላይ እንደሆነ፣ ቤት ቶሎ ቶሎ መምጣት እንደተወና ቀጥሎስ ምን እንደሚያደርግ እንደማይታወቅ በሥጋት ነገርኳቸው፡፡ አያይዤም "እኔ ላይ የፈለገውን ቢያደርግ ግድለየኝም፣ ነገር ግን በእኔ ምክንያት የገዛ ሚስቱና ልጆቹ ላይ የሚያደርገውን ነገር መቋቋም አልቻልኩም፡፡ ከፍተኛ የጥፋተኝነት ስሜት እየተሰማኝ ነው፡፡ ይሄን ከማይ ... ብር ብዬ ብጠፋ እመርጣለሁ" አልኩና ሳጌን ለማቆም ታገልኩ፡፡

እማማ አፀደ ዝም ብለው ሲሰሙኝ ቆዩና ጉሮሮአቸውን አፅድተው ፀጉሬን እያሻሹ እንዲህ አሉኝ፡፡ "ይኸውልሽ ልጄ...ያንቺን ፍላጎት፣ የተጋፈጥሽውንም ፈተና፣ ያሳየሽውንም ተጋድሎ በደንብ ስከታተልና ሳደንቅ፣ በአቅሜም ስፀልይልሽ ቆይቻለሁ፡፡ ደግሞም እናትሽ ነኝ፡፡ እናም እስቲ የእናትነት ምክርና አስተያየት ልስጥሽ" አሉና ዓይኔን ፍለጋ ወደኔ ጎንበስና ዞር አሉ፡፡ እንባ ባቀረረው ዓይኔ እያየኋቸው "እኔም እኮ ሲጨንቀኝ ይህንኑ ፍለጋ ነው የመጣሁት" አልኳቸው፡፡ "አይዞሽ ልጄ" ብለው ይበልጥ ጥብቅ አርገው እያቀፉኝ ቀጠሉ፡፡ "ዝም ብዬ የአንቺን ነገር ሳስተውለው የፈተናሽ ብዛቱና ያንቺም ጽናት ከቅዱሳን አንስትና ከሰማዕታት ጋር ብዙው ነገር ይመሳሰልብኛል፡፡ ከቅድስት አርሴማ፣ ከቅድስት ኢየሉጣ፣ ከወለተ ጴጥሮስ፣ ከሌሎቹም ቅዱሳን ሴቶች ጋር፡፡ እኒህ ቅዱሳን የተጋፈጡት ፈተናና ያሳዩት ጽናት እጅግ ትልቅ ስለሆነ ለእንዲህ ያለው ደረጃና ክብር መመረጥም ያስፈልጋል፡፡ አንቺ ምንም እንኳ እስካሁን ያሳየሽው ተጋድሎ የዚህ ዘመን ሰማዕት ሊያሰኝሽ ቢችልም ቤታችሁ ካለው የገነገነ ችግር የተነሳ እንዳትሰበሪብኝ እሰጋለሁ፡፡ ይሄን ያሳሰበኝ ልጄ ስለሆንሽና ስለምሳሳልሽ ሊሆን ይችላል" አሉና ጥቂት ዝም አሉ፡፡ ቀና ብዬ እያየኋቸውና "ምን ሊሉኝ ነው?" የሚል ጉጉት እየናጠኝ "ታዲያ ምን አድርጊ እያሉኝ ነው?" ስል ጠየኳቸው፡፡ ረጋ ብለው ቀጠሉ "አንዳንድ ጊዜ እንደ ተራራ የገዘፈ ችግር ሲገጥመን ጽናታችን ብቻ፣ መጋፈጣችን ብቻ፣ ቁርጠኛነታችን ብቻ ለውጤት ላያበቃን ይችላል፡፡ በተጨማሪ ብልሃት ያስፈልገናል፡፡ አውሎ ነፋሱን ጎንበስ ብሎ የማሳለፍ ጥበብ፣ እንደ እሳት የሚነድ ቁጣን በለዘብታ ቃል የማብረድ ዘዴ፣ የሰይጣንን እብሪት በትሕትና ድል የመንሳት መላ ያስፈልጋል፡፡ መጽሐፉም "እንደ ርግብ የዋሕ እንደ እባብም ብልህ ሁኑ" ነው የሚለው፡፡ አሉና አሁንም ጥቂት ዝም አሉ፡፡ ዝም ባሉ ቁጥር የእኔን ስሜትና ግብረ መልስ እያጠኑ ነበሩ፡፡

የእምነትና የጽናት ተምሳሌቴ እኚህ ጎምቱ አዛውንት ዛሬ ምን እያሉኝ ነው? ስል አሰብኩና "ታዲያ ይህ የሚሉኝ ጥበብ ምንድነው?" አልኩ እንዳቀረቀርኩ፡፡ "በሆነ መንገድ ከአባትሽ ተፅዕኖ መላቀቅ አለብሽ" ሲሉኝ ክው አልኩ፡፡ "ይሄን ቃል የት ነበር የሰማሁት?" ቃሉን ከማስታወስ የእርሳቸውን ሃሳብ ማስጨረስ የተሻለ እንደሚሆን በቅጽበት አስቤና ወስኜ "እንዴት?" አልኳቸው፡፡ "ስፈልግ የኖርኩት ይህንኑ ነፃነት መሆኑ እንዴት ተሰወረባቸው?" ብዬ በማሰብ እየተደነቅሁ፡፡ እርሳቸው ግን "በሆነው መንገድ" አሉኝ፡፡ "በሆነው መንገድ...በጋብቻ ሊሆን ይችላል፣ የራስሽን ሥራ በመጀመር ሊሆን ይችላል፣ ወደ ውጭ ሀገር በመሄድ ሊሆን ይችላል...ብቻ በሆነው መንገድ ይሁን፡፡ የሚፈለገው መንገዱ ሳይሆን ውጤቱ ነው" አሉ፡፡ ለጥቂት ደቂቃ ያሉትን አማራጮች በውስጤ አውጠነጠንኳቸው፡፡ የራስን ሥራ መጀመር ያሉት በድፍረትና በኃይል ቤቱን ጥዬ መሄድን ተከትሎ የሚመጣ እንጂ በሰላምና በአባቴ ፈቃደኝነት የሚታሰብ አይደለም፡፡ እንኳን ሥራ ቀርቶ ትምህርት እንኳ እንዳልቀጥል በክፋትና በጥበብ ያስቀመጠውን የእንቅፋት ድንጋይ ቤተሰቤ ሁሉ ያውቀዋል፡፡ ቤቱን ጥዬ ሄጄ ይህን አማራጭ ብሞክር እንኳ የሚገጥሙኝ ፈተናዎች እንዳሉ ሆነው የቤተሰቤን ሰላም ከድጡ ወደ ማጡ የሚከት ነው፡፡ ወደ ውጭ ሀገር የመሄድን አማራጭም ከዚህ በፊት ለአባቴ አቅርቤለት አምርሮ የተቃወመው ሃሳብ ነው፡፡ ይህን ሃሳብ እርሱ የሚያየው ይበልጥ ካፊር ለመሆን መርቆ እንደ መሸኘት አድርጎ ነው፡፡ የጋብቻን አማራጭ ግን እማማ አፀደ እንዴት ሊያስቡት እንደቻሉ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ "ያዘጋጁልኝ ባል አለ እንዴ?" ስል አሰብኩና በራሴ ሃሳብ ፈገግታዬ አመለጠኝ፡፡ እንደገና መልሼ ደግሞ "ነው የጋብቻ ሽምግልናውን በአሉታ መመለሴን እየተቃወሙ ነው" ብዬ በማሰብ ተገረምኩ፡፡

ካቀረቀርኩበት ቀና ብዬ ወደ ውጭ ለመሄድ ለአባቴ ሃሳብ አቅርቤለት በምን አይነት ምሬት እንደተቃወመውና የራሴን ሥራ መጀመርም የሚፈጥረውን ሁከት በአጭሩ ካብራራሁላቸው በኋላ "ባል ማግባት የሚለውን አማራጭ ለምን እንዳቀረቡት ግን አልገባኝም፣ ክርስቲያን ባል አግቢ ማለቶት ነው ወይስ የአባትሽን ፈቃድ ፈፅሚ እያሉኝ ነው?" ስል በቀጥታ ጠየኳቸው፡፡ እርሳቸው ግን በዚያው እርግት ባለ አነጋገራቸው "ሁለቱንም ማለቴ አይደለም" አሉኝ፡፡ እኔም ወደርሳቸው ዞሬ ግራ ከተጋባ ገጽታዬ ጋር "እና ምን ማለቶት ነው?" በሚል አስተያየት አየኋቸው፡፡ ገልመጥ ብለው ገጽታዬን አዩና በፍጥነት እንደገባቸው ሁሉ "የትኛውንም አማራጭ አወዳድሮ የተሻለ ውጤት የሚያመጣውን መምረጥ ብልህነት ነው፡፡ ቢቻል አባትሽን ጨምሮ ሁሉንም ቤተሰብ የሚያስደስት የአንቺንም ዓላማና ፍላጎት የሚያሟላ፣ ካልሆነም ኪሳራውና የሚከፈለው ዋጋ አነስተኛ ሆኖ የአንቺን ፍላጎት የሚያሳካውን መምረጥ ይኖርብሻል" አሉኝ፡፡ በንግግራቸው ይበልጥ ዞሮብኝ እንደተደናገርኩ ጥቂት ደቂቃዎች አለፉ፡፡ ሆን ብለው ከእነ አዕምሮ ውዝግቤ የተዉኝ የሚያስመስልባቸው የዝምታ ጊዜ ሲያበቃ "እኔ የምልሽ አፊያ" ብለው ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ወደ እኔ ዞር አሉ፡፡ ድምፀታቸውም ከእስካሁኑ እርጋታ በመጠኑ ፈጠን ያለና ኃይል የተሞላ ነበረ፡፡ እኔም ባልረጋና ሥልት በሌለው አኳኋን ከሃሳብ ሃሳብ ሲዘል የነበረውን አዕምርዬን ሰብስቤ "አቤት እማማ አፀደ" አልኩ፡፡ ፊት ለፊቴ በሚመረምር ዓይኖቻቸው አተኩረው እያስተዋሉኝ "ይሄ ቤታችሁ የሚመላለሰው ክልስ ማነው?" ሲሉ ጠየቁኝ፡፡

ሜሪዬ..እንደዚያ ቀን ድንግጥ ያልኩባቸው ጊዜያት ቢቆጠሩ ከአንድ እጅ ጣቶች አያልፉም፡፡ ብቻ ክው ስል እርሳቸውም በደንብ አስተውለውኝ ነበረ፡፡ ከድንጋጤዬ ሌላ የሚያስደንቅ መገረምም በውስጤ ሲመላለስ ይታወቀኛል፡፡ በውስጤ "እኚህ ሴቲዮ የነቢያት ዘር አለባቸው እንዴ?" ስል ራሴን ደጋግሜ ጠየኩ፡፡ ሑመይድ ያቀረብልኝን ሃሳብ ለማንም አልተነፈስኩም፡፡ እርሱም ለሌላ ሰው ያወራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በእርግጥ ቤታችን መመላለሱን ከቢዝነስ ጉዳዮች ሌላ እኔ ላይ ፍላጎት አሳድሮ በመሆኑ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጎረቤት በቀላሉ መገመት አያዳግተውም፡፡ እኔን በእጅጉ ያስደነቀኝ ሑመይድ ያቀረብልኝ ሃሳብ በእማማ አፀደ እንደ አማራጭ መፍትሄ ከመቅረቡም በላይ ስለ እርሱ ማንነት ጥያቄ ማንሳታቸው ነው፡፡ ከሁሉ ደግሞ  "ቢቻል አባትሽን ጨምሮ ሁሉንም ቤተሰብ የሚያስደስት የአንቺንም ዓላማና ፍላጎት የሚያሟላ.." ሲሉ ያቀረቡት ሃሳብ የሑመይድ ንግግር ኮፒ ፔስት መሆኑ ነው፡፡ ሑመይድ ያንን የጋብቻ ጥያቄ ሊያስገኝልኝ ከሚችለው ጥቅም ጋር አሰናስሎ ሲያቀርበው እጅግ ተጨንቄ እማማ አፀደን ለማማከር ወስኜ ነበር፡፡ ሆኖም በዝንጋታና በተለያዩ ያለመገጣጠሞች ሳላማክራቸው ቆይቼ በእንዲህ ያለ ሁኔታ የእርሱን ገለፃ የሚመስል ንግግር ከእርሳቸው ማድመጤን አጋጣሚ ነው ብሎ ማለፍ ከባድ ነበር፡፡ እኔ የውስጤን አግራሞት ሳዳምጥ እርሳቸው ፊቴ ላይ ያስተዋሉትን ድንጋጤ ታዝበው "ምነው ልጄ ደነገጥሽ? ጥያቄው ያስደነግጣል እንዴ?" አሉኝ አይናቸውን ከዓይኔ ሳይነቅሉ፡፡ ፈገግ እያልኩ "አይ ገርሞኝ ነው" አልኳቸው፡፡ "ምኑ ነው ያስገረመሽ?" አሉኝ ዜማ ባለው አነጋገር፡፡ እኔም ስለ ሑመይድ ማንነት፣ ስለሚከተለው የአኗኗር ዘይቤ፣ ስላቀረበልኝ የጋብቻ ጥያቄ፣ ስለገባልኝ ቃል፣ ያስገኘዋል ብሎ ስለሚያስበው ጥቅምና እኔ ስለሰጠሁት ምላሽ በዝርዝር ነገርኳቸው፡፡ ይህንኑ ነገር ከባለፈው ሽምግልና በፊትና ሑመይድ በነገረኝ ሰሞን ላማክራቸው አስቤ እንደነበርና በዝንጋታና በተለያየ ምክንያት እንደዘገየሁ ጨምሬ አስረዳሁ፡፡

እማማ አፀደ ሲያወጡ ሲያወርዱ ከቆዩ በኋላ "ለምክሩ እንኳን ብዙም አልዘገየሽ፣ ለሌላው ጊዜ ግን ወደ ልብሽ የመጣን ነገር አታሰንብቺው፡፡ ይህ ነገር እስከመቼ እንደዚህ ይቀጥላል? የሚለው ነገር ግን የእኔም የዘወትር ጭንቀት ነው፡፡ እንጃ...እስቲ ጸልዪበት ልጄ፡፡ እኔም ለማያልቅበት ጌታ ለመድኃኔዓለም እነግረዋለሁ" አሉ ሁለት እጃቸውን ዘርግተው በዓይኖቻቸው ሽቅብ እያንጋጠጡ፡፡ ቀጠሉናም "አየሽ...መድኃኔዓለም ያዘጋጀልሽ የዚህ ፈተና መውጫ ቀዳዳ ይሆን እንደሆን ማን ያውቃል? ብቻ አንድን ሃሳብ በቅጡ ሳያስቡበትና ሳይፀልዩበት በጥቁርም በነጭም መነጽር ማየት አይገባም፡፡ ብዙ ጊዜ እኛ የሚበጀንን አናውቅም፡፡ ለውሳኔ የምንዘገይና የምንፈራ ስለሆንን ብዙ አጋጣሚዎችና መልካም ዕድሎች ያመልጡናል፡፡ በአላስፈላጊ ጥድፊያም ለበርካታ ወጥመዶች እንዳረጋለን፡፡ ስለዚህ ተረጋግቶ ብዙም ሳይዘገዩ፣ ተካልበውም ሳይጣደፉ ማሰብና አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ ይገባል፡፡ እስከዚያው ግን ይህን ሰው ሳትገፊውም ልብሽን ሳትሰጪውም በወዳጅነት አቆዪው፡፡ ይህ ነው የሚሻለው ልጄ" አሉና በብዙ የእናትነት ምክርና ምርቃት አሰናበቱኝ፡፡ ወደ ቤት ከገባሁ በኋላ አንድ ሰሞን አስጨንቆኝ የነበረው ይህ ሃሳብ አዲስ አጀንዳ ሆኖ አዕምሮዬን ያምሰው ጀመር፡፡ በሁኔታው ጊዜና ሥፍራ ሳልመርጥ እየደጋገምኩ በአጭሩም በረዥሙም እፀልያለሁ፡፡ የእማማ አፀደ ሃሳብ ይሁን፣ የጸሎቴ ውጤት ይሁን፣ ወይም ደግሞ ነፃ የመውጣት ጉጉቴ የፈጠረብኝ ተፅዕኖ ይሁን ባላውቅም የሑመይድ ሃሳብና ጥያቄ አዎንታዊ ጎኑ እየጎላብኝ ሲመጣ ይታወቀኝ ነበር፡፡

ከአራት ቀን በኋላ ታሪከኛው አባቴ በክፋቱ በመቀጠል ቤተሰቡን በሙሉ ያበሸቀ ሌላ ተጨማሪ ነገር አደረገ፡፡ አባቴ ያሉት ንብረቶችና የንግድ ሥራዎች ባልተፃፈ ሕግና በልማድ በሦሥቱ ቤተሰቦቹ ተከፋፍለው የተያዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በእኔ ስም የሚጠራ አንድ ባለ አራት ፎቅ ሕንጻ፣ ወንድሜ ፋይሰል የሚያስተዳድረው የቡና ላኪ ድርጅትና ሌሎች ሁለት ሱቆች በእኛ ቤተሰብ የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ የቀሩትም ሁለት ቤተሰቦች እንዲሁ የሚቆጣጠሯቸው በቂ ቢዝነሶች አሏቸው፡፡ ታዲያ ሐጂ ሁሴን ሆዬ ቡና ኤክስፖርት ከሚያደርገው ድርጅቱ ለፋይሰል የሰጠውን ሙሉ ውክልና በማንሳት ሃላፊነቱንም ውክልናውንም ኢብራሒም ለሚባል ከሌላኛው ሚስቱ ለሚወለድ ልጅ ይሰጠዋል፡፡ ይህን የሰማው ወንድሜ እንዴት እንደተቃጠለ አትጠይቂኝ፡፡ በእርግጥም ፋይሰል ይህ ሥራ ብዙ ልምድ ያካበተበትና ትልቅ ደረጃ ያደረሰውም ነበር፡፡ በቂ ልምድና ችሎታ ለሌለው ሰው ሃላፊነቱን ማስተላለፉ የአባቴን በቀለኝነት ያመላከተ ነውረኛ አካሄድ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ይህን ሁሉም ቤተሰብ የተገነዘበው ሲሆን እኔ ደግሞ ይበልጥ ሃላፊነት በመውሰድ የተበሳጨ ወንድሜን አቅፌ አባበልኩት፡፡ "አይዞህ እኔ ሁሉንም አስተካክለዋለሁ" ስለው ከእቅፌ እየወጣ በመገረም ያየኝ ነበር፡፡ ይህን ጉዳይ ተሰብስበን በምናወራበት ምሽት ቤተኛው ሑመይድ "ጤና ይስጥልኝ...እንዴት አመሻችሁ?" እያለ ገባ፡፡ ከጥቂት የሰላምታ ግርግርና ጨዋታ በኋላ አንድ እያሉ ወጥተው እኔና እርሱ ብቻ ሳሎኑ ውስጥ ቀረን፡፡ "ምንድነው ኤፊ ችግር አለ? ሁላችሁ የሆነ ድብርት ውስጥ ትመስላላችሁ" አለ፡፡ በአጭሩ አባቴ ያደረገውንና ሰሞኑን እየሆነ ያለውን ነገርኩት፡፡ ጥቂት እንደ መተከዝ ብሎ ፈገግ አለና "ኤፊ ቆንጆ የመፍትሄ ሃሳብ አቅርቤልሽ ነበር...አንቺ ግን እምቢ አልሽ" አለ፡፡ ንግግሩ ከፈገግታው ጋር የፈጠረውን ሕብር ሳይ ለምን እንደሆነ ባላውቅም ብሽቅ አረገኝ፡፡ ለአፍታም ቢሆን አስጠላኝ፡፡ ቀጠለናም "ኤፊ..ያን ጥያቄዬን ባትቀበዪውም እስቲ በሌላም መንገድ ቢሆን ችግርሽን እንድካፈል ፍቀጂልኝ" አለና እጁን ዘረጋልኝ፡፡ በጥርጣሬ ዓይን እያየሁትም ቢሆን እጄን ሰጠሁት፡፡ "አመሰግናለሁ ኤፊ" አለና ብድግ ብሎ እጄን ሳመና ተቀመጠ፡፡

                        (ይቀጥላል)

     --------- ማርያማዊት ገብረመድኅን ---------

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የምዕራፍ አምስት(፭)የ46 የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ

✝በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡ አሜን! ↪️የምዕራፍ አምስት(፭) 46ኛ ዙር የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ⤵️ 1⃣ ቅዱስ ያሬድ ከመላዕክት የተማራቸው ሦስቱ የዜማ ዓይነቶች ምን ምን ናቸው?ሞገር...