2018 ጃንዋሪ 26, ዓርብ

አፊያ ሁሴን ክፍል 12

አፊያ ሁሴን ክፍል #12saramareyame.890@gmail.com

አፊያ ሁሴን (ክፍል ፲፪)

የጀመርኩት አዲስ ሕይወት ከእርግዝናዬ ጋር ተደማምሮ ነው መሰለኝ የሚፈራረቁብኝ ስሜቶች ቅጥ የለሽ ሆኑብኝ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ያለ ምክንያት ቁጭ ብዬ ስነፈርቅ እውላለሁ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በስልክም ሆነ በአካል ለሚያናግሩኝ ሰዎች ቅን መልስ መስጠት ይቸግረኛል፡፡ ከመሬት ተነስቶ ውስጤ ብስጭትጭት ይልብኛል፡፡ አንዳንዴ ሙሉ ቀን ተኝቼ ሌላ ጊዜ ደግሞ ራሴን በሥራ ጠምጄ እውላለሁ፡፡ በመኝታም ሆነ በሥራ ተወጥሬ የምውለው በውስጤ ከሚጮህብኝ አንዳች ነገር ለማምለጥ የማደርገው እንደሆነ ቆይቶ ነበር የተረዳሁት፡፡ ለእርግዝና ክትትል የሚጎበኘኝን ሀኪም ስለሚሰማኝ ስሜት ነግሬው ነበር፡፡ እርሱ ግን "ከእርግዝና ጋር ተያይዞ በውስጥሽ በሚፈጠር የሆርሞን ለውጥ የስሜት መለዋወጦች ይከሰታሉ፡፡ ነገሩ ተፈጥሮአዊ በመሆኑ መጨነቅ የለብሽም" አለኝ፡፡ በሰርጌ ሰሞንና በአውሮፓ ጉብኝቴ አዕምሮዬ ከመደነቅ የሚተርፍ ሌላ ስሜትን የሚያስተናግድበት ጊዜም ቦታም አልነበረውም፡፡ አሁን ግን የጋብቻው ትኩስነት በመጠኑ መብረድ ሲጀምር፣ ዙሪያዬን የሚያጅበኝ ሰው ሁሉ ወደየመደበኛው ኑሮው ሲመለስ፣ ሁመይድም ሥራ እያለ የተለመደ ውክቢያውን ሲቀጥል የብቸኝነት ስሜት እየከበበኝ መጣ፡፡ በእርግጥ የሚያነጋግረኝ ሰው አላጣም፣ በስልክም ከተለያዩ ሰዎች ጋር ማውራት እችላለሁ፡፡ ችግር የሆነብኝ እርካታ የሚባል ነገር ማጣቴ ነው፡፡ ቤቴ ውስጥ እጅግ ውድ፣ ዘመናዊና ምቹ በሆኑ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች ተከብቤ ነው የምውለው፡፡ ግቢው መሐል ደግሞ እስካሁን ያልተነዱ ሁለት የራሴ የምላቸው መኪኖች አሉ፡፡ ቁስና ምቾትን እንደ ሕይወት ግብ ለሚቆጥሩ ሰዎች የእኔን እርካታ ማጣትን ከቅብጠት እንደሚቆጥሩት አያጠራጥርም፡፡ ማንም ምንም ተሰማው እኔ ግን በውስጣዊ እኔነቴ እርካታ፣ እረፍትና ሰላም አጥቻለሁ፡፡

ሁመይድ ከሀገር እየወጣ አሥራ አምስት ቀንም፣ ሦሥት ሳምንትም አንዳንድ ጊዜ ወር ያህልም እየቆየ ይመጣል፡፡ እርሱ ሀገር ውስጥ በማይኖርበት ጊዜ እህቴ ሰዓዳ ወይም ፋይሰል እየመጡ እኔ ጋር ያድራሉ፡፡ እናቴም ቀን ቀን አዘውትራ ትመጣለች፡፡ አባቴ ግን ከሁለት ቀን በላይ ብቅ አላለም፡፡ እማማ አፀደና ልጃቸው ሄለን፣ አስቻለውና ኤርምያስ የተወሰነ ጊዜ ጎብኝተውኛል፡፡ በተለይ ሄለን አዲሱ ቤት የገባሁ ሰሞን ለሳምንታት ሙሉ ቀን አብራኝ እየዋለች ጓደኝነቷንና አለኝታነቷን አሳይታኛለች፡፡ እርግዝናዬ እየገፋ ሄዶ ሆዴ ማስታወቅ ሲጀምር ቤት የምውልበት ሰዓት እየበዛ መጣ፡፡ ባሌ ሁመይድ ደግሞ ወራቴ እየጨመረ ሲመጣ የእርሱም ወደ ውጭ መመላለስ እየጠነከረ፣ በላይ በላዩም እየሆነ፣ ሄዶ የሚቆይበትም ጊዜ እየሰፋ መጣ፡፡ አንዳንድ ጊዜ "ገና ከማግባቴ ማርገዝ አልነበረብኝም" ስል አስባለሁ፡፡ በእርግጥ "ቸኮልሽ" የሚሉኝም ነበሩ፡፡ ሌሎች ደግሞ "ካገቡ በኋላማ የምን መቆየት ነው? የትዳር ማጥበቂያና የቤት ማድመቂያው ልጅ ነው"  ይላሉ፡፡ ያም ሆኖ እኔ ምኑንም ሳላስብ የልጅ እናት ለመሆን መንገድ ላይ ነኝ፡፡ ከወለድኩ በኋላ ስለሚሆነው ነገር ለማሰብ እሞክርና በፍርሃት "መጀመሪያ እስቲ በሰላም ልገላገል" እልና እተወዋለሁ፡፡ ሃሳቤ ግን እኔ ልተወው ብል እንኳ በዋዛ የሚለቀኝ አልነበረምና በሃሳብ ባህር እዋጣለሁ፡፡ በእርግጥ የሚያሳስቡ በርካታ ነገሮች አሉብኝ፡፡ ትምህርት የመቀጠል ብርቱ ፍላጎትና የከረመ ዕቅድ አለኝ፡፡ አባቴ ዶክሜንቴን ነጥቆ በተንኮልና በማን አለብኝነት እንዳልማር በማድረጉ የትምህርት ፍላጎቴ ይበልጥ ጨምሯል፡፡ ጋብቻዬን ተከትሎ ዶክሜንቶቼን ከመለሰልኝ ሰነባብቷል፡፡ እናም ከወለድኩ በኋላ ስለምማረው ትምህርት አስባለሁ፡፡ ልጄን ማንን እንደሚመስልና እንዴትስ ተንከባክቤ እንደማሳድገውም አሰላስላለሁ፡፡ በሰላም የመገላገሌ ነገርም እንዲሁ ያሳስበኛል፡፡ ከሁሉ ይልቅ የሚያብሰለስለኝ ጉዳይ ግን ሁመይድን ያገባሁበት ዋንኛ ምክንያት የሆነው የህሊና ነፃነቴና እርሱን ተጠቅሜ አደርገዋለሁ ብዬ ያቀድኩት ነገር ነው፡፡

ሁመይድን ለማግባት ስወስን በዋናነት የታየኝ ነገር ከአባቴ መገላገልን ነው፡፡ ሳገባ ይብዛም ይነስም የተሻለ የኢኮኖሚ ነፃነት እንደሚኖረኝ ገምቻለሁ፡፡ ስለዚህም ዋንኛ መደራደሪያ ያደረኩት የህሊና ነፃነትን ነበር፡፡ በዚያ ላይ ያገባች ሴት በዕድሜ የበሰለች፣ ከእርሷ አልፎ ቤተሰቧን የማስተዳደር ሃላፊነት የሚጣልባት ስለሆነች ከወላጆች የሚደርስባት ጫና ይቀንሳል፡፡ የኢኮኖሚ ነፃነቴን በመጠኑም ቢሆን ለማስከበር ሁመይድ የናጠጠ ቱጃር መሆኑና ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌለው መሆኑ ጠቅሞኛል፡፡ ለእርሱ ቀላል ከመሆኑ በተጨማሪ በእኔና በቤተሰቦቼ ዘንድ ሞገስ ለማግኘት ሲል የምንኖርበትን ቤትም ሆነ የሰጠኝን መኪና በእኔ ስም ነበር የገዛቸው፡፡ እኔ ሙሉ ውክልና የሰጠሁት ወንድሜ ፋይሰል ነው ተዋውሎ የገዛው፡፡ እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም በውስጤ ሲብላላ የኖረውን ክርስትና በወግ ልማረውና ልቀበለው አቅጃለሁ፡፡ ጌታ ከፈቀደ ምናልባት ለሁመይድም እተርፍ ይሆናል፡፡ ይህ የእኔ ሃሳብ ይሁን እንጂ እንዲህም ሆኖ ጠንካራ ተግዳሮቶች መኖራቸው አይቀርም፡፡ ከሥጋቶቼ አንዱ ያው አባቴ አንዱ ነው፡፡ እርሱ ካመነበት አስተሳሰብ እንዳልወጣ ምንም ነገር ከማድረግ አይመለስም፡፡ በዚህ መንገድ አቋሙንም ጭካኔውንም ባለፉት ጊዜያት አሳይቶኛል፡፡ በዚያ ላይ እጀ ረጅምና የተፅዕኖው አድማስ የሰፋ ነው፡፡ ምንም እንኳ እኔም ከመጣብኝ ለምንም ነገር ግንባሬን የማላጥፍ ጽኑ መሆኔ ባይጠፋውም እንቅፋቶች ከመፍጠር ወደ ኋላ እንደማይል ግልፅ ነው፡፡ ሌላው አሳሳቢ ነገር ራሱ ሁመይድ ነው፡፡ እርሱ ገጽታው ሲታይ የዋህ፣ ፎልፏላና ቅን ቢመስልም በደንብ አውቀዋለሁ ማለት ግን አልችልም፡፡ ሌላው ቀርቶ ለሥራ ጉዳይ ወደ ውጭ ሄድኩ ሲለኝ አምኜ ከመሸኘት፣ እዚያም ሳለ ሲደውል ከማውራትና ሲመጣ ከመቀበል የዘለለ ዝርዝር ነገር አላውቅም፡፡ በተለያዩ ሀገሮች ልዩ ልዩ ሥራዎች እንዳሉት የታመነ በመሆኑ ለመጠራጠር ዕድል አይሰጥም፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋር ለእኔ ያለው ፍቅርን የእውነት የሚያስመስሉ በርካታ ሁኔታዎችም ይታዩበታል፡፡ ይሁን እንጂ ከጋብቻ በፊት ስላወራነው የሕሊናና የእምነት ነፃነት ላለፉት 6 ወራት አንስተን አናውቅም፡፡ ብዙውን ጊዜ ቤት የማሳልፍ ስለሆንኩ ይሁን ያልኩትን ነፃነት እያከበረልኝ ስለ እስላማዊ አለባበስ አንስቶብኝ አያውቅም፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን በማላውቀው ምክንያት መጪውን ጊዜ አስመልክቶ ሁመይድን ጭምር በጥርጣሬ ቀለበት ውስጥ እንዳውለው የሚሰማኝ ስሜት አለ፡፡

ስለዚህ ነገሮችን ከተለያየ ማዕዘን ሳያቸው ከሁሉ በፊት ልጄን መውለድ እንደሚኖርብኝ አመንኩ፡፡ ያን ሁሉ መሥዋዕትነት የከፈልኩበትን ነገር ያላግባብ እንደገፋሁትና እንዳዘገየሁት የሚወቅስ መንፈስ በውስጤ እየተመላለሰ እያወከኝ ቢሆንም በቅድሚያ መውለድ ይኖርብኛል እያልኩ ደጋግሜ ለራሴ ነገርኩት፡፡ እንዲህ ያለው ውሳኔ ፈተና ምናልባትም መከራ ሊከተለው ስለሚችል በጽናት ለመጋፈጥና  በአገባብ ለመጋደል የአካልና የአዕምሮ ጤንነት ላይ መሆን እንደሚያስፈልግ ተሰምቶኛል፡፡ ሆኖም አልፎ አልፎ በራሴ ማስተዋልና ብልሃት ለመመራት እየሞከርኩ እንዳለሁ በማሰብ እጨነቃለሁ፡፡ መልሼ ደግሞ ከየት ያገኘሁት ትምህርት እንደሆነ ባላውቅም "እግዚአብሔር ያለልክ ቸር በመሆኑ በራሱ ጊዜም በእኛ የጊዜ ሰሌዳም ገብቶ ለማዳን የሚሰራ አምላክ ነው" በማለት ራሴን አፅናናዋለሁ፡፡ እንዲህ ባለው የሕሊና ሙግት፣ በዚህ ዓይነት ውጫዊ ሁኔታ ተከብቤ ቀሪዎቹ ወራት ነጎዱና የመውለጃዬ ጊዜ ደረሰ፡፡ ከአሁን አሁን ምጥ ያጣድፈኛል እያልኩ በምጠባበቅበት ሰዓት ሚዜዬና ጓደኛዬ የሆነችው ሄለን ደወለችና "ሁመይድ ተመልሷል እንዴ?" ስትል ጠየቀችኝ፡፡ ግርም አለችኝና "ምን ሆነሻል? በሦሥት ቀኑ ነው እንዴ የሚመጣው? ናዝሬት የሄደ አስመሰልሽው እኮ፡፡ ይልቅ ለምን በፍጥነት አትመጪም?" አልኳት፡፡ በእኔ ቤት የጅል ጥያቄ መጠየቋ አናዶኛል፡፡ ለመውለድ በመቃረቤ እንደ ሚዜነቷና አብሮ አደግነቷ ሰሞኑን ሁሉ አጠገቤ ነበረች፡፡ ዛሬ ግን ብቅ ሳትል ከሰዓቱ ተጋመሰ፡፡ ሄለን አጠገቤ ስትሆን በጣም ደስ ይለኛል፡፡ የሆነ ሁነኛ ሰው ከጎኔ እንዳለ ይሰማኛል፡፡ ስለዚህም ዛሬ በመዘግየቷ ተነጫነጭኩባት፡፡ እህቴ ሰዓዳ ከእኔ ጋር ብትሆንም እንደ ልጅ ስለማያት ለጨዋታ እንጂ ለጭንቅ የምትሆን አይመስለኝም፡፡ ውስጤ መረጋጋት ሲያቅተው "እንደውም ለምን ብዬ ምጥ እስከሚጀምረኝ እዚህ እቆያለሁ?" አልኩና ክትትል ሳደርግበት የነበረ አንድ ልዩ የማዋለጃ ክሊኒክ ሄድኩ፡፡ እዚያም ምንም እንኳ ምጥ ባይጀምረኝም ጊዜዬ መድረሱን አይተው አልጋ ሰጡኝና ተኛሁ፡፡

እግዚአብሔር ይመስገን የበኩር ልጄን ምጥ ብዙም ሳይጠናብኝ በሰላም ተገላገልሁ፡፡ ዙሪያዬ በበርካታ ሰው ተሞልቶ በማየቴ እጅጉን ደስ አለኝ፡፡ መኝታዬ በአበባና በመልካም ምኞት መግለጫ ተሞልቷል፡፡ የሌለው ሰው ቢኖር የልጄ አባት ሁመይድ ብቻ ነው፡፡ አባቴ ሳይቀር አጠገቤ ነበር፡፡ ከአባቴ የሚወለዱት ወንድሞቼና እህቶቼ፣ ዘመዶቻችን፣ የሰፈራችን ሰዎች እየተመላለሱ ሲጠይቁኝ የሆነ የኩራት፣ ብቻዬን ያለመሆን ስሜትና ለማህበራዊ መስተጋብር ገዘፍ ያለ ዋጋ የመስጠት ሃሳብ ውስጤን ይሞላዋል፡፡ አንድ ተለቅ ያለ ጉድለት የሚታየው የሁመይድ አለመኖር ነው፡፡ የመጀመሪያ ልጁ ሲወለድ ባለማየቱ፣ አጠገቤ ባለመሆኑ፣ በጠያቂዎች ሊቀርብለት የሚገባን የ"እንኳን ደስ አለህ" ምርቃት አደግድጎ ያለመቀበሉ አሳዘነኝ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ነገሩ ያበሳጨኝ ጀመር፡፡ በተለይ ሰዎች "አባቱ የታለ? እንኳን ደስ አለህ እንበለው" ሲሉ ብሽቀቴ ይጨምራል፡፡ ሆኖም ይህን ነገሬን የተረዱ የቅርብ ሰዎቼ እንዲህ ያለው መገጣጠም የተለመደ እንደሆነና ብዙም ቦታ ልሰጠው እንደማይገባ ደጋግመው ስለወተወቱኝ ነገሩን ቀለል አድርጌ ለማየት ሞከርኩ፡፡ በወለድኩኝ በአራተኛ ቀኔ ሁመይድ ደወለና በተለመደ ጩኸቱና ሳቁ ታጅቦ ደስታውን ገለፀልኝ፡፡ አሁን ዱባይ እንዳለና ከጥቂት ቀን በኋላ በዚያው ወደ እንግሊዝ አቅንቶ እንደሚመለስ ነገረኝ፡፡ አጠገቤ የተኛውንና ከእርሱ የተወለደውን ጨቅላ ሕጻን ዝም ብዬ ሳስተውለው የፈጣሪ ሥራ ይደንቀኛል፡፡ እኔ ለዘጠኝ ወራት ያህል በሆዴ የተሸከምኩትን ይህን ሕጻን እንዲህ አሟልቶና ውብ አድርጎ መሥራት ምን ዓይነት ጥበብ ነው ብዬ እገረማለሁ፡፡ ክንዴ ስር ተወሽቆ በጸጥታ ሲተኛ፣ ጡት ፍለጋ ደረቴ ላይ ሲርመሰመስ፣ ጡቴን በአፉ ጎርሶ በዓይኖቹ ዓይን ዓይኔን ሲመለከት እንዴት አንጀቴን እንደሚያንሰፈስፈው ልነግርሽ አልችልም፡፡ በቃ ተፈጥሮ የራሷ እጅግ የረቀቀ የእናትና ልጅ መስተጋብር አላት፡፡ ወልደው ካላዩት በቀር በፍፁም ለመረዳት ይከብዳል፡፡ በቃ...ገና ከወልድኩ በጥቂት ቀናት ውስጥ "ወይ እናቴ ለካ እንዲህ በስስት ነው ያሳደግሽኝ" እያልኩ መደመም ጀምሬያለሁ፡፡

በአራስነት ጊዜዬ ቤቴ እንደደመቀ ሰነበተ፡፡ እናቴና ሰዓዳ ሙሉ በሙሉ እኔ ጋር ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ሄለንም አዳሯ እኔ ጋር ነው፡፡ ብዙ ጠያቂዎች ስለሚመላለሱ ቀኑ ሳይታወቀኝ ነጎደ፡፡ ሁመይድ እንደተለመደው በሦሥት ትላልቅ ሻንጣዎች ለእኔና ለሕጻኑ የልብስ መዓት አጭቆ መጣ፡፡ ገና ምኑንም ለማያውቀው ጨቅላ በየዓይነቱ አሻንጉሊትና መጫወቻ በመግዛት ቤቱን ሞላው፡፡ የፈጠረው ድባብ የሆነ ዓይነት ደስታ ፈጠረብኝ፡፡ ውጭ ሀገር እንደሚያየው ዓይነት እዚሁ እኛ ጋር የሚኖሩ የሕጻኑን ጤና የምትከታተል ነርስና የምትንከባከብ ሞግዚት ካልቀጠርኩ ብሎ ከእኔ ጋር ሙግት ገጠመ፡፡ እኔ ከአራስ ቤት እስክወጣ እናቴ አጠገቤ መኖሯንና ከዚያም በኋላ ቢሆን ልጄን ራሴ መንከባከብ እንደምፈልግ ለዚህም እንደማላንስ በመናገር ተከራከርኩ፡፡ ይሁን እንጂ ሸምጋዮች ልጁን የምትንከባከብ ሞግዚት እንድትቀጠር የነርሷ አስፈላጊነት ግን ብዙም እንዳልሆነ በማስረዳት ዳኙን፡፡ ለእኔም "ሕጻኑ ከፍ ሲል አንቺም ወጣ ወጣ ማለት ስትጀምሪ የግድ ጠባቂ ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ ካሁኑ ቢለምዳት የተሻለ ነው" አሉኝ፡፡ አያይዘውም "አይዞሽ...እናትነቱን እንደው አትቀማሽም፣ በጠረንሽ ነው የሚለይሽ" እያሉም ቀለዱብኝ፡፡ በዚህ የግርግር ወቅት አዲስ አበባ ያልነበረችው ሌላዋ ሚዜዬ ልዕልና ልትጠይቀኝ መጣች፡፡ ስንጫወት ቆይተን አመሻሽ ላይ ሁመይድ መጣ፡፡ ከልዕልና ጋር ረዥም ጊዜ ባለመገናኘታቸው ሞቅ ያለ ሰላምታ ተለዋወጡ፡፡ "ኤፊን ለመጠየቅ ትንሽ አርፍጃለሁ፣ አንተም እንኳን ደስ አለህ" ስትለው ትንሽ ራቅ ብዬ ካለሁበት እያስተዋልኳቸው ነበር፡፡ እርሱም "እንኳን አብሮ ደስ አለን..! ለማርፈዱ ግን ችግር የለም፡፡ እኔ ባልየው እንኳን አሁን በቅርብ ነው የመጣሁት" አለ፡፡ "እንዴ..!? ስትወልድም እዚህ አልነበርክም እንዴ?" አለች ልዕልና፡፡ ከሌላኛው ጥግ ያለችው ሄለን ልዕልናን በዓይኗ ስትገስፃት ተመለከትኳት፡፡ "ሄለንና ልዕልና ባሌ ላይ ሙድ እየያዙበት ነው እንዴ?" ስል አሰብኩና ይበልጥ ጆሮዬን እነርሱ ላይ ለማድረግ ሞከርኩ፡፡ ነገር ግን አጠገቤ ያሉት ሰዎች ሲያዋሩኝ ቀሪው የባሌና የጓደኞቼ የቃላት ልውውጥ አመለጠኝ፡፡

ሜሪዬ.. መቼም የልጄን ስም አወጣጥ በተመለከተ የነበረውን ውዝግብ ሳልነግርሽ ባልፍ ደግ አይሆንም፡፡ እኔ የልጄ ስም እስላማዊና አረባዊ ዘይቤ ያለው እንዲሆን አልፈለኩም፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስም መስጠትም መሰረታዊው ነገር ሳይነካ በዘርፍ ጉዳዮች ፀብ ማስነሳት መስሎ ታየኝ፡፡ ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ እየተመናመኑ ባሉ ኢትዮጵያዊ ስሞች የሚቆጭ አንድ ጽሑፍ አንብቤ ስለነበር የልጄ ስም ኢትዮጵያዊ ይዘት እንዲኖረው ወስኜ ነበር፡፡ ስለሆነም ለክትባት ክሊኒክ በሄድኩ ጊዜ የልጄን ስም "በረከት" ብዬ አስመዘገብኩ፡፡ ይህን ያልሰሙት ቤተሰቦቼ ስም በመምረጥ ተጠመዱ፡፡ ብዙዎቹ መሐመድ ይሁን አሉ፡፡ የቀሩት ሙስጠፋ፣ ሌሎች ደግሞ ካሊድ እንዲባል ተመኙ፡፡ ነስረዲን፣ ጀማል፣ ሀሰን፣ አብደላህ... መዓት ስም በአማራጭ ቀረበ፡፡ እኔን እንድመርጥ ሲጠይቁኝ ስም እንዳወጣሁለትና ክሊኒክ እንደተመዘገበ፣ የልደት ካርዱንም በአዲሱ ስም እንዲያዘጋጁት እንደላክሁ ነገርኳቸው፡፡ ማን ብዬ እንዳወጣሁለት ሲጠይቁኝ እጄ ላይ ሆኖ የሚቁለጨለጨውን ልጄን በጨዋታ መልክ ወደ ላይ እያነሳሁት "በረከት ብዬዋለሁ...በረከት ሁመይድ" አልኳቸው፡፡ ከተሰበሰቡት ብዙዎቹ ኩምሽሽ ሲሉ ያስታውቅባቸዋል፡፡ አባቴ ግን በእኔና በስም አውጭዎቹ መካከል የማቀራረብ ሥራ ለመስራት እየጣረ "ጥሩ ነው ይሄም ጥሩ ነው..ግን ሙባረክ ቢባል የበለጠ ውብ ይሆናል" አለ ወደ ሰዎቹም ወደ እኔም እያፈራረቀ ተመለከተ፡፡ አባቴን በሰዎች ፊት ለማክበር ስል ገልመጥ አድርጌ አይቼው ዝም አልኩ፡፡ አስተያየቴና ዝምታዬ አንዳች መልዕክት አስተላለፈለት መሰለኝ ጥቂት ግርግር ፈጥሮ ሹልክ አለ፡፡ ከአባቴ የቅርብ ሰዎች አንዱ እንደ ምክርም እንደ ልመናም በሚመስል ቃና "አፊያ ሐጂ ልክ ናቸው፣ ሙባረክ የአንቺንም የሁሉንሜ ፍላጎት ያሟላል" አለኝ፡፡ እኔም "ምነው..በረከት መጥፎ ስም ነው?" ስል ጠየኩት፡፡ "አይ...መጥፎ አይደለም፣ ይበልጥ ውብ ለማድረግ ብዬ ነው፡፡ እስላማዊ ይዘት ቢኖረው ደስ ይላል" አለኝ፡፡ ፈገግ አልኩና "ቀኑን ሙሉ 'ወበረካቱ' ስትሉ አይደል እንዴ የምትውሉት? ምኑ ነው ከእስላማዊ ይዘት የወጣው?" አልኩ፡፡ እርሱ ግን በዋዛ የሚተወኝ አልሆነም፡፡ ቀጠለና "ቁራን በወረደበት፣ ነቢያችን ጥሪ ባደረጉበት ቋንቋ ስም ሲወጣ ጥሩ ነው" አለ፡፡ እኔም "ተው ባክህ አታድክመኝ፣ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ በአፍ መፍቻ ቋንቋዬ የተዋበ ትርጉም ያለው ስም አውጥቻለሁ፡፡ ስነ ልቡናዬ በአረቦች ቅኝ ግዛት እንዲገዛ አልፈቅድም" ብዬው ዞሬ ከሌላ ሰው ጋር ማውራት ቀጠልኩ፡፡ በሁመይድ በኩል ጫና ፈጥረው ስሙን ሊያስቀይሩ ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀረ፡፡

ልጄ ስድስት ወር ከሞላው በኋላ አንድ ቀን ከሁመይድ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በኃይለኛው ተጨቃጨቅን፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የተለመደው እስላማዊ አለባበስ ነው፡፡ አንድ ምሽት ቤታችን ውስጥ አንድ ተለቅ ያለ ግብዣ ማድረግ እንደሚፈልግ ነገረኝ፡፡ እኔም በድግሱ ምንም ቅሬታ እንደሌለኝ ነግሬው የግብዣው ምክንያት ግን ምን እንደሆነ ጠየኩት፡፡ እርሱም "እውነት ለመናገር ምንም የተለየ ምክንያት የለኝም፡፡ ነገር ግን ከሰርጋችን ወዲህ በተለይ ደግሞ ቤታችን ውስጥ ግብዣ አዘጋጅተን አናውቅም፡፡ ዘመዶቻችን፣ ጓደኞቻችን፣ ሌሎችም እንግዶች የሚገኙበት ፕሮግራም ቢኖረን መልካም ነው፡፡ እንደ አባወራነቴ ቤቴ ውስጥ ወዳጆቼን ብጋብዝና ቆመን ብናስተናግድ በጣም ደስ ይለኛል" አለኝ፡፡ ሃሳቡ እኔንም ደስ አሰኘኝ፡፡ እንደ ቤተሰብ ሃላፊ ማሰቡንም መናገሩንም ወድጄለታለሁ፡፡ ወዲያው ግን የተሰማኝን በጎ ስሜት ሁሉ የገለበጠ ነገር ተከተለ፡፡ እጄን እየያዘና በዓይኑ እየተለማመጠኝ "ኤፊ ቆንጆ የእኔ ውድ..አንድ ነገር ልለምንሽ...እባክሽ እምቢ እንዳትዪኝ?" ብሎ ሁለቱንም እጆቼን በየተራ ይስም ጀመር፡፡ በጥርጣሬ እየተመለከትኩት "ምንድነው..?" አልኩት፡፡ አጥፍቶ በሚቀጣው አባቱ ፊት እንደቆመ ታዳጊ ልጅ መሬት መሬት እያየ ሲቅለሰለስ ቆየና "የዚያን ቀን ማለቴ የግብዣው ቀን በእስላማዊ ልብስ ተውበሽ ብትታዪ በጣም ደስ ይለኝ ነበር" አለኝ፡፡ ጠላትሽ ክው ይበልና ሜሪዬ እንዴት እንዳስደነገጠኝ አትጠይቂኝ፡፡ በድንጋጤ ከደረቅሁበት ሁኔታ ስወጣ ንዴት ከአጥንቴ ሥር እንደ አዲስ ምንጭ ሲፈልቅ ይሰማኝ ነበር፡፡ ነገሩን ሳስበው ድግስ ደግሶ እኔን በሂጃብና አባያ ቁጥጥር ሥር እንዳደረገኝ ለማሳየት የፈለገ መሰለኝ፡፡ ቀድሞውኑ ዋናው ነገር እኔን በእስላማዊ ልብስ ማሳየት እንጂ ድግሱ አልነበረም፡፡ ግብዣው ማጀቢያ ፕሮግራም ብቻ ነበር፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ይህ ሃሳብ ፈፅሞ የእርሱ እንዳልሆነ፣ የአባቴና የግብር አበሮቹ ዕቅድ ሊሆን እንደሚችል ማሰላሰል ያዝኩ፡፡ በውስጤ እንደ እሳት የሚነደውን ብሽቀት አምቄ ልመረምረው ፈለግሁ፡፡

"በጣም ይገርማል...ከመጋባታችን በፊት በዚህ ጉዳይ ተነጋግረን አልነበረ እንዴ? የገባኸውን ቃል ማጠፍህ ነው?" አልኩት የተሰማኝን ንዴት ለመደበቅ እየታገልኩ፡፡ "አይ አይ አይ...እንደዚያ አይደለም ኤፊ፣ እየለመንኩሽ ነው፡፡ ውሳኔው የአንቺ ነው፣ እኔ ልመና ነው ያቀረብኩት" አለ ሁለቱን መዳፎቹን በመዘርጋት የልመና ምልክት ለማሳየት እየሞከረ፡፡ በአንድ በኩል የሌሎች ሰዎች ምክርና ግፊት መሆኑን ሳስብ በሌላ በኩል ደግሞ "በእስላማዊ ልብስ ተውበሽ" የሚለው ንግግሩ እየታወሰኝ 'የራሱ ድብቅ አጀንዳ ይሆን እንዴ?' ስል ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ ይህን ነገር ማውጣጣት አለብኝ ብዬ ምርመራዬን ቀጠልኩ፡፡ "ይህን ሃሳብህን ባልቀበለውስ ድግሱና ግብዣው ይቀራል?" ስል ጠየኩ፡፡ ቀና ብሎ አይቶኝ ዝም አለኝ፡፡ እኔም "መልስልኝ እንጂ እየጠየኩህ እኮ ነው?" ብዬ ኮስተር አልኩ፡፡ እንደማመንታት አረገውና "አይ...ለምን ይቀራል?" አለ፡፡ በጣም እንደተከፋ ያስታውቃል፡፡ ከመጋባታችን በፊትም ሆነ በኋላ እንዲህ ዓይነት ቅሬታ አይቼበት አላውቅም፡፡ "ሁመይድ" ስል ጠራሁት፣ ከአንገቱ ቀና ብሎ አየኝ፡፡ አስተያየቱ "አቤት" ከማለት በላይ ነበር፡፡ "በዚህ ጉዳይ መነጋገር ይኖርብናል፣ እየጠየከኝ ያለኸው ከሕይወት መመሪያዬ ውጪ የሆነ ነገር ነው፡፡ በዚያ ላይ በሕሊና ነፃነቴ ላይ ላትገባ የገባኸው ቃል አለ፡፡ ለምንድነው ታዲያ እንዲህ ቅር የሚልህ?" ስል ጠየኩት፡፡ እርሱም በተለመደ የንግግር ዘዬው "ኤፊ..እኔ እያስገደድኩሽ ወይም እየተጫንኩሽ አይደለም፡፡ ቃሌንም እያጠፍኩ አይደለም፡፡ ልመና ነው ያቀረብኩት፡፡ እኔ ባልሽ ነኝ፣ የልጅሽ አባት ነኝ፡፡ አንቺ ባልሽውና በፈለግሽው መንገድ ነው የተጋባነው፡፡ እስካሁንም አንቺ የፈለግሽው ብቻ ነው እየሆነ ያለው፡፡ አንድ ትንሽ ነገር ብጠይቅሽ ይሄን ያህል..." ብሎ ጭንቅላቱን በትዝብት መልክ ነቀነቀ፡፡ ለምን እንደሆነ ባላውቅም አሳዘነኝ፡፡ ይህ ሰው ባሌ ነው ስል አሰብኩ፣ ከወላጅ አባቴ መሸሻ ይሆነኝ ዘንድ አምኜ የተጠጋሁት ሰው ነው፡፡ እውነት ለመናገር እስካሁንም አስቀይሞኝ አያውቅም፡፡ ምናልባት ግፊት እየተደረገበት ይሆን? በእኔስ ለመኩራት ወይም ለማፈር መንታ መንገድ ላይ እንዲቆም ሥልታዊ በሆነ ዘዴ እየተገደደ ይሆን? ይህን መሳዩን ነገር ሳወጣና ሳወርድ ቆየሁና ብድግ ብዬ እርሱ ያለበት ሶፋ ላይ በጎን እየተቀመጥኩና እጁን እየያዝኩ "እውነቱን ንገረኝ ሁመይድ..ይህ የአንተ ሃሳብ ነው? ንገረኝ፣ እያየኸኝ እውነቱን ንገረኝ?" አልኩት፡፡ ቀና ብሎ አይቶኝና ፈገግ ብሎ "የራሴ ሃሳብ ነው ኤፊ፡፡ ምነው ተልኮ ነው ብለሽ ተጠራጠርሽ እንዴ?" አለኝ፡፡ ለጥቂት ሰከንዶች አስተዋልኩትና "መልካም፡፡ አስቤ ውሳኔዬን አሳውቅሀለው" ብዬ የለቅሶ ድምፁን የሰማሁት ልጄ ጋር ተነስቼ ሄድኩ፡፡

ሁመይድ ባነሳው ሃሳብ ላይ ምን ዓይነት ውሳኔ ላይ እንደምደርስ ችግር ሆነብኝ፡፡ ነገሩን ከሁለቱም አቅጣጫ ለማጤን ሞከርኩ፡፡ ሂጃብና አባያ ላይ በማመፅ ከአባቴ ጋር ብዙ ነገር ተዳርሰናል፡፡ ቤተሰቤን ለበርካታ ጊዜያት ሰላም ነስቻለሁ፡፡ እኔም አባቴም በየፊናችን ለወራት ለከባድ ሕመም ተዳርገናል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ በአቋሜ እንደፀናሁ ዘልቄያለሁ፡፡ ባደረኩት ተጋድሎና ባሳየሁት ጽናት በብዙዎች ዘንድ ሞገስን ሳተርፍ የሚሰድቡኝና የሚረግሙኝም ነበሩ፡፡ ስለዚህም ይህን ጽናቴን መተውና ለሽንገላ መሸነፍ ትልቅ ክህደት መስሎ ታየኝ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ እኔ ያን ሁሉ ፈተና የተቀበልኩት ልቤን ላሳረፈው እምነትና ቃል እንጂ ለሂጃብና አባያ ብቻ አይደለም፡፡ እምነት አጠቃላይ ነገር ነው፣ ልብስ ደግሞ አንድና አነስተኛ መገለጫ ብቻ ነው፡፡ ምነው መካከለኛው ምስራቅ ያሉ ክርስቲያን እህቶች ሂጃብና አባያ ለብሰው ይውሉ የለ፣ የልብ እምነትና የሰውነት ጨርቅ የሚገጥሙበትም የማይገጥሙበትም ጊዜ ይኖራል ስል አሰብኩ፡፡ በዚያ ላይ ምንም ነገር ጠይቆኝ የማያውቀው ሁመይድን ማስቀየም ከባድና ለትዝብት የሚጥል መስሎ ተሰማኝ፡፡ እንዲህ ያለው ፈተና ውስጥ የከተተኝ ለምን እንደሆነ ወደፊት በደንብ ይጠየቃል አልኩና ሃሳቡን ለመቀበል ከጀለኝ፡፡ በሂጃብና አባያ የሚያዩኝ አባቴና አጋሮቹ ምን እንደሚሉ፣ እንዴትስ እንደሚፈነድቁ ታሰበኝ፡፡ በእነርሱ ሁኔታ ከመናደድ ይልቅ ፈገግ አልኩ፡፡ በውስጤ 'ሌላኛውንም መንገድ ማየት ደግ ነው' ብዬ ከመኝታዬ ተነሳሁ፡፡ ከቁርስ በኋላ ለመውጣት የሚዘገጃጀውን ሁመይድ "ሃሳብህን ተቀብያለሁ፣ ለዚያን ቀን በምትፈልገው አለባበስ እታይልሃለው፣ የግብዣውን ቀን በፍጥነት አሳውቀኝ" አልኩት፡፡ ያልጠበቀውን ነገር እንደሰማ የተደነቀው ሁመይድ ጥቂት ከተደናገረ በኋላ "አመሰግናለሁ ኤፊ" ብሎ ግንባሬን ስሞኝ ወጣ፡፡

                        (ይቀጥላል)

    -------- ማርያማዊት ገብረመድኅን --------

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የምዕራፍ አምስት(፭)የ46 የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ

✝በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡ አሜን! ↪️የምዕራፍ አምስት(፭) 46ኛ ዙር የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ⤵️ 1⃣ ቅዱስ ያሬድ ከመላዕክት የተማራቸው ሦስቱ የዜማ ዓይነቶች ምን ምን ናቸው?ሞገር...