2017 ዲሴምበር 15, ዓርብ

ውዳሴሃ ለእግዝትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘይትነበብ በዕለተ ቀዳሚት ሰንበት


 ቅዳሜ የሚጸለይ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ምስጋና።

፩. ንጽሕት ነሽ ብርህትም ነሽ።  ጌታን በመካከል እጅ የያዝሽው ሆይ በሁሉ የተቀደሽ ነሽ። ፍጥረት ሁሉ ቅድስት ሆይ ለምኝልም ብለው እየጮኹ ካንቺ ጋር ደስ ይላቸዋል።

፪. ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ። ባለሟልነትን አግኝተሻልና ደስ ይበልሽ። እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ። ግርማ ያለሽ ድንግል ሆይ ገናንነትሽን እናመሰግናለን እናደንቃለን። እንደ መልአኩ ገብርኤልም ምስጋና እናቀርብልሻለን የባሕርያችን መዳን በማህጸንሽ ፍሬ ተገኝቷልና። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፫. እንደ ሠርግ ቤት ጉድፍ የሌለብሽ ነሽ መንፈስ ቅዱስ አድሮብሻልና የልዑል ኃይልም ጸልሎሻልና። ማርያም ሆይ ለዘለዓለም የሚኖር መጥቶ ከኃጢያት ያዳነን የአብ ልጅ ቃልን በውነት ወለድሽ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፬ ከዳዊት ሥር የተገኘሽ ባሕርይ (ዘር) አንቺ ነሽ። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ ወልደሽልናልና። ከአብ የተወለደ ከዓለም በፊት የነበረ አንዱ ቃል ራሱን (ባሕርዩን) ሰወረ። ካንቺም የተገዥን (ሰውን) አርአያ ነሣ።ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፭. አምላክን ያለርኩሰት የወለድሽው ሆይ የምድር ሁለተኛ  ፀሐይ ካንቺ ወጥቶልናልና። እንደነቢያት  ትንቢትም ያለዘርና ያለመለወጥ ወለድሽው። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፮. ከተለዩ የተለየች የተባልሽ የኪዳን ጽላት ያለብሽ የተሰወረ መና ያለበት የወርቅ መሶብ ያለብሽ ደብተራ ድንኳን አንቺ ነሽ። ይኸውም መና የተባለው መጥቶ በድንግል ማርያም ያደረው የእግዚአብሔር ልጅ ነው። የአብ ቃል በርስዋ ሰው ሆነ መጥቶ ያዳነን የባሕርይ ንጉሥን በዓለም ውስጥ የወደችው የሚናገር በግ የክርስቶስ እናቱ ገነት ደስ ይላታል ለዘላለም የሚኖር የአብ ልጅ እርሱ መጥቶ ከኃጢአት አድኖናልና።ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፯. የንጉስ ክርስቶስ እናቱ ተባልሽ እርሱን ከወለድሽ በኋላም በድንግልና ኖርሽ። ድንቅ በሆነ ምሥጢር (ተዋህዶ) አማኑኤልን ወለድሽው ስለዚህም ባለመለወጥ አጸናሽ።ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፰ እግዚአብሔር በላይዋ ተቀምጦባት ያዕቆብ ያያት መሰላል አንቺ ነሽ። በሁሉ በኩል የማይመረመር እርሱን ተፈትሖ በሌለበት ማህፀንሽ ተሸክመሽዋልና። እኛን ስለማዳን ካንቺ ሰው በሆነ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ አማላጅ ሆንሽን።ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፱. የተባረክሽ ንጽህት የሆንሽ አዳራሽ ሆይ እንሆ ጌታ የፈጠረውን ዓለም ሁሉ በይቅርታው ብዛት ያድን ዘንድ ካንቺ ወጣ (ተወለደ) ፈጽመን እናመስግነው። ቸርና ሰውን ወዳጅ ነውና።ቅድስት ሆይ ለምኝልን።

፲. ያለርኩሰት ድንግል የሆንሽ ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ። የዓለም ሁሉ ምክበርያ ጽዋ  ነሽ። የማትጠፊ ፋና ነሽ የማትፈርሽ መቅደስ ነሽ። የቅዱሳን መደገፊያቸው (መጠጊያቸው) የማትለወጪ የሃይማኖት በትር ነሽ። ቸር አዳኛችን ወደ ሆነ ልጅሽ ለምኝልን ፈጽሞ ይቅር ይለን ይምረን ዘንድ ኃጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ።ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
አ           አ         ን
   ሜ         ሜ       ሜ
        ን          ን        ን
💙💚💖💞💓💙💜💖💞❤️saramareyama.890@gmail.com

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የምዕራፍ አምስት(፭)የ46 የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ

✝በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡ አሜን! ↪️የምዕራፍ አምስት(፭) 46ኛ ዙር የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ⤵️ 1⃣ ቅዱስ ያሬድ ከመላዕክት የተማራቸው ሦስቱ የዜማ ዓይነቶች ምን ምን ናቸው?ሞገር...