እሑድ 3 ዲሴምበር 2017

መንፈሳዊ ጥያቄና መልስ!!

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን፩

*ይህ በማህበረ ተዋህዶ ዘኦርቶዶክስ ጥያቄና መልስ ዝግጅት ክፍል እየተዘጋጀ የሚቀርብላችሁ ሳምንታዊ መረሃ ግብራችን ነው.እነሆ ማጠቃለያ መልስ*

ለሚከተሉት ጥያቄዎች ትክክለኛውን መልስ ስጡ

1⃣በደብተራ ኦሪት ታቦተ ፅዮንን እንዳገለግሉ የተመረጡት 2 ካህናት ስማቸው ማን ይባላል ? አባታቸውስ ማን ይባላል?   ከፈፀሟቸው በደሎች ሁለቱን ዋና ዋና በደሎች ጥቀሱ

*መልስ*አፍኒን እና ፊንሐስ. ናቸው. አባታቸው ካህኑ ኤሊ ነው

አፍኒን እና ፊንሐስ/ ፈቃደ እግዚአብሔርን ተላልፈው ሦስት ታላላቅ በደሎችን
ፈጸሙ፡፡ የመጀመሪያው በደል፤ በሙሴ ሥርዓት በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት በርታ
በቀዳማይ ሰዓተ መዓልት የምትጠፋ መብራት እንድትቀመጥ የተሠራ ሥርዓት
ነበር፡፡ ሆኖም አገልግሎት ከሌለ ሲበራ ማደሩ ለምን ? ብለው መቅረዙን አነሡ፤
መብራቱንም አጠፉ፡፡ ሁለተኛ፣ ለራሳቸው ሥጋዊ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥተው
ለመሥዋዕት እንዲሆን ከመጣው እንስሳ ታርዶ ስቡ ሳይጤስ፣ደሙ ሳይፈስ
ሥጋውን እየመረጡ ተመገቡ፡፡ሦስተኛ ጸሎት እናደርሳለን ሥርዓተ አምልኮ፣
እንፈጽማለን ብለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይመጡ ከነበሩት እስራኤላውያን
ቆነጃጅት ጋራ በዝሙት ወደቁ፡፡ አባታቸው ካህኑ ዔሊም የልጆቹን በደል እያየ
እንዳላየ እየሰማ እንዳልሰማ ቸል በማለቱ እግዚአብሔርአዘነ፡፡ በዚህም ምክንያት
ፍልስጥኤማውያንን አስነሥቶ በጦርነት ቀጣቸው፡፡
ዕብራውያን በጦርነት ውሎ ያለልማዳቸው በአሕዛብ ተሸነፉ፡፡ ሕዝበ እስራኤልም
ግራ ቢገባቸው «ድል የተነሣነው ታቦተ ጽዮንን ይዘን ባለመዝመታችን ነው»
ብለው አፍኒን እና ፊንሐስ ጽላቱን እንዲሸከሙ አድርገው ወደ ፍልስጥኤማውያን
የጦር ምሽግ ገሠገሡ፡፡ ሆኖም ያሰቡት ሳይሳካ ታቦተ ጽዮን ተማረከች፣ አፍኒንና
ፊንሐስ ሞቱ፤ ዕብራውያንም በጦርነቱ ድል ተደረጉ፡፡ፍልስጥኤማውያንም ታቦተ
ጽዮንን ማርከው ዳጎን ከተባለው ጣዖታቸው ላይ አስቀመጧት፡፡ በማግስቱ
ሲመለሱ ዳጎን ተገልብጦ ታቦተ ጽዮን በላይ ተቀምጣ አገኟት፡፡ በማግስቱም
ተመሳሳይ ድርጊት ተፈጽሞ ዳጎን ወድቆና ተሰባብሮ አገኙት፡፡ 1ሳሙ 5÷4 ይኽን
በተመለከተ ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጽጌ ድንግል ሰቆቃወ ድንግል በተባለው
ድርሰቱ፤
«ታቦተ አምላከ እስራኤል ጽዮን ዘነገደት ምድረ ኢሎፍሊ፤
ወቀጥቀጠቶ ለዳጎን ነፍሳተ ብዙኃን ማህጎሊ፤
አመ ነገደት ቁስቋመ በኀይለ ወልዳ ከሃሊ፤
ወድቁ አማልክተ ግብፅ መናብርተ ሰይጣን ሐባሊ፡፡
ወተኀጉሉ ኲሎሙ ዘቦሙ አስጋሊ. . .፤
ወደ ኢሎፍሊ ምድር ተማርካ የሔደች የእስራኤል አምላክ የቃል ኪዳኑ ታቦተ
ጽዮን የብዙዎችን ነፍሳት ያጠፋ ዳጎንን ሰባበረችው፡፡ ድንግል ማርያምም ሁሉን
ማድረግ ከሚችለው ከልጇ ጋር ግብፅ ወደሚባል ሀገር በሔደች ጊዜ የሐሰተኛ
ሰይጣን ዙፋኖች የሆኑ የግብፅ ጣዖታት ፈረሱ ጠንቋይ አስጠንቋይ ያላቸው ሁሉ
ዐፈሩ» በማለት በንጽጽር አስቀምጦታል፡፡ ኢሳ 19÷1 ኃይል እና ድል ማድረጉን
በዳጎን የጀመረችው ታቦተ ጽዮን የፍልስጥኤማውያንን መንደር በአባርና በቸነፈር
በእባጭም መታች፡፡ ሕዝበ ፍልስጥኤምም ታቦተ ጽዮን ወደ እስራኤል ምድር
እንድትመለስ አደረጉ፡፡
በእንደዚህ ዓይነት ታላቅ ክብር በሀገረ እስራኤል ትኖር የነበረችው ታቦተ ጽዮን
ወደ ሀገራችን ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷ ታላቅ የሆነ መንፈሳዊ ሐሴት እንዲሰማን
ያደርጋል፡፡

2⃣ሙሴ መቶ 20 አመት ዕድሜው በተፈፀመለት ጊዜ እግዚአብሔር ህዝቡን ለማን እንድሰጥ አዘዘው❓

  *መልስ*  ለነዌ ልጅ ለእያሱ

3⃣ባህረ ሐሳብን ማን ደረሰው❓

*መልስ*ባሕረ ሐሳብን ለማወቅ ብዙ አባቶች ተመኝተው ነበር። ይሁን እንጂ ሁሉ የሚሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና የመንበረ እስክንድርያ አስራ ሁለተኛ ሊቀ ጳጳስ ለነበረው ለቅዱስ ድሜጥሮስ ተጸልጾለታል። ድሜጥሮስ ማለት መስታወት ማለት ነው። መስታወት፦ በጥርስ ያለውን እድፍ በጸጉር ያለውን ጉድፍ እንደሚያሳይ ሁሉ ድሜጥሮስም የተሰወሩ በዓላትን እና አጽዋማትን አሳይቶናል፤ አንድም ድሜጥሮስ ማለት መነጽር ማለት ነው። መነጽር፦ የራቀውን አቅርቦ ፣የረቀቀውን አጉልቶ፣የተበተነውን ሰብስቦ እንደሚያሳየው ሁሉ ድሜጥሮስም የራቁ አዝማናትን አቅርቦ፣ የተበተኑ አጽዋማትን ሰብስቧልና
ድሜጥሮስ ባጭር ታጣቂ፣ እርፍ አራቂ፣ ዲኮ ታጣቂ፣ ነገር አዋቂ፣ ፍርድ ጠንቃቂ  መስተገብረ ምድር/ገበሬ/ ነበረ። በሞያው ምንም ዓይነት የቤተከርስቲያን ሞያ ያልነበረው ነገር ግን ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቆ የሚኖር ምዕመን ነበር። የድሜጥሮስ ኣባት ደማስቆ ወይም አስተራኒቆስ ይባል ነበር። ይህ የድሜጥሮስ አባት አርማስቆስ ወይም አስተራኒቆስ የሚባል ወንድም ነበረው። ይኖሩበት የነበረው ዘመን ዘመነ ሰማዕታት ስለነበረ ሁለቱ ወንድማማቾች ከሀገራቸው ተሰደው በባዕድ ሀገር ይኖሩ ነበር። በምድረ ዓላውያን ክርስቲያኖች ያነሱበት ዓላውያን የበዙበት ስለሆነ የድሜጥሮስ አጎት ከመሞቱ በፊት ሴት ልጁን  ለሌላ ለአሕዛብ እንዳይድርበት ለድሜጥሮስ አባት አምሎት ሞቶ ነበር። በኋላ ድሜጥሮስም ሆነ የአጎቱ ልጅ ስሟ ልዕልተ ወይን/የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የሚጠሩበት ስም ነው/ ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሔዋን ደርሰው ስለነበር ለሌላ ለአሕዛብ ድረናቸው ሕንፃ ሃይምኖት ከሚፈርስ ዘመዳሞችን አጋብተን ሕንፃ ስጋ /የዝምድና ግንኙነት/ ቢፈርስ ይሻላል በማለት ሁቱን አጋብተዋቸዋል። በጋብቻው ዕለት ስርዓተ መርዓት ወመራዊ ይፈጽሙ ብለው መጋረጃ ጥለውባቸው ሄደዋል። በዚህን ጊዜ ልዕልተ ወይን አምራ አለቀሰች። እንዲህም ብላ ጠየቀቸው፤ እኔን ንቀህ ነው? ወይስ ተዘምዿችንን? እንዴት አህትህ /የአጎትህ ልጅ/ ስሆን እኔን ታገባለህ? አለቸው። እርሱም እኔ አንቺንም ሆነ ተዘምዿችንን ንቄ አይደለም “አላ ከመ እፈጽም ፈቃደ አቡየ- ይልቁንም የአባቴን ፈቃድ ልፈጽም ብዬ ነው’ አላት። እንግዲያውስ ፈቃድሽ ከሆነ አንቺም ሴት እኔም ወንድ እንደሆንን በአዳማዊ ሩካቤ ሳንተዋወቅ መኖር እንችላለን። ለሌላም እንዳያጋቡን ባልን ሚስት መስለን በአንድ ላይ እንኑር አላት። እርሧም ደስ ብሏት ሀሳቡን ተቀበለች። ሁለቱም አንድ ምንጣፍ አንጥፈው፣ አንድ አንሶላ ተጋፈው እያደሩ በድንግልና አርባ ስምንት ዓመት ኑረዋል። ቅዱስ ሚካኤልም እንድ ክንፉን ለእርሱ አንድ ክንፉን ለእርስዋ እየጋረደ አድሮ በጠዋት በአምሳለ ርገብ በመስኮት ወጥቶ ሲሄድ ይታይ ነበር።
በዚህ ዘመን የመንበረ እስክንድርያ አሰራ አንደኛ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ዩልያኖስ ወይም ዩልዮስ የተባለው ዕድሜው ገፍቶ አርጅቶ ስለነበር ሕዝቡን ሰብስቦ ከእኔ በኋላ የሚሾመውን ሰው ምረጡ አላቸው። ሕዝቡም ‘’አባታችን እኛ ምን እናውቃለን? አንተ ሱባዔ ገብተህ ጸልየህ ንገረን እንጂ’’ አሉት እርሱም “እናንተም ጸልዩ እኔም እጸልያለሁ” አላቸው። በሶስተኛው ቀን መልአከ እግዚአብሔር ለሊቀ ጳጳሱ ተገልጾ ያለጊዜው ያፈራ የወይን ዘለላ እና የስንዴ ዛላ ይዞልህ የሚመጣው  ከአንተ ቀጥሎ የሚሾመው አርሱ ነውና  እርሱን ሹመው ብሎ ነገረው። በዚህም ዕለት ቅዱስ ድሜጥሮስ እርሻውን ሊያቃና ወደ አዝመራው ሲገባ ያለጊዜው ያፈራ የወይን ዘለላ እና የስንዴ ዛላ አገኘ፤ ወስዶም ‘ለሚስቱ’ ሰጣት። እርሷም “ይህንን እኛ ልንመገበው አይገባም ይልቁንም ወስደህ ለቤተ እግዚአብሔር ሰጥተህ ከሊቀጳጳሱ በረከት ተቀበል’’ ብላ ላከቸው። እርሱም ይዞ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ሲሄድ ሊቀ ጳጳሱም ሕዝቡን ሰብስቦ መልአኩ የነገረውን እየነገራቸው እያለ ድሜጥሮስ ገብቶ ስጦታውን ለሊቀ ጳጳሱ አበርክቶ ወጣ። ከወጣ በኋላ ሊቀ ጳጳሱ ለሕዝቡ ከእኔ ቀጥሎ የሚሾመው እርሱ ነው እሺ አይለችሁም ነገር ግን ግድ ብላችሁ አስቀምጡት ብሎ ነገራቸው።
ከጥቂት ቀናትም በኋላ ሊቀ ጳጳሱ አረፈ። ሕዝቡም መንበር  ባዶውን አያድርምና ድሜጥሮስን ተሾምልን ብለው ጠየቁት። እርሱም ደንግጦ “እኔ በአንድ በኩል ምንም ያልተማርኩ /ጨዋ/ ገበሬ ነኝ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ያገባሁ ሕጋዊ ነኝ እንዴት በንጹህ በማርቆስ ወንበር እቀመጣለሁ? አላቸው። እነርሱም አንተ እንደምትሾም አባታችን ነግሮናል! በማለት ግድ ብለው አስቀመጡት። ከዚህ በኋላ ድሜጥሮስ ሕዝቡን አባታችን ምን ምን ያስተምራችሁ ነበር? ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም አላውቅም ብትለን ነው እንጂ አባታችንማ አንቀጸ ኖሎትን አንቀጸ አባግዕን ተርጉም ያስተምረን ነበር አሉት። በዚህን ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍት/ብሉያትና ሐዲሳት ተገልጸውለት አንቀጸ ኖሎትን አንቀጸ አባግዕን  ተርጉሞ ለሕዝቡ አስተምሯቸዋል።

4⃣እግዚአብሔርን እንዴት ነው የምናፈቅረው❓እስኪ. እግዚአብሔርን እናፈቅራለን ስንል እንዴት ነው አብራሩልን ❓
*መልስ*ትዕዛዛቱን ሙሉ በሙሉ በመጠበቅ. ነው.
1 ዮሐ 4:8 "ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።"1 ዮሐ 4:8 የእግዚአብሔርን ፍቅር ሳናውቅ ስለፍቅር መናገር አስቸጋሪ ነው:: ያለ እግዚአብሔር እውነተኛ ፍቅር የለም:: እግዚአብሔር እንዴት እንደወደደን ሳናውቅ ስለፍቅር መናገር አንችልም:: 1 ዮሐ 4:10 እንዲህ ይላል:- "ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።" (1 ዮሐ 4:10) በእግዚአብሔር እንደተወደድክ ካላወቅህ ሌሎችን መውደድ አስቸጋሪ ነው:: ይሄ የኃይማኖተኞች ንግግር አይደለም:: ይህ እግዚአብሔር ልጁን ለኃጢያታችን አሳልፎ በመስጠት ለእኛ ራሱን ያሳየበት እውነትና ሃቅ ነው:: ስለዚህ ያለ እግዚአብሔር ፍቅሩ እግዚአብሔርን ማወቅ አንችልም:: ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ አለ:- "በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ
ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም  አይጠቅመኝም።" (1 ቆሮ 13:1-3)
"ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም"(1 ቆሮ 13:8)፤ ያለን ነገር በሙሉ ሊወድቅ ይችላል:: ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ፍቅርን መሰረት ያደረገ ነው፤ ይህም ባሕሪው ነው:: ፍቅር ከእግዚአብሔር የሚወጣ ነው:: የእኛም ባህሪ ሊሆን ይገባል::
ጌታ ኢየሱስ እንዲህ አለ:- "እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።" (ዮሐ 13:35) እውነተኛ ጋብቻም ሆነ ማንኛውም እውነተኛ ግንኙነት የሚታወቀው ፍቅር  በሆነ መሰረቱ ነው:: ምንም አይነት ነገር በመንገድ ላይ ቢመጣም መሰረቱ ፍቅር ከሆነ አይናወጥም:: እርግጠኛ መሆን የምትችለው ይህ ከሆነ ነው:: የይሁዳ መልእክት 1:21 እንዲህ ይላል:- "ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።" (ይሁዳ 1: 21) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- "ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ
ፈልጉ። ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ።" (1 ቆሮ 12:31) ፍቅር ከሁሉ የሚበልጥ ጸጋና መንገድ ነው:: የምትወዱትን
ሰው ይቅር ማለት አይከብድም:: 1 ጴጥ 4:8 እንዲህ ይላል:- ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። (1 ጴጥ 4:8)  "የምትወዳቸውን ሰዎች ኃጢያት አትቆጥርም:: መንፈስና ሕይወት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል የመንፈስን ፍሬ በእኛ ያበቅላል:: ፍቅር የመንፈስ ፍሬ ነው:: መንፈስ ቅዱስ ይወደናል::በውስጣችንም ለዘላለም መኖር የሚፈልገው ለዚህ ነው:: ማንም ሆነ ምንም ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም  ሮሜ 8:35 እንዲህ ይላል:- "ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን?" (ሮሜ 8:35) ፍቅር ከእግዚአብሔር ጋርያስተሳሰረን ገመድ
ነው:: እናም ሊበጠስ የማይችል ነው:: ጥላት ይህንን ገመድ መበጠስ አይችልም:: ለዚህ ነው ሌሎችን እንድንወድ የታዘዝነው:: ምክንያቱም በአማኞች መካከል እውነተኛ ፍቅር ካለ ጠላት ሊሰራ አይችልም:: ሌሎችን መውደድ ከባድ ከሆነብህ ሌሎችን እንደራስህ አድርገህ እንድትወድ የእግዚአብሔርን ፍቅር በልብህ እንዲያፈስ መንፈስ ቅዱስን  ጠይቅ:: ፍቅር የመንፈስ ፍሬ ነው::

 5⃣እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን እኔ ነኝ ብሎ የተናገረውን ሰባቱ ቃላት ምን ምን ናቸው❓ በየትኛው ምዕራፍና ቁጥርስ ይገኛል❓

*መልስ*-      እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ። ዘፍ ፲፭፣፩
-      እኔ ኤልሻዳይ ነኝ።. ዘፍ ፲፯፣፩
-      የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። ዘፍ ፵፮፣፫
-      ያለና የሚኖር እኔ ነኝ። ዘጸ ፫፣፲፬
-      እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ዘጸ ፮፣፫
-      ከግብጽ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ አኔ ነኝ። ዘጸ ፳፣፪
  እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝ።

በሐዲስ ኪዳንም ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ነኝ ብሏል

የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። ዮሐ ፮፣፴፭
እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ። ዮሐ ፰፣፲፪
  እኔ የበጎች በር ነኝ። ዮሐ ፲፣፯
መልካም እረኛ እኔ ነኝ። ዮሐ ፲፣፲፩
 ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ። ዮሐ ፲፩፣፳፭
   እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ። ዮሐ ፲፬፣፮
እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ። ዮሐ ፲፭፣፩
እኔ…..እንዲህ… ነኝ ብሎ የተናገረና መናገር የሚችል አምላክ ብቻ ነው። ምክንያቱም፡-
፩. የማይለወጥ /የማይወሰን ስለሆነ፡
እንዲህ / እዚህ ነበርኩ። እንዲያ / እዚያ እሆናለሁ… አይልም። ቦታ ጊዜ ሁኔታ አይገድበውም።
እግዚአብሔር አይለወጥም፡ አይወሰንም።
ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬም እስከለዘላለምም ያው ነው።… ዕብ ፲፫፣፰

፪. ሁሉ በእጁ / በእርሱ ስለሆነ፡
እግዚአብሔር ሁሉን ፈጥሮአል፣ ሁሉን ይመግባል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። ሮሜ ፲፩፣፴፮።
፫. ከእርሱ በላይ ማረጋገጫ ስለሌለ፡
አንድ ነገር. ነው አይደለም የሚል ልዩነት ቢፈጠር በሦስተኛ በበላይ አካል እንዲረጋገጥ ይደረጋል።
እግዚአብሔር ሌላ አስረጅ፣ ምስክር አያስፈልገውም። ከእርሱ በላይ የሚያረጋግጥ ስለሌለ።
፬. ነኝ ያለው የሆነውን ስለሆነ
ሁልጊዜ የነበረውን፣ የሆነውን፣ ወደፊትም የሚሆነውን ነኝ አለ።

6⃣አንድ ክርስቲያን ወደ እግዚአብሔር ቤት ለምን ይመጣል❓

*መልስ* በመጀመርያ ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ትርጉሞችን ያመለክታል። ቤተ ክርስቲያን ለአምልኮተ እግዚአብሔር ተሰብስበን ጸሎታችንና ምስጋናችንን ለእግዚአብሔር የምናቀርብበት ቦታ ማለት ነው። ለዚሁ ዓላማ የታቀደው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ወይም ቤተ እግዚአብሔር ይባላል። ይህም በድንጋይ፣ በብረት እና በእንጨት እንዲሁም በሌላ የቤት መስሪያ ቁሳቁስ ይታነጻል።
ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ለታነጸው ቦታ ደግሞ እግዚአብሔር የተለየ ግምት የሚሰጠው መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በአንደኛ መጽሐፈ ነገሥት እንዲህ ሲል ያስተምረናል።
“ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት፥ የንጉሡን ቤትና ሰሎሞን የወደደውን የልቡን አሳብ ሁሉ ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በገባዖን ለሰሎሞን እንደ ተገለጠለት ዳግመኛ ተገለጠለት። እግዚአብሔርም አለው። በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ።” 1ኛ ነገሥት 9፡1-3
እንግዲህ ንጉሥ ሰሎሞን ቤተ መቅደስን ሠርቶ በጨረሰ ጊዜ ለእግዚአብሔር ባቀረበው ጸሎት በቤተ መቅደስ ተገኝቶ የሚደረገው ጸሎት ሁሉ ተሰሚነት እንዲያገኝ ብሎ ለለመነው ልመና እግዚአብሔር መልስ እንደሰጠው ይህ ጥቅስ ያስገነዝበናል።
ሌላው ትርጉም ደግሞ ለአምልኮተ እግዚአብሔር የተሰበሰቡ ምእመናንን የሚያመለክት ነው። ይህን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ካህናት ምን እንዳላቸው እንመልከት።
“ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” የሐ. ሥራ 20፡28
ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር 122 ቁጥር 1 “ወደ ቤተ እግዚአብሔር እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ።” ይላል።
እናም እኛ ይህን የማያልፈውን የእግዚአብሔር ቃል መሠረት በማድረግ ዘወትር ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሄዳለን።
ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄዳችን ደስ ከሚያሰኙን ምክንያቶች አንዱ ፤ ከሥጋ ድካማችን የተነሳ የምንሠራው ሃጢአት የመንፈስ ጭንቀት ስለሚፈጥርብንና ለዚህም መድኅሃኒቱ የእግዚአብሔር እርዳታ ብቻ በመሆኑ ይህንኑ የእግዚአብሔር እርዳታ ለማግኘት ስንል ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሄዳለን። የሰላምን ጌታ ሰላሙን እንዲሰጠን ስንለምነው የሚያስፈልገንን ሁሉ የሚያውቅ ጌታ ልመናችንን ሰምቶ ፍላጎታችንን ሁሉ እንደሚያሟላልን ስለምናምን ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ሊያስደስተን ይገባል።
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በዐይን በሚታይና በጆሮ በሚሰማ የአምልኮተ እግዚአብሔር አገልግሎት አማካይነት በዐይን የማይታይና በእጅ የማይዳሰስ የእግዚአብሔርን ጸጋ ለመሳተፍ ስለምንበቃ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንሄድ ደስ ይለናል።
ሌላው ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄዳችን ሊያስደስተን የሚገባን እግዚአብሔር በቃሉ ሁለት ወይም ሦስት ሁነው በስሜ በሚሰበሰቡበት ቦታ እኔ በመካከላቸው እግኛለሁ ብሎ በማረጋገጡ ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት ማድረጋችን ነው።
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነን የምናቀርበው ጸሎት ተቀባይነትን እንዲያገኘ የአምላክ ፈቃዱ ስለሆነና እኛ ለምናቀርበው ጸሎት ሁሉ ከጌታችንና ከመድሃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መልስ እንደምናገኝ ስለምናምን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሄዳለን በመሄዳችንም ደስ ይለናል።

7⃣ቅዱስ ሉቃስ በቤተ ክርስቲያናችን. ዘላህም እየተባለ ለምን ይጠራል❓ዘርዝሩ

*መልስ* 1.ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በበረት: በላምና በአህያ መካከል መወለዱን በመጻፉ::

2.ጌታችንን "መግዝአ ላሕም - የሚታረድ ሜልገች (ላም)" ብሎ በመግለጹ:: እና

3.ከ4ቱ እንስሳ (ኪሩቤል) አንዱ (ገጸ ላሕም) ይራዳው: ይጠብቀውም ስለ ነበር ነው::

 8⃣ቅዱስ ሉቃስ ወንጌል መፃፍ የጀመረው ጌታ ባረገ በስንተኛው አመት ነው❓

*መልስ*ጌታ ባረገ በ22ኛው ዓመት ሲሆን ይኼውም በ56 ዓ.ም አካባቢ ማለት ነው:: ሲጽፍም ብቻውን አልነበረም:: ልክ ቅዱስ ማርቆስ ወንጌሉን የጻፈው ከሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ጋር እንደ ሆነው ሁሉ: ቅዱስ ሉቃስም የጻፈው ከብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ጋር ነው:: ምክንያቱም ለረዥም ዓመታት አብረው ለስብከተ ወንጌል ተጉዘዋልና::

9⃣ቅዱስ ሉቃስ ጌታን ከመከተሉ በፊት ስራው ምን ነበር❓

*መልስ* ዶክተር ነበር

🔟እግዚአብሔር ከመልከ ጼዴቅ ጋር ያደረገው ኪዳን ምንድነው❓

*መልስ* መልከ ጼድቅ የእግዚአብሔር ካህኑ የክርስቶስም ምሳሌው የሆነ የሳሌም ንጉስ ነው በ15 አመቱ መንኖ አጽመ አዳምን ይዞ በቀራንዮ በህብስትና በወይን. ያስታኩት ነበር. እግዚአብሔር ለመልከ ጼዴቅ በሐድስ ኪዳን ለምትሰራው ክህነትና ምስጢር ቁርባን ምሳሌ. አድርጎ በቃል ኪዳን አትሞታል በዚሕም ተሰውሮ ይኖራል እንጂ. ሞትን እስካሁን አልቀመሰም. ይህም ካሕኑ መልከ ጼዴቅ. ከአብርሃም ጋር በተገናኙበት  ጊዜ ተገልጧል.  ዘፍ 14፡17 እና ዕብ 7፡1

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
 ወለ ውላዲቱ ድንግል
 ወለ መስቀሉ ክቡር
 አሜን ይቆይን@sara mariyam

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የምዕራፍ አምስት(፭)የ46 የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ

✝በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡ አሜን! ↪️የምዕራፍ አምስት(፭) 46ኛ ዙር የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ⤵️ 1⃣ ቅዱስ ያሬድ ከመላዕክት የተማራቸው ሦስቱ የዜማ ዓይነቶች ምን ምን ናቸው?ሞገር...