2017 ዲሴምበር 28, ሐሙስ

አፊያ ሁሴን ክፍል 10

#አፊያ #ሁሴን ክፍል 10

ፀሀፊ #ማርያማዊት ገብረ መድህን

አንባቢ #ገብረ ሚካኤል

አፊያ ሁሴን (ክፍል ፲)

ከአንድ ሳምንት በኋላ ሁመይድ ደወለና አንድ ካፌ ውስጥ ቀጠረኝ፡፡ ሰርፕራይዝም አለሽ በማለት አጣደፈኝ፡፡ ብቻዬን እንድመጣም ለመነኝ፡፡ በቦታው ስደርስ ለብቻዬ እንድመጣ የወተወተኝ ብቻችንን ነፃ ሆነን ለማውራት እንዲመቸንና የያዘው ርዕስም ሌላ ሰው ማወቅ እንደማይገባው ስላመነ መሆኑን ሊያስረዳኝ ብዙ ጣረ፡፡ ሰርፕራይዝ ያለውና ሌላ ሰው እንዳይሰማው የፈለገው ነገር ባለፈው "እንድረዳሽ ፍቀጅልኝ" ብሎኝ የተስማማሁትንና አባቴ ቤተሰቤ ላይ እየፈጠረ ስላለው ችግር ነው፡፡ ፊት ለፊቴ ሆኖ አይን አይኔን እያየ "ከሐጂ ጋር በነገርሽኝ ነገር ላይ ተነጋግረን ነበር፡፡ እናም የቡና ላኪ ድርጅቱን ሃላፊነትና ውክልና ለፋይሰል ሊመልሱለት ተስማምተናል" አለኝ፡፡ በጣም ተደንቄ "እውነት...?!" አልኩት መዳፌን እየዘረጋሁለት፡፡ "really" አለ እኔ ባወጣሁት ዜማና መዳፌን በመሐላ መልክ እየመታ፡፡ በሰበቡም እጄን በእጆቹ ይዞ እያፍተለተለ ቆየ፡፡ "ያው ታውቂያለሽ ከሐጂ ጋር ቢዝነስ ፓርትነር ነን፡፡ ስለሆነም ቤት ያልተለመደ ፀባይ ማሳየታቸውንና የፋይሰልንም ሃላፊነት እንደነጠቁት ገልጬ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ጠየኳቸው፡፡ እርሳቸውም መንስኤው አንቺ እንደሆንሽና ቤተሰቡ በጠቅላላ አድማ እንዳረጋችሁባቸው በከፍተኛ ንዴት ገለፁልኝ፡፡ እኔም ችግሮች በውይይት መፈታት እንዳለባቸውና በተለይ ነገሩን ከቢዝነስ አንፃር ስናየው ፋይሰል ብዙ ልምድ ካካበተበት ሥራው ማንሳት ፈፅሞ ተቀባይነት እንደሌለው ቆይቶም ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው ነገርኳቸው፡፡ ሥራን በእልህና በስሜት ለማስኬድ መሞከር በዘመናዊ የቢዝነስ አመራር ዘዴ ለውድቀት እንደሚዳርግ አስጠንቅቄ አሳሰብኳቸው፡፡ ያንቺንም ችግር በተመለከተ ከፈቀዱልኝ እኔም የመፍትሔው አካል በመሆን ላግዝ እንደምችል ገለፅኩላቸው፡፡ ከዚያ ትክክል እንደተናገርኩ አረጋግጠውልኝ የፋይሰልን ሥራና ሃላፊነት በቅርቡ እንደሚመልሱለት ቃል ገቡልኝ፡፡ አንቺንም የተሻለ ተግባቦት ካላችሁ እስቲ እባክህ ምከርልኝ ሲሉ አደራ ብለውኛል" አለና ፈገግ አለ፡፡

አባቴ እንዲህ በቀላሉና በፍጥነት ሃሳቡን የማለሳለሱ ነገር ከፍተኛ አግራሞት ፈጠረብኝ፡፡ በእርግጥ ለሁመይድ ትልቅ አክብሮት እንዳለው አጠያያቂ አይደለም፡፡ ቢሆንም ይህን ያህል በፍጥነት ውሳኔውን ይቀይራል ብዬ አልጠበኩም ነበር፡፡ ምናልባት የቡናው ንግድ አሳስቦቶ ይሆን? ስል አሰብኩ፡፡ ፋይሰል በዚህ ሥራ ላይ ብዙ ጊዜ በማሳለፉ ከፍተኛ ልምድ አካብቷል፡፡ ከሥራው ጋር የተያያዙና ጠቃሚ የሆኑ በርካታ ሰዎችንም ያውቃል፡፡ የአባቴ ውሳኔ እልህ የወለደው እንደሆነ ገብቶት ነው ወይስ ሁመይድ ሲያናግረው ይሉኝታ ይዞት...? ለማንኛውም ለእኔ እጅግ በጣም ያሳሰበኝ የፋይሰል ሁኔታ ነበርና ይህንኑ ዜና ልነግረው ቸኩያለሁ፡፡ ይህን መሰሉን ነገር ፀጥ ብዬ እያብሰለሰልኩ እያለሁ ፊቴ የተቀመጠው ሁመይድ "ኤፊ ይህን ነገር ግን ለማንም አትንገሪ... ሐጂ በራሳቸው ተነሳሽነት ነገሩን እንዳስተካከሉት እንዲሰማቸው እፈልጋለሁ" አለኝ፡፡ ሃሳቡ ቢገባኝም እኔ ደግሞ ለፋይሰል የተፈጠረውን ችግር እንደማስተካክለው ቃሌ ገብቼለት ስለነበር ይህንኑ በስሱም ቢሆን ብነግረው ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ስለሆነም ለሁመይድ ችግሩ ሁሉ የተፈጠረው በእኔ ምክንያት መሆኑን እየደጋገምኩና እያስረገጥኩ ከተናገርኩ በኋላ አያይዤም "ለፋይሰል ሁኔታዎችን እኔ ራሴ እንደማስተካክለው ቃል ገብቼለታለሁ" አልኩት፡፡ "so..?" አለኝ መቀመጫው ላይ እየተመቻቸ፡፡ "ስለዚህ የአባቴን ሃሳቡን የመቀየር ዜና ልነግረው እፈልግ ነበር...አንተን ቅር ካላለህ" አልኩት አተኩሬ እያየሁት፡፡ "እሺ..." አለ እየተኩመሸመሸ፡፡ ሁኔታውን ሳየው "ይህ ሰው በእርግጥ ከእኔ ፍቅር ይዞታል እንዴ?" ስል በሃሳቤ ራሴን ጠየኩ፡፡ አያይዞም "እሺ ኤፊ ነገሩ ምስጢር ቢሆን እመርጥ ነበር፣ አንቺ ካልሽ ግን ለሌላ ሰው እንዳያወራና ምንም እንዳላወቀ እንዲያስመስል አስጠንቅቀሽው ንገሪው፡፡ ሐጂ ከአንቺ ጋር ተነጋግሬ ጉዳዩን እንዳነሳሁባቸው ባያውቁ የተሻለ ነው" አለ፡፡ እኔም "ትክክል ነህ ሁመይድ... እኔም እንደዚያ ነው የማስበው" አልኩት፡፡

ሁመይድ ጥቂት በሃሳብ እንደመዋጥ ካረገው በኋላ "ኤፊ..እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቅሽ?" አለ ፊቱ ላይ የሆነ የሥጋት ገፅታ እየታየበት፡፡ "ምን..?" አልኩት ቀልጠፍ ብዬ፡፡ በፍጥነት ፈገግታው ጠፍቶ መልኩ እንደ መወየብ ስላረገው በውስጤ እየገረመኝ ነበር፡፡ እንዳቀረቀረ "ለፋይሰል ችግሩን እንደምታስተካክዪው ቃል የገባሽለት በምን መንገድ ለማስተካከል አስበሽ ነው? ሌላ የማስተካከያ ዘዴ ነበረሽ?" ሲል ጠየቀኝ፡፡ ጥያቄውን እንደሰማሁ ሳቄ ተናነቀኝ፡፡ ምስኪን ሁመይድ የወንድሜንና የቤተሰቤን ችግር ከማይ የአባቴን ፈቃድ ፈፅሜ እርሱ ያመጣልኝን ባል ለማግባት የምስማማ መስሎታል፡፡ ወይም ደግሞ ሌላ የተለየ መንገድ ኖሮኝ የፎከርኩ መስሎት ነው ሥጋት በውስጡ የገባው፡፡ እንደምንም ያፈነኝን ሳቅ ተቆጣጥሬና ኮስተር ብዬ "የለኝም" አልኩት፡፡ ቀና ብሎ በጥርጣሬ ሲመለከተኝ "በእውነት ሌላ መንገድ አልነበረኝም፣ አንተን ተማምኜ ነው" አልኩት፡፡ ፊቱ ከደመና መሐል በምትወጣ ጸሐይ ምክንያት ብሩህነትን በቅጽበት እንደምትላበስ የምድር ገጽ እዚያው በዚያው ሲፈካ ሳየው ሳላስበው ፈገግ አልኩ፡፡ "really..? ትተማመኝብኛለሽ ኤፊ? በእኔ ትተማመኛለሽ?" አለ እንደመቆምም እንደመቀመጥም እያረገው፡፡ ያለ አንዳች ሃፍረት እየተፍለቀለቀ፣ እጄን እየሳመና እየተቁነጠነጠ የሚሆነውን ሲያሳጣው እኔ በሃፍረት ተሸማቅቄ ላልቅ ደረስኩ፡፡ የእርሱ ሁኔታ ካፌው ውስጥ ያሉትን ሰዎች ትኩረት በመሳቡ ወደ ግራ ወደ ቀኝ መዞር እንኳ አፈርኩ፡፡ ከሥንት መቁነጥነጥ በኋላ ተረጋጋና "ይህን ቃል ከአንቺ በመስማቴ የተሰማኝን ደስታ ልደብቅ አልችልም...ለምን ሌላ ቦታ ሄደን በቆንጆ ራት አናከብረውም?" አለኝ፡፡ ወደ ቤት ቶሎ መመለስ እንዳለብኝ ገልጬ የራት ግብዣው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍልኝ ጠየኩ፡፡ እርሱም "በእኔ ላይ ያለሽን እምነት እንድትጨምሪ እለምናለሁ፡፡ ከዚህም ለበለጠ ነገር ለመታመን ዝግጁ ነኝ" አለና ተያይዘን ወጣን፡፡ ወደ ቤት ከመግባቴ በፊት ስላደረገልኝ ነገር ልባዊ ምስጋናዬን አቅርቤ ተሰነባበትን፡፡

ነገሮች በዚህ ሁኔታ እያሉ ጥቂት ቀናት አለፉ፡፡ ለወንድሜ ፋይሰል ለሁመይድ ያለውን ችግር እንደነገርኩትና እርሱም አባቴን በማናገርና በመምከር የእርሱን ሥራና ሃላፊነት እንዲመልስለት እንዳሳመነው ነገርኩት፡፡ ይሁን እንጂ ወንድሜ በጸጥታ ካዳመጠኝ በኋላ ክፉም ደግም ሳይናገር ሄደ፡፡ አተኩረው ሲያዩኝ የነበሩ ዓይኖቹ ውስጥ በውስጡ የሚመላለሰውን ሃሳብ ለማግኘት አዕምሮዬን አስጨነኩት፡፡ ነገር ግን የተጨበጠና ወጥ የሆነ ሃሳብ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ታላቄ እንደመሆኑ መጠን የቤተሰቡን ችግር ለመፍታት ከአቅሜ በላይ የሆነ ሸክም ተሸክሜ መንገላታቴን አይቶ ያዘነልኝ መስሎ ተሰምቶኛል፡፡ በአባቴ በቀለኛ አካሄድ ያለልክ በመበሳጨቱ የነጠቀውን ሥራ መልሶ ቢሰጠውም ባይሰጠውም የማይበርደውም የማይሞቀውም የሚመስል ዓይነ ውሃም አይቼበታለሁ፡፡ በቤተሰብ ጉዳይ የሁመይድ ጣልቃ መግባትና የእርሱ እርዳታ ማስፈለጉም ከክብር አንፃር ምቾት ያልፈጠረለትም ይመስላል፡፡ ምናልባትም ይህን ችግር ለመፍታት ስል እኔ ይዤ የኖርኩትን ክብርና ኩራት እንዳላጣም ሰግቶ ይሆናል፡፡ ብቻ ምንም ይሁን አንዳች ሳይተነፍስ ሄደ፡፡ ዝምታው ትንሽ ቢያስጨንቀኝም እንዲህ ያለው የወንዶች እልህ ተፈጥሯዊ መሆኑን በማሰብ ራሴን አሳመንኩት ወይም ሸነገልኩት፡፡ ከሁመይድ ጋር ካወራን ከአንድ ሳምንት በኋላ አጠር ላለ የሥራ ጉዳይ ነው ብሎ ወደ እንግሊዝ ተጓዘ፡፡ እርሱ በሄደ በአሥረኛው ቀን አካባቢ አባቴ የቡናውን ንግድ ድርጅት ውክልና ሞልቶ መጥቶ እንዲፈርምና ሃላፊነቱንም እንዲረከብ ለፋይሰል ደውሎ ነገረው፡፡ ወንድሜ ክፉኛ አንገራግሮ የነበረ ቢሆንም በእኔና በእናቴ ግፊትና ልመና ጭምር ሄዶ ፈረመ፡፡ ሃላፊነቱንም መልሶ ተረከበ፡፡

ሁመይድ እንግሊዝ ሀገር ሳለ ሌላ ጊዜ አርጎት በማያውቀው ሁኔታ በየቀኑ ይደውልልኛል፡፡ የለንደንንና ሌሎች የእንግሊዝ ከተሞችን በወፍ በረር ያስቃኘኛል፡፡ እዚያ ስለሚገኙ ታሪካዊ ሥፍራዎች፣ ሙዚየሞች፣ አርት ጋለሪዎች፣ ሐውልቶች፣ ቤተ መጻሕፍቶችና ሌሎች መስህቦች ገለፃ ያደርግልኛል፡፡ አያይዞም እኔ ፈቃደኛ ከሆንኩ ምንም ዓይነት ምትክ ውለታ ሳይጠይቅ እንግሊዝንና ሌሎች የአውሮፓ ሀገሮችን እንደሚያስጎበኘኝ እየደጋገመ ከመሐላ ጋር ይነግረኛል፡፡ በአንፃሩ አባቴ ደግሞ ለፋይሰል ሥራውን ከመለሰለት በኋላ በዚያው ኩርፊያው ቀጥሏል፡፡ ጥቂት የተሻሻለው ከፋይሰል ጋር የነበረው ግንኙነት ብቻ ነው፡፡ የሥራ ጉዳይ የግድ ስለሚያገናኛቸው በጥቂቱም ቢሆን ያወራሉ፡፡ እንደ ወትሮው ቤት የመምጣቱን ነገር ካቋረጠ በኋላ ይህን ነገር ሳያሻሽል መቆየቱ ሁልጊዜ ያሳስበኛል፡፡ በሳምንት አንዴ ብቅ ይልና እየተጎማለለ ግቢው ውስጥ ይዟዟራል፡፡ በትንሽ በትልቁ እናቴ ላይ ይጮሃል፡፡ በገዛ እጁ ከሚፈቀር አባት ወደሚፈራ ንጉሥ ራሱን ስለቀየረ የቤቱ ሰው ሁሉ በተቻለው መጠን ከእርሱ ለመራቅ ይጥራል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በድፍረት ላናግረውና በእኔ ምክንያት ቤተሰቡን ሁሉ ማወክ እንደሌለበት ነግሬው ከፈለክ እኔን የፈለከውን ማድረግ ትችላለህ ልለው አስባለሁ፡፡ ነገር ግን መልሼ ይህ ስሜታዊነት ነው ብዬ እተወዋለሁ፡፡ የጀመርኩትን ስልታዊ አካሄድም ማበላሸት መስሎ ይሰማኛል፡፡ ብቻ በአዕምሮዬ "ይህ ነገር ማብቂያው የት ይሆን?" እያልኩ ፍፃሜው ይናፍቀኛል፡፡ በዚህ ሁሉ የሃሳብ እንግልት ሰንብቼ ለጥቂት ቀናት ብሎ ወደ እንግሊዝ ሄዶ የነበረው ሁመይድ ከ40 ቀናት በኋላ ተመልሶ መጣ፡፡ ከአንድ ሳምንት የእንግሊዝ ቆይታው በኋላ ወደ ዱባይ ጎራ ብሎ በፍጥነት እንደሚመለስ በስልክ የነገረኝ ቢሆንም እዚያ ከወር በላይ መቆየቱ ትንሽ ግርታ ፈጥሮብኝ ነበር፡፡ እርሱ ግን እዚያም በርካታ ሥራዎች ስለቆዩት እንደዘገየ ነገረኝ፡፡ 

ከዚህ ሰው ጋር ያለኝ ግንኙነት ወደሆነ ምዕራፍ እየተሸጋገረ እንደሆነ በውስጤ ይታወቀኛል፡፡ በየቀኑ ማለት በሚቻል መልኩ አብረን ሻይ መጠጣት፣ ምሳ መብላትና አንዳንድ ሥፍራዎች መታየት አዘወተርን፡፡ እኔም የዚህን ሰው ሁኔታ ለማጥናት አስቤ ራሴን በመጠኑ ለቀቅ አደረኩት፡፡ በጣም የሚደንቀው አባቴ ወደ ውጭ ወጣ ወጣ ማለቴ መረጃ እንደሚኖረው የታወቀ ቢሆንም ምንም ያለማለቱ ነው፡፡ ሁመይድ ለአባቴ "ከፈቀዱልኝ የመፍትሄው አካል እሆናለሁ" ሲል እንደነገረው የነገረኝና እርሱም "ከሰማችህ እባክህ ምከርልኝ" ያለውን ተግባራዊ እያደረገው መስሎት ይሆን? ብዬ አሰብኩ፡፡ "ድንቄም ምክር እቴ" ስል ሁኔታው ላይ ለመዘባበት ሞከርኩ፡፡ ያም ሆኖ ከዚህ ክልስ ሰው ጋር የጀመርኩት ወጣ ገባ የት እንደሚያደርሰኝ ለመገመት እየጣርኩ ነበር፡፡ ከእማማ አፀደ ጋር በሁኔታው ልንፀልይበትና ልናስብበት የወሰድነው ጊዜ በራሳችን ግምት የተጠናቀቀ ሲመስል ቁጭ ብለን አውርተናል፡፡ እማማ አፀደም "እንግዲህ ልጄ በምንችለው አቅም ፀልየናል፣ ለእያንዳንዱ ነገር የራዕይ ወይም የሕልም ምሪት መጠበቅ የእምነት መጉደል ምልክት ነው፡፡ ምናልባት ወደ ስህተት የመምራት ዕድልም ይኖረዋል፡፡ በሕሊናሽ የተለየ መላ ካልተከሰተልሽ በያዝሽው መንገድ ወስኖ መቀጠሉ ተመራጭ ነው፡፡ እኔም ቢሆን የመውጫው መንገድ ይኸው ብቻ ነው መስሎ የተሰማኝ፡፡ ደግሞ አይዞሽ...አነሰም በዛም በነገሩ ላይ ፀለይንበት አይደል እንዴ? ጸሎት ማለት ራስንና ነገሮችን ለእግዚአብሔር አደራ መስጠት ማለት ነው እኮ" ብለውኛል፡፡ ሁመይድ የገባልኝን የነፃነት ቃል በየጊዜው በብዙ እርግጠኝነት የሚደግመው ቢሆንም እንኳ በምስክር ፊት የሚያረጋግጥበትን አንድ የጋራ ሥልት ነደፍን፡፡ የእማማ አፀደ ሴት ልጅና የእኔም አብሮ አደግ የሆነችው ሄለንንም የስትራቴጂያችን አካል አደረግናት፡፡

ከሁመይድ ጋር ጊዜ ባሳለፍን ቁጥር እኔን በእጁ የማድረግ ፍላጎቱ ጣራ ነካ ማለቱ ይቀላል፡፡ የዘወትር ውትወታው እንድንጋባ ነው፡፡ ለሐጂም እኔ እሺ ሳልለው አንዳች ነገር እንደማይተነፍስ እየደጋገመ ይነግረኛል፡፡ ይህ አባባሉ ሁልጊዜ ትርጉም አልባ ቢሆንብኝም እንደ ዋዛ ግን እሰማው ነበር፡፡ ለተደጋጋሚው የጋብቻ ጥያቄው ከዚህ በፊት የነገርኩትን ወገብ የሚቆርጥ መልስ አሁን አልሰጠውም፡፡ ይልቁንም ለበርካታ ቀናት እሺም እምቢም ሳልል አብሬው እታይ ነበር፡፡ ወደ በኋላ ላይ "ወንዶች ስትባሉ ጠብ እርግፋችሁ የምትፈልጉትን በእጃችሁ እስክታስገቡ ድረስ ነው" እለው ጀመር፡፡ እንዲህ ስለው እሺ ለማለት ጫፍ የደረስኩ ነገር ግን በእርሱ ላይ እምነት የማጣቴ ነገር ትልቅ እንቅፋት የሆነ እየመሰለው ከብዙ መሃላ ጋር የቃል ኪዳን መዓት ይገባል፡፡ ከተደራረበብኝ ችግር በተጨማሪ በዋናነት ልቤን በከፊልም ቢሆን እንድከፍት ያደረገኝ እሰጥሻለሁ ያለኝ የሕሊና ነፃነት ነው፡፡ ይህንኑ ነገርም እያስረገጠ ይነግረኛል፡፡ ከዚህ በኋላ ከእማማ አፀደና ከሄለን ጋር በተነጋገርነው መሰረት ከጓደኛዬ ጋር ላስተዋውቅህ ብዬ አንድ እሑድ ረፋድ ቀጠርኩት፡፡ ይህን ማድረጌ ለእርሱ የድል አጥቢያ እንደሆነ ስለተሰማው ያለልክ ፈነጠዘ፡፡ ብሥራተ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ሬስቶራንት በረንዳ ላይ ከሄለን ጋር ጠበቅነው፡፡ እርሱም በሰዓቱ ሲከንፍ መጣና ተቀላቅሎን ቁርስ እየበላን ስንጫወት ቆየን፡፡ ለሄለን እየሳቅሁና ነገሩን ለማዛት እየጣርኩ "ይኸውልሽ ጓደኛዬ ይህ ሰውዬ ካላገባሁሽ እያለ መቆሚያ መቀመጫ ነስቶኛል" አልኳት፡፡ እርሷም እኛ ቤት ሲመላለስና እኔ ጸበል ሳለሁ በተደጋጋሚ እንዳስተዋለችው ነገረችው፡፡ እርሱም ብድግ ብሎ በአክብሮት እጇን ከጨበጠ በኋላ ተቀመጠና ስለ ራሱ አንዳንድ ነገር ማውራት ቀጠለ፡፡ በመሐል ላይ ሄለን ወደ ውጭ ስታይ ቆየችና "እናቴ...እናቴ ያቻትና" ይቅርታ በመጠየቅ ደረጃውን ተንደርድራ ወርዳ ሄደች፡፡ ዓይናችን እርሷን ሲከተል እማማ አፀደ ከሁለት ሴቶች ጋር ከቤተክርስቲያን እየተመለሱ ነበር፡፡ እኔም ከመቀመጫዬ እየተነሳሁ "እማማ አፀደ ናቸው፣ ታውቃቸዋለህ አይደል?... ያስታመሙኝ ሴቲዮ" አልኩት ለማስታወስ እንዲረዳው፡፡ "እህ...!" አለ አንገቱን በአዎንታ እየነቀነቀ፡፡ ወደርሳቸው መንገድ ስጀምር "ይዘሻቸው ነይ...ቁርስ ይብሉ" አለ፡፡ መንገዱ ዳር እንደቆሙ ተቀላቀልኳቸውና ጥቂት አውርተን እያመነቱና በግድ በሚመስል መልክ ከሰዎቹ ነጥለን ወሰድናቸው፡፡ ሁመይድ ብድግ ብሎ በአክብሮት ተቀበላቸው፡፡ በፍጥነትም ከበረንዳው ወደ ውስጠኛው ክፍል ገብተን ተቀመጥን፡፡

እማማ አፀደ ከተላበሱት ግርማ ሞገስ በተጨማሪ ጨዋታ አዋቂም ናቸው፡፡ በራሳቸው ለዛና ዘይቤም ስለ እምነታቸው ሲመሰክሩ በጣም ያስገርማሉ፡፡ እርሱ በደንብ እንደሚያውቃቸው ሁሉ ለመስተንግዶ ተሽቆጠቆጠ፡፡ የቀረበላቸውን ቁርስ እንደነገሩ ቀማምሰው ሲያበቁ ስለ እኔ ከልጅነት ጊዜ አንስተው  የነበረኝን ቁጥብነት፣ አሁን በቤታችን የተፈጠረውን ችግር ከወጣነትና ዘመኑ ከፈጠረው ተፅዕኖ ጋር እያያያዙ አወጉ፡፡ እግረ መንገድም ከልጃቸው ከሄለን የማይለዩኝ ልጃቸው እንደሆንኩ አፅንኦት ሰጥተው ተናገሩ፡፡ እኔም በመሐል ለእማማ አፀደ ሁመይድ ካልተጋባን ብሎ ወጥሮ እንደያዘኝ ነገርኳቸው፡፡ እርሳቸው በእኔ ሕይወት ውስጥ ጉልህ ተፅዕኖ ካላቸው ጥቂት ሰዎች አንዷ ናቸው፡፡ በብዙ ነገር የሚተማመኑባቸው፣ ለእያንዳንዱ ችግር የሆነ መላ የማያጡ ዓይነትም ናቸው፡፡ የሁመይድን ጥያቄ ከነገርኳቸው በኋላ "እናንተ ወጣቶቹ እኛ አሮጊቶች ምንም የማናውቅና የማናስተውል ይመስላችኋል እንጂ በጥቂት እይታና በትንሽ መረጃ ወደ እውነታ የሚጠጋ ድምዳሜ ሰጭዎች ነን፡፡ ነገር ግን ይህን ብስለት እኛ ዕድሜ ላይ ሳትደርሱ በፍፁም አታውቁትም" ብለው እንቅስቃሴያችን ወደዚያ እንደሚያመራ ጠርጥረው እንደነበር ነገሩን፡፡ አያይዘውም ፈጣሪ ሃሳባችንን እንዲባርክልን ደጋግመው መረቁን፡፡ ከምርቃታቸው በኋላ በዘዴና በለዘብታ ቃል ጥያቄ አነሱ፡፡ "እሺ...ለቁም ነገር መብቃት ትልቅ ፀጋና ክብር ነው፡፡ ሆኖም በምን መልክ ነው ያሰባችሁት?? ከቤተሰብ ጋርስ ተማክራችኋል? ይቺ ልጅ ያሳለፈችውን መከራና በቤቷ ያለውንም ችግር ታውቃለህ አይደል?? በምን መልኩ ነው ጉዳያችሁን ልትፈፅሙ ያሰባችሁት??" አሉት ሁመይድን በሚመረምር አይኖቻቸው እያስተዋሉት፡፡

ሁመይድ የእማማ አፀደን ጥያቄ ለመመለስ ተርበተበተ፡፡ አይኖቻቸውን ሽሽትም እንደ ዓይናፋር ልጃገረድ አንዴ ወደ ሰማይ አንዴ ወደ ምድር ዓይኖቹን አቅበዘበዘ፡፡ ነገረ ሥራው ብሽቅ አደረገኝና በጠረጴዛው ሥር እግሬን ሰድጄ በጫማዬ ቅልጥሙ ላይ አቀመስኩት፡፡ እንደመባነን አለና ተንተባተበ፡፡ ሄለን ሁኔታው አስገርሟት ሳቋ ሊያመልጣት ሲል በዘዴ ጎንበስ ብላ እግሯን በማሸት ፊቷን ለመደበቅ ሞከረች፡፡ የእርሷን ሁኔታ አይቼ እኔም ሳቅ አፈነኝና ፈገግ እያልኩ "ሁመይድ የእማማ አፀደ ጥያቄ አልገባህም መሰለኝ" አልኩት፡፡ "አይ... አዎ... ምንድነው? መጀመሪያ እኮ እርሷ ገና ፈቃደኛ መሆኗን አልነገረችኝም እማማ" አለ እጁን ወደ እኔ እየጠቆመ፡፡ ሁኔታው ክስ የሚያቀርብ ከመምሰሉም በላይ በጭንቀት ፈገግ ለማለት ሲሞክር የውሸት ፈገግታው ፊቱ ላይ ደስ የማይል ገጽታ ይፈጥራል፡፡ እማማ አፀደ የሁመይድ ጭንቀት ስለገባቸው በዕድሜና በሕይወት ልምድ ያካባቱትን ጥበብ ተጠቅመው የተፈጠረውን ደስ የማይል ድባብ በፍጥነት ቀየሩት፡፡ እሳቸው ወጣት እያሉ የነበረውን የትዳር አመሰራረት፣ የሽምግልና አላላክ፣ የእጮኛ አመራረጥ እየተረኩ፣ የገጠሟቸውን አስቂኝ ገጠመኞች እያወሩ በሳቅ አፈረሱን፡፡ ሁመይድ በሁኔታው ፍፁም ተለወጠና ዘና አለ፡፡ ከዚያ በኋላ ማንም ሳይኮረኩረው እኔ እሺ ብዬ ላግባው እንጂ የሚያደርግልኝን ነገር፣ የሚወስደኝን ቦታ፣ የሚሰጠኝን ሥጦታ፣ የሚጠብቅልኝን የሃይማኖትና የህሊና ነፃነት እየማለና እየተገዘተ በዝርዝር ተናገረ፡፡ እንዲያውም እማማ አፀደን "እርስዎ እናቴ ነዎት፣ ትልቅ ሰውም ነዎት፣ በእርስዎ ፊት ያልኩትን ሁሉ ልፈፅም ቃል እገባለሁ" እስከማለት ደረሰ፡፡ የዚያን ዕለት ፕሮግራም ባቀድነው መልክ ከተጠናቀቀ በኋላ ሁመይድ እየፈነጠዘ በቅርብ ርቀት ወደሚገኘው ሰፈራችን አድርሶን ሄደ፡፡ እማማ አፀደ ቤት ገብተን ከሄለን ጋር በአንዳንድ ሁኔታዎች ስንሳሳቅ ቆየንና በመሐል ላይ ሄለን "ባልሽ ደስ የሚል ሰው ነው፣ በተለይ እንደ ሕጻን ልጅ ሲያፍር ያዝናናል... ከዚሁ ጋር ግን የአይኖቹን መቅበዝበዝ ሲያዩት ሌባ ያስመስለዋል" ብላ ከት ብላ ሳቀች፡፡ እኔም "አንቺ ባሌን እንዴት ነው የምትናገሪው?" ብዬ ለሳቅ ባጎነበሰችበት ጀርባዋን ደለቅኳት፡፡ እርሷ ግን ይባስ በሳቅ መንከትከት ጀመረች፡፡ ንግግሯን የሰሙት እማማ አፀደም "አንቺ ሹል አፍ ምኑን ነው የምትቀባጥሪው?" ብለው ሲጠጓት እየሳቀች ሮጣ አመለጠች፡፡ እማማ አፀደ እያቀፉኝ "ልጄ ሁሉን ፈፃሚው መድኃኔዓለም ነው፡፡ ለምናልባቱም ግን በእኛ ፊት ቃሉን መስጠቱ ደግ ነው" ብለው በብዙ ምርቃት አሰናበቱኝ፡፡

ከዚያ ቀን ጀምሮ ሁመይድ እርሱን ለማግባት እንደተስማማሁና የእሺታ ቃሌን እንደሰጠሁት ቆጠረ፡፡ እውነት ለመናገር እኔም ቀጣዮቹን የአካሄድና የቅደም ተከተል ጉዳዮች ማሰብ ጀምሬያለሁ፡፡ ስለሆነም መጀመሪያ ለፋይሰል ቀጥሎም ለእናቴ ለመንገር ወሰንኩኝ፡፡ ከአሁን በኋላ የነብር ጅራት እንደያዝኩ ዓይነት ራሴን አሳምኜ ቁርጠኛና የውሳኔ ሰው ለመሆን ለራሴ ቃል ገባሁ፡፡ ፋይሰልን ከቤት ውጭ አንድ ካፌ ቁጭ አድርጌ ያለውን ሁኔታና የደረስኩበትን ውሳኔ ነገርኩት፡፡ ከፊት ለፊቴ ሆኖ ፀጥ ብሎ ሲሰማኝ ቆየና ምንም ሳይናገር ዝም አለ፡፡ "ወንድሜ አንድ ነገር አትለኝም እንዴ?" ብዬ ጠየኩት፡፡ በመስኮት ማዶ ማዶውን እያየ "ምን ልበልሽ? እኔ ያንቺን ውሳኔ አከብራለሁ፣ ደስተኛ እንድትሆኚ ብቻ ነው የምፈልገው" አለ፡፡ ገጽታው ላይና ዓይኖቹ ውስጥ ግን ግልፅ ቅሬታ ይነበብ ነበር፡፡ የተሸነፍኩ፣ የቤተሰቡን ሰላም ለመጠበቅና ከጥቃት ለመከላከል ስል ከአቋሜ የተንሸራተትኩ አድርጎ በማሰብ ያዘነልኝ ይመስላል፡፡ የወንድሜን አለኝታነትና አሁን ስለ እኔ ሲል ነፍሱን ማስጨነቁን አስቤ ድንገት ኤንባዬ ዝርግፍ አለብኝ፡፡ ማልቀሴን ሲመለከት አጠገቤ መጥቶ ሊያባብለኝ ብዙ ደከመ፡፡ እየደጋገመ "ደስተኛ እንድትሆኚ ብቻ ነው የምፈልገው" ይለኛል፡፡ የሚመለከቱን ሰዎች በአንዳች ነገር ያልተግባባን ፍቅረኛሞች እንጂ ወንድምና እህት አልመሰልናቸውም ነበር፡፡ ይህንኑ ነገር ለእናቴ ስነግራትም ተመሳሳይ ቅሬታ ተመልክቼ መደነቅ ጀመርሁ፡፡ ተስፋ በመቁረጥና አባቴን በማማረር ስሜት "እስቲ እንግዲህ አግቢላቸውና ይረፉት፣ ከዚያ ደግሞ በምን ሰበብ እንደሚነታረኩ እናያለን" አለች፡፡ ከሁሉ ያስገረመኝ ግን የሰዓዳ ነው፡፡ ግዴለሽ ከሚመስል ተፈጥሮዋና ለሁመይድ ካላት ቅርበት የተነሳ ዜናውን በደስታ ትቀበላዋለች ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ እያሳሳቅሁ "ሁመይድን እኮ ላገባው ነው" ስላት ዱብ ዕዳ የወረደባት ይመስል ክው ብላ ቀረች፡፡ ከመፍለቅለቅ ሙዷ ተስፈንጥራ ወጥታና ኮስተር ብላ "ምን..?" ብላ ስትጠይቀኝ በዕድሜዋ ላይ በአንድ ጊዜ 20 ዓመት ጨምራ ታየችኝ፡፡ "አንቺ ክርስቲያን አይደለሽ እንዴ? እንዴት ሙስሊም ታገቢያለሽ?"  አለችኝ፡፡ ረጋ ብዬና ደቂቃዎች ወስጄ ላስረዳት ብሞክር እንኳ በፍፁም ሊገባላት አልቻለም፡፡ "ያ ሁሉ ችግር ለዚሁ ነበር?" ብላ በሚታዘቡ የልጅነት ዓይኖቿ ስትመለከተኝ የምገባበት አሳጣችኝ፡፡ "እንጃ የምትዪው ነገር ምንም አልተዋጠልኝም" ብላ በተቀመጥኩበት ጥላኝ ሄደች፡፡

ክፍሌ ገብቼ መራራ ለቅሶ አለቀስኩ፡፡ ባሳየሁት ጽናትና በፈፀምኩት ተጋድሎ በቤተሰቤ ዘንድ አትርፌው የነበረውን ሞገስ በአንድ ጊዜ ያጣሁት መስሎ ተሰማኝ፡፡ "የእኔ እንባ መቼ ይሆን የሚያቆመው?" እያልኩ ስነፈርቅ አመሸሁ፡፡ የደረስኩበትን ውሳኔ እንደገና ለመመርመር እስክከጅል ድረስ ውስጤ ተነዋወጠ፡፡ ሌሊቱን እንቅልፍ አጥቼ አድሬ ነጋ አልነጋ በማለት በማለዳ እማማ አፀደ ጋር ሄድኩ፡፡ ቤተክርስቲያን መሄዳቸውን ስሰማ ደፍሬ ብሥራተ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሄድኩ፡፡ እዚያው ስፀልይ ቆይቼ ሲወጡ ተገናኘንና መጠለያ ውስጥ ብዙ ደቂቃ ተቀመጥን፡፡ ከቤተሰቦቼ ያገኘሁትን ምላሽና የፈጠረብኝን አሉታዊ ስሜት እያለቀስኩ ነገርኳቸው፡፡ ውሳኔዬ ልክ መሆኑን መጠራጠር ሁሉ መጀመሬንም አልደበኳቸውም፡፡ እርሳቸው ግን ከእንዲህ ያለ ውሳኔ ጀርባ የተለያዩ ተግዳሮቶች መኖራቸው የተለመደ መሆኑን እየጠቀሱ ጠንካራ መሆን እንዳለብኝ ነገሩኝ፡፡ "በእርግጥ የሰው ልጅ ባህሪ ጀግና ወዳድና አድናቂ ከመሆኑም በላይ ያ ጀግና ጥራቱም ጽናቱም እንዳይቀንስ በብርቱ የሚመኝ ነው፡፡ ነገር ግን የእርሱን ጽዋ ለመቅመስ የሚፈልግ በባትሪም ተፈልጎ አይገኝ፡፡ አሁን አንድ ጊዜ ወስነሽ ከአፍሽ የወጣ ነገር ሆኗል፣ ወደ ኋላ መመለስ ደግ አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ሁነኛ መፍትሄ ሳያመላክቱ ግፊ በርቺ ማለት ብቻውን የአንቺንም ሰብዐዊነት ግምት ውስጥ ያለመክተት ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ሁሉን ነገር ለመድኃኔዓለም ሰጥተናል፡፡ እርሱ እንደሚያበጀው በፍፁም ልብሽ እመኚ፡፡ ከብዙ ለቅሶ በኋላ ነው ሳቅና ደስታ የሚገኘው" ሲሉ መከሩኝ፡፡ እማማ አፀደ ሀኪሜ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ከእርሳቸው ጋር ከተነጋገርኩ በኋላ እንደገና ሁሉን ነገር ለጌታ ሰጥቼ ወደፊት ብቻ መሄድ እንዳለብኝ ይሰማኝ ጀመር፡፡

ሁመይድ እንደገና ለጥቂት ቀናት ከሀገር ወጥቶ ቆየና ተመልሶ መጣ፡፡ ያን ጊዜ "ኤፊ አሁን ነገሩን ለሐጂ ብነግራቸው ምን ይመስልሻል?" ሲል እየተለማመጠ ጠየቀኝ፡፡ እኔም በአጭሩ "ንገረው" አልኩት፡፡ ያልሰማ ይመስል "እ..." አለኝ፡፡ "ንገረው..ከዚያ የሚልህን ትነግረኛለህ" አልኩት፡፡ የእርካታ ስሜት እየተነበበበት "አመሰግናለሁ ኤፊ" አለኝ፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ እንደ ሕጻን ልጅ አኩርፎ መጣና "ሐጂ እርሷ ካላረጋገጠችልኝ አላምንህም...እርሷ እንሆነ እኔን ያለማሳፈር ሥራ የላትም፡፡ ሽማግሌ ተልኮ ሲያበቃ ደግማ ታዋርደኝ እንዴ?" አሉኝ አለና ተከዘ፡፡ "ችግር የለውም...ሄጄ አረጋግጥለታለሁ" አልኩና ብድግ አልኩ፡፡ "የት ልትሄጂ ነው?" አለኝ በተቀመጠበት አሻቅቦ እያየኝ፡፡ "እርሱ ቢሮ እሄዳለሁ" አልኩት፡፡ "ቆይ ላድርስሽ" ሲል "በፍፁም በታክሲ ነው የምሄደው" ብዬ አዋክቤው ወጣንና ኮንትራት ታክሲ ይዤ ሱማሌ ተራ አካባቢ ወደሚገኘው ቢሮው አመራሁ፡፡ በከፍተኛ እልህና ወኔ ተሞልቼ ወደ አንድ ዓይነት ግጥሚያ የምሄድ ዓይነት ስሜት እየ ቢሮው ያሉት ሰራተኞችን ከሞላ ጎደል ያውቁኛል፡፡ ስለሆነም በቀጥታ ቢሮው ገባሁና ፊት ለፊቱ ቆምኩ፡፡ መነጽሩን ሰክቶ ከሚያየው ፋይል ቀና ብሎ ሲያየኝ ዓይኑን ማመን አቃተው መሰል መነጽሩን አውልቆ በግርምት አስተዋለኝ፡፡

                         (ይቀጥላል)

     ---------- ማርያማዊት ገብረመድኅን ----------saramareyama.890@gmail.com

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የምዕራፍ አምስት(፭)የ46 የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ

✝በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡ አሜን! ↪️የምዕራፍ አምስት(፭) 46ኛ ዙር የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ⤵️ 1⃣ ቅዱስ ያሬድ ከመላዕክት የተማራቸው ሦስቱ የዜማ ዓይነቶች ምን ምን ናቸው?ሞገር...