2017 ዲሴምበር 8, ዓርብ

አፊያ ሁሴን (ክፍል ፰)

#አፊያ #ሁሴን ክፍል 8

#ማርያማዊት ገብረመድኃን

አፊያ ሁሴን (ክፍል ፰)

ወንድሜ መኪናውን በፀጥታ ሲያሽከረክር እኔ ደግሞ በከፊል ወደ እርሱ ዞሬ አተኩሬ ስመለከተው መሳቅ ጀመረ፡፡ ሳቁን ተከትዬ ስላልሳቅሁ ወይም ምንም ስላልተነፈስኩ ይልቁንም አሁንም ዝም ብዬ እንደማስተውለው ሲረዳ መኪናውን ጥግ ይዞ አቆመና ወደ እኔ እየዞረ "ምንድነው ኤፊ? አስጨነቅሽኝ እኮ" አለ፡፡ "ምንድነው?" አልኩት ኮስተር ብዬ፡፡ "ምኑ?" አለ እንዳልገባው ለመምሰል ጥረት እያደረገ፡፡ "ያልገባህ አትምሰል፣ እነዚህ ተከታትለው የገቡት መኪኖች ምንድናቸው? የአባቴ እንግዶች እንዴት በጠዋት መጡ? ዛሬ ያለ ልማድህ እንዴት በጠዋት ይዘኸኝ ወጣህ? እርሱስ እንዴት በቀላሉ ፈቀደ?" ብዬ በጥያቄ አጣደፍኩት፡፡ ነገሩን እንዳከረርኩት ከድምፄም ከገፄም ተረዳ መሰለኝ መሪውን እንደመደገፍ እያለ ተከዝ አለ፡፡ "ንገረኝ እንጂ ምን ይዘጋሃል?" ብዬ ጮህኩበት፡፡ ከዚያም "በቃ እኔ ወንድምም የለኝም ማለት ነው?" አልኩና ማልቀስ ጀመርኩ፡፡ በእርግጥም በጣም ተከፍቼ ነበር፡፡ ተደናገጠና አቅፎ ሊያባብለኝ ብዙ ጣረ፡፡ ባባበለኝ ቁጥር ሆድ እየባሰኝ ብዙ ቆየሁበት፡፡ በኋላ "ቆይ እነግርሻለሁ ኤፊ፣ እንባሽን ጥረጊ...አይዞሽ እኔ ወንድምሽ ነኝ" እያለ ተለማምጦ እንደምንም ዝም አሰኘኝ፡፡ ስልኩ ቀደም ብሎ ጀምሮ ደጋግሞ ሲጮህ ነበር፡፡ ስለሆነም "ቀጠሮው በጣም ረፈደብኝ፣ ብዙ አንቆይም፣ አንዳፍታ ሰዎቹን አነጋግሬ ቁርስ እየበላን ቁጭ ብለን እናወራለን" አለና ተነስተን ሄድን፡፡ በእርግጥም አራት ኪሎ የሚገኘው ማለዳ ካፌና ሬስቶራንት መናፈሻው ውስጥ አራት ሰዎች እየጠበቁት ነበር፡፡ ሰዎቹ ሁለቱ ሙስሊሞች መሆናቸው ከንግግራቸውና ከተደጋጋሚ መሃላቸው ያስታውቃል፡፡ ሁለቱ ደግሞ ክርስቲያን መሆናቸውን የአንገታቸው ማተብ ያስረዳል፡፡ በቢዝነስ ጉዳዮች ለ30 ደቂቃ ያህል አወሩ፡፡ እኔም ወሬው ላይ በጥቂቱ ተሳተፍኩ፡፡ ነገሩ ተጠናቆ ሲነሱ አንዱ ክርስቲያን ወንድሜን "ቆንጆ ሚስት አለችህ" ሲለው ጆሮዬ ጥልቅ አለ፡፡ ወንድሜ እየሳቀ "አፊያ..ታናሽ እህቴ ነች" አለው፡፡ የእኔ ከመቀመጫዬ ያለመነሳት እዚያ ቦታ እንድንቆይ መፈለጌን ወንድሜ ተገነዘበና ሰዎቹን ትንሽ እንደምንቆይ ነገሮ ሸኛቸው፡፡

ቁርስ በልተን እንዳጠናቀቅን ወንድሜ በቀጥታ ወደ ጉዳዩ ገባ፡፡ በውስጡ ሲያወጣ ሲያወርድ ቆይቶ ነገሩን ያለ ምንም ማንዛዛት ሊነግረኝ ወስኗል፡፡ ነገሩን ሳስተውለው አባቴ አልፎ አልፎ፣ ቀሪው ቤተሰቤ ደግሞ በብዛት ለእኔ የሚያሳዩት ሀዘኔታና የስስት ልጅ ዓይነት እንክብካቤ የሥጋ መዋለድ ከሚያሳድረው ተፅዕኖ በላይ ይሆንብኛል፡፡ "እንዲህ እንዲሆኑ አንዳች የሚያስገድዳቸው መንፈስ ይኖር ይሆን?" ስል አሰብኩ፡፡ ወዲያውም በዚያው ሃሳቤ "ምን ይሳነዋል የእኔ መድኃኔዓለም" አልኩ፡፡ አባባሌ የእማማ አፀደን አባባል አስታወሰኝና ሳላስበው ፈገግ አልኩ፡፡ ፈገግታዬን የተመለከተው ፋይሰል "ምንድነው የሚያስቀሽ ኤፊ?" አለኝ በፈገግታዬ እየተደሰተ "የልጁ ንግግር ገርሞኝ ነው..ሚስትህ መስዬው ነው?" ብዬ በፍጥነት ነገሩን አዞርኩት፡፡ ወዲያው መልሼ ወደ ቁዘማዬ ገባሁና የሚነግረኝን እንዲነግረኝ ተጠባበኩ፡፡ ወንድሜ እጆቼን በእጆቹ ያዘና "ኤፊ እነዚያ ያየሻቸው ሰዎች አንቺን ለትዳር ሊጠይቁ የመጡ ሽማግሌዎች ናቸው" አለኝ፡፡ ነገሩን ከግምት በላይ አውቄው ስለነበር ብዙም አልተገረምኩ፡፡ ከዚያ ይልቅ የእርሱን አለኝታነት መመርመር ፈለግሁ፡፡ እናም "አንተ መቼ ነው ያወቅኸው?" ስል ጠየኩት፡፡ "ከትናንት ወዲያ የጁምዐ ዕለት መስኪድ ስወስደው ነው የነገረኝ" አለና ቀጠለ "እሑድ እህትህን ለጋብቻ የሚጠይቁ ሽማግሌዎች ይመጣሉ፣ እርሷን በጠዋት ይዘሃት ትወጣለህ፡፡ ጠያቂው ኡመር ይባላል ብታየው ታውቀዋለህ፣ በእስልምናም ትምህርት በቀለሙም ትምህርት የገፋ እንዴት ያለ ልጅ መሰለህ፣ ከወጣት አሰጋጆች መካከል አንዱ ነው፡፡ ልጁስ ለዚህ መላ ለሚያሳጣት ነገር ደህና መድሃኒት ይሆናት ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው ይህች የተረገመች ልጅ በጄ የምትል ይመስልሃል? አለኝ" አለና ቀና ብሎ አየኝ፡፡ "እሺ..." በሚል አስተያየት አየሁት፡፡ እርሱም "እኔም የምትስማማ አይመስለኝም፣ ነገር ግን ጠያቂን ለምን ሽማግሌ ላክህ ማለት አይቻልም፡፡ ጥያቄያቸውን ሰምተህ እርሷን አነጋግሬ መልስ እሰጣለሁ ብለህ መሸኘት ነው" ስለው ምን እንዳለኝ ታውቂያለሽ?" አለ እየሳቀ፡፡ "ምን አለ?" አልኩት በጉጉት፡፡ ድምፁን የአባቴን ድምፅ ለማስመሰል ጎርነን አድርጎ "ጅሎ እርሱ ይጠፋኛል ብለህ ነው? አንተ ደግሞ ወደ ላይ ሽቅብ ልታስተምረኝ ትፈልጋለህ...እኔ የቸገረኝ ከዚያ በኋላ ምን እመልስላቸዋለሁ የሚለው ነው" አለ፡፡

በዚህ መንገድ ወንድሜ በከፊልም ቢሆን ከእኔ ጋር መሆኑን ከተገነዘብኩ በኋላ "አንተና አባትህ ናችኋ ተደራጅታችሁ ሽማግሌ ያስላካችሁብኝ?" ብዬ ቀልድ አዘል ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ እርሱም "ኤፊ ደግሞ ትገርሚኛለሽ...የአባታችንንም ስነ-ልቡና ተረጂ እንጂ፡፡ ለትዳር መጠየቅ ክብር ነው፣ ለምን ልጄን ጠየቃችሁኝ ማለት ይችላል?" ሲል መልሶ እኔኑ ጠየቀኝ፡፡ የእኔ ሥጋት ለእንዲህ ያለው ጥያቄ በምሰጠው አሉታዊ ምላሽ ከአባቴ ጋር የምፈራው ውዝግብ መልሶ እንዳይመጣ ነው፡፡ በእርግጥም ነገሩን በአባቴ በኩል ሆኜ ሳየው የሚቸግር ነገር እንደሆነ አልጠፋኝም፡፡ ከፋይሰል ጋር በእኔ የፀና አቋምና ከአባቴ ጋር ስለሚፈጠረው ችግር፣ አባቴ ሆስፒታል ሳለ ከእኔም ከእርሱም ጋር ስለተጣላው ሱሌይማን፣ ስለ ሁመይድ፣ ስለሌላም ሌላም ነገር ስናወራ ቆየን፡፡ ጊዜውን ለመግደል በሚመስል መልኩ የተለያየ ቦታ ስንዘዋወር በርካታ ሰዓታትን አሳለፍን፡፡ ወደ 8፡00 ሰዓት አካባቢ ከቤት ተደወለና እንግዶቹ ቀጠሮ ተሰጥቷቸውና ምሳ ተበልቶ መመለሳቸውን ለወንድሜ ተነግሮት ወደ ቤት አመራን፡፡ ቤት ስንደርስ የግቢው ውስጥ ድባብ እንግዶቹ ወደመጡበት የተመለሱ አይመስልም፡፡ ሁለት አጎቶቼ፣ ሌሎች ሁለት የአባቴ ጓደኞች፣ ታላቅ እህቴ ከእነ ባሏ፣ የእናቴ እህት የሆነች አንዲት ክርስቲያን አክስቴና አንድ የተከበሩ ሼኽ ቤት ውስጥ ነበሩ፡፡ እንግዲህ እነዚህ ለሽምግልናው ከእኛ ወገን ለመቆም የመጡ ነበሩ፡፡ ግቢው ውስጥ አነስተኛ ግርግር ስለነበር ከሰርቪስ ቤቶች ውስጥ አንዱ ክፍል ገብቼ ተቀመጥሁ፡፡ አንዷን ሰራተኛችንን ሰዓዳን እንድትጠራልኝ ነግሪያት ገና ከመቀመጤ ሳሎን ትፈለጊያለሽ የሚል መልዕክት መጣልኝ፡፡

ለምን እንደሆነ ባይገባኝም ፍርሃት በሁለመናዬ ተሰራጨ፡፡ መረጃ ከሰዓዳ ሳልጠይቅ በድንገት በመጠራቴ ተደናገጥኩ፡፡ ከመሄዴ በፊት ማን ማን እንዳለ ሰራተኛዋን ጠየኳት፡፡ "አጎቶችሽ አሉ...ሌላ ማንም የለ" ብላ እየተጣደፈች ሄደች፡፡ በጓሮ በወጥ ቤቱ በኩል አድርጌ ሰዓዳን በአይኔ እየቃኘሁ ወደ ዋናው ሳሎን አመራሁ፡፡ ፀጉሬ ላይ ሻርፕ ነገር ጣል አድርጌ በውስጤ "ጌታ ሆይ እርዳኝ...ጌታ ሆይ እርዳኝ" እያልኩ ለመግባት ሳመነታ እናቴ ከሳሎኑ ድንገት ብቅ ብላ "ውይ እቺው መጥታለች..ነይ ግቢ ነይ ግቢ" አለች፡፡ እኔ ኮሪደሩ ላይ ጥቂት እንድታዋራኝ ስፈልግ እርሷ ደግሞ ከተጠራሁ ትንሽ በመዘግየቴ ተጨንቃና የተቀመጡት አዋቂዎች ከብደዋት ልትጠራኝ መውጣቷ ነበር፡፡ ስለሆነም ያለ ድጋሚ ጥሪ በራሴ እንደመጣሁ ለማሳየት ፈልጋ ነበር በር ላይ ሆና "ይኸው መጥታለች..ነይ ግቢ" ስትል ድምጿን ከፍ አርጋ የተናገረችው፡፡ የእናቴን ሁኔታና ጥድፊያ በመቃወም ዓይነት በአይኔ ከገረመምኳት በኋላ ቀስ ብዬ በሩን አልፌ ገባሁና ቆምኩ፡፡ ነገረ ሥራዬ ሁሉ ተከስሼ በችሎት ፊት የቆምኩና በተከበሩ ዳኞች ፊት የምናገረው የጠፋብኝ ምስኪን አስመስሎኛል፡፡ ዝም ብዬ መገተሬን ያየው አባቴ "አጎቶችሽን ሰላም በያቸው እንጂ አፊያ.. እርሷም አክስትሽ ናት፣ ሼኽ ጅብሪልንና ሐጂ ሙሐመድንም ታውቂያቸዋለሽ" አለኝ፡፡ አስቀድሜ ሼኹ ጋር ሄጄ ጉልበታቸውን ሳምኩ፡፡ ሼኹ በዕድሜ ከሁሉ ከፍ ያሉ ከመሆናቸውም በላይ ጥቁር መነጽር የደነቀሩበት ዓይናቸውም እምብዛም አያይላቸውም፡፡ ጉልበታቸውን ስስም እጃቸውን ትከሻዬ ላይ አኑረው የምርቃት ናዳ አወረዱብኝ፡፡ ሁሉንም በየተራ ስስም እግሬ እየተወለካከፈ ስላስቸገረኝ "አይዞሽ..አይዞሽ" የሚሉ የማበረታቻ ድምፆች ከዚህም ከዚያም ይሰሙኝ ነበር፡፡ አክስቴን ስስማት ጥብቅ አርጋ እየያዘችኝ "አይዞሽ የእኔ ቆንጆ..ምንም አትፍሪ" ብላ ሞራል ሰጠችኝ፡፡ እህቴና ባሏን ሰላም ብዬ ስጨርስ ከአባቴና ከሼኹ ፊት ለፊት ባለው ሶፋ ላይ እንድቀመጥ ታዘዝኩ፡፡ ከተቀመጥኩ በኋላ ባለው ጥቂት አፍታ ክፍሉንና በውስጡ ያሉትን በስሱና በፍጥነት ቃኘኋቸው፡፡ ወንድሜ ከአንዱ ጥግ የሶፋ ኩርሲ ላይ ተቀምጦ መሬት መሬት እያየ በያዘው ስንጥር ምንጣፉ ላይ ይጭራል፡፡ እናቴ ለመታዘዝ እንዳደገደገ አገልጋይ መስላ ከሳሎኑ ወደ ኮሪደሩ በሚወስደው በር ላይ ቆማለች፡፡ እህቴ ከባሏ ጎን ተቀምጣ በሀዘኔታ የምታየኝ ትመስላለች፡፡ አክስቴ በዓይኖቿ ቆፍጠን እንድል ትጠቅሰኛለች፡፡ አባቴና ወንዶቹ አዋቂዎች የጀመሩትን ጨዋታ ቆም አረጉና ሼኹ መናገር ጀመሩ፡፡

ሼኹ ወደ አባቴ ጠጋ ብለው የሆነ ነገር ጠየቁት፣ የጠየቁት ስሜን ለመሆኑ ያስታውቅ ነበር፡፡ እናም "አፊያ...እንግዲህ እዚህ የጠራንሽ ሃሳብሽን ልንጠይቅሽ ነው፡፡ ሃሳብሽን ከአንቺ ለመስማት ያህል እንጂ ከእኛም ቃል ከአባትሽም ፈቃድ እንደማትወጪ እናውቃለን፡፡ ቀድሞውኑ አላህ በራሕመቱ የባረከሽ ነሽ፡፡ አሁንም አላህ (ሱባሀነ ወተዐላ) በምድር ዱንያውን በአኺራም ፈርዶውስ ጀነትን ይወፍቅሽ" አሉና ጉሮሮአቸውን አፅድተው ቀጠሉ "እና ልጄ...ዛሬ ለአንቺ ባል መጥቶልሻል" አሉና ስለ ባል ጥቅም፣ ሴት ዕድሜዋ ሲደርስ በፍጥነት ማግባት እንዳለባት፣ ባል አጥተው የተቀመጡ ብዙ ሴቶች እንዳሉና በትዳር ውስጥ ስለሚኖረው መልካም ነገር ሰፋ አርገው አብራሩ፡፡ የሼኹ የዕድሜ ባለፀግነት አይናቸውን ብቻ ሳይሆን ንግግራቸውንም እንደተጫነው ያስታውቃል፡፡ ከተናገሩት ከፊሉ ጭራሽ የማይሰማ ሲሆን የቀረውንም ለማድመጥ ጭንቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዕድሜም በማዕረግም ከፍ ያሉ ስለነበር ንግግራቸውን ለማቋረጥ የደፈረ አልነበረም፡፡ ከእርሳቸው ቀጥሎ ሁሉም በየተራ የሚሰማቸውን ከብዙ ምክርና ምርቃት ጋር ተናገሩ፡፡ አባቴ የጋብቻ ጥያቄ ያቀረበው ሰው በዕድሜ ወጣት በቀለሙም ሆነ በሃይማኖት ትምህርት የበሰለ መሆኑንና ባየው እንደማውቀው የተለያዩ ማስታወሻዎችን እየጠቀሰ ሊያስረዳኝ ደከመ፡፡ በመጨረሻ ከአባቴ ጓደኞች አንዱና ፈገግታ የሚያዘወትሩት አቶ ይመር ዳውድ ሳቅ እያሉ "አፊያ ታዲያ ሃሳብሽ ምንድነው? ከመጣሽ ጀምሮ መሬት መሬት እያየሽ ከመሬቱ ጋር ነው የምትጫወቺው" ብለው ሰዉን ሁሉ አሳቁት፡፡ ቀጠል አርገውም "ለጨዋታው ያህል ይህን አልኩ እንጂ አፈር ማለት፣ ቁጥብ መሆን፣ ቀደም ቀደም ያለማለት የጨዋ ሴት ምልክት ነው፡፡ አንቺም ላይ የምናየው ይህንኑ ነው፡፡ እንዲህ ያለች በሃይማኖትና በመልካም ስነ ምግባር ተኮትኩታ ያደገች ልጅ ደግሞ ለወላጆቿ ኩራት ለባሏም ሽልማት ነች፡፡ ለአንቺ ደግሞ ሽማግሌ ሆኖ መቀመጥ በእውነት ኩራት ነው...ታዲያ ጋብቻ በዋናነት የሚመለከተው አንቺን በመሆኑ እስቲ ሃሳብሽን ንገሪን...አይዞሽ አትፍሪ" አሉና በፊታቸው የተቀመጠውን የታሸገ ውኃ ጎንጨት አደረጉ፡፡ ሌሎቹም "በያ" "አይዞሽ" "ዝምታሽን ከመስማማት እንውሰደው?" እያሉ እንድናገር ገፋፉኝ፡፡

ዝም ብሎ ለሰማቸው ንግግራቸው ያለ ፍላጎት እሺ የሚያስብል ጫናና ኃይል አለው፡፡ በዕድሜና በደረጃ ከፍ ያሉና ለአንቱታ የበቁ እንዲህ ያሉ ሰዎች አንዲት ልጃገረድ ላይ ሲረባረቡ በእርግጥም የማሸነፍና በውድም በግድም የማሳመን ብቃት ይኖራቸዋል፡፡ ብዙ ወጣት ሙስሊም ሴቶች በደህናው ጊዜ ሲፎክሩ ቆይተው በኋላ ተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ የሚገቡት ለካ ወደው አይደለም ስል አሰብኩ፡፡ በዚያው ሃሳቤ "እኔ ግን አፊያ ነኝ" አልኩና ቀና አልኩ፡፡ ለጥቂት ሰከንዶች ሁሉንም በየተራ አየኋቸው፡፡ የእኔን ቀና ማለት የተመለከቱ ሁሉ አተኮሩብኝ፡፡ አባቴ ፊት ላይ ሥጋት መነበብ ሲጀምር ይታየኛል፡፡ ወንድሜ በጉጉት፣ እናቴ በጭንቀት፣ እህቴ በፍርሃት እያስተዋሉኝ ነበር፡፡ አክስቴ ቅንድቦቿን ፈታና ኮስተር እያደረገች የምልክት ማበረታቻዋን እየለገሰችኝ ነው፡፡ እኔ ከአንገቴ ቀና ባልኩ ጊዜ ፍርሃቴን የምመለክተው መሬት ላይ ትቼው ተነስቼ ነበር፡፡ የሆነ የመረጋጋት፣ የድፍረትና የጽናት መንፈስ በውስጤ ሲገባ ይታወቀኛል፡፡ ከመቀመጫዬ ብድግ ስል የሁሉም ትኩረት ጨመረ፡፡ ሆኖም ከዚያም ከዚህም አጣድፈው እንድቀመጥ አስገደዱኝ፡፡ ከዚያም ፈገግ እንዳልኩ "በእኔ ጉዳይ ተጨንቃችሁና ከአባቴም ጎን ለመቆም እዚህ በመገኘታችሁ በእውነት በጣም አመሰግናለሁ፣ ፈጣሪ ብድራችሁን ይክፈላችሁ" በማለት ብድግ ብዬ አመሰገንሁ፡፡ መልሼ ረጋ ብዬ ተቀመጥኩና "ምክራችሁንና ምርቃታችሁን አመስግኜ ተቀብያለሁ፣ ወገንነታችሁንም በልቤ ውስጥ አኖረዋለሁ፡፡ የጋብቻ ጥያቄውን ግን ለመቀበል አልችልም፡፡ ምክንያቱም እኔ አሁን በውስጤ ጋብቻ የመመስረት ፍላጎቱም ሆነ መነሳሳቱ የለኝም፡፡ ዋናው አላማዬ ያቋረጥኩትን ትምህርት ከዳር ማድረስ ነው፡፡ እናም ከትልቅ ይቅርታ ጋር በዚህ ነገር ባታስቸገሩኝ ደስ ይለኛል፡፡ ፈፅሞ የማልቀበለውና የማልደራደርበት ጉዳይ ነው" አልኩኝ፡፡ ለጥቂት ጊዜ ቤቱን አስፈሪ ጸጥታ ዋጠው፡፡ ሰዎቹ ንግግሬ የማያወላዳና አሳሪ መስሎ ሳይሰማቸው አልቀረም፡፡ ከዚያም አቶ ይመር ዳውድ ወደ አባቴ ጠጋ ብለው ዝቅ ባለ ድምፅ "የምን ትምህርት ነው? ያቋረጠችው ትምህርት አላት?" ሲሉ ጠየቁት፡፡ እርሱ ግን ግልፍ ብሎትና እየጮኸ "ምን ትምህርት ትምህርት ትላለች..የትም ስትንዘላዘል ወድቃ የተባረረችውን ትምህርት" አለ፡፡ ያ የተፈራው ፀብና ውዝግብ እንደገና ሊጀምር መሰለ፡፡ ሆኖም ሰዎቹ እየተረዳዱ አባቴን ማረጋጋትና "እንደርሱ እኮ አይደለም ሐጂ.." እያሉ ማረም ጀመሩ፡፡ ከተወሰነ ሁከት በኋላ ነገሮች ሰከን አሉ፡፡

አጎቴ ሰይድ የምንለው የአባቴ ታናሽ ወንድም ልመናም ማግባቢያም የሚመስል ቃና ባለው ንግግር "ልጄ ትምህርቱንም እኮ ቢሆን አግብተሽስ መማር ትቺያለሽ እኮ፣ ደግሞም ልጁ ወጣትና የተማረ ነው የትምህርትን ጥቅም ያውቀዋል፡፡ ሥንቶቹ ይኸው አግብተው አይደለም ወልደው እንኳ ይማሩ የለ እንዴ.. አባትሽንም አታበሳጪው፡፡ ያ ያለፈውን ክፉ ነገር እያወቅሽ" አለ፡፡ ሌላኛው አጎቴም በእርሱ ላይ እየጨመረ "ጋብቻ እኮ ክቡር ነው፣ የፈጣሪ ትዕዛዝ እኮ ነው፡፡ እንዲህ ያለ የተከበረ ሰውስ ለጋብቻ ጠይቆ በአሉታ መመለስ አግባብ ነው እንዴ? ፈፅሞ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው ለሴቶች ጋብቻ መጣሁ መጣሁ ሲል እንደሚያስፈራ ይታወቃል፡፡ ቢሆንም ጨክነው ሲገቡበት ነው የባል ፍቅር፣ የልጅ ደስታ፣ ራስን የመቻል ክብር የሚገኘው" አለ፡፡ ሁሉም የመሰለውን እየተናገረ ባለበት ሁኔታ ሼኽ ጅብሪል ሁሉ ዝም እንዲል በእጃቸውም በአፋቸውም ምልክት ከሰጡ በኋላ "ወገኖቼ እዚች ልጅ ልብ ውስጥ የሆነ ጥመት ያለ ይመስለኛል፡፡ አንቺ ከመቼ ወዲህ ነው ልጅ ከአባቷ ፈቃድና ምርጫ መውጣት የጀመረችው?" ሲሉ ተቆጡ፡፡ ከቁጣቸው የተነሳ መቀመጫው አልበቃቸው ያለ ይመስል ተቁነጠነጡ፡፡ "የአባት ክብር እንዲህ ነው እንዴ? አንቺ..! እንዴት ያለ ድፍረት ነው? እዚህ የተሰበሰብነውንስ ከቁም ነገር አልቆጠርሽንም ማለት ነው? በይ አሁን ተነሺና አባትሽንም ሁሉንም ይቅርታ ጠይቂ፡፡ ጥያቄውንም ተቀብያለሁ፣ አጥፍቻለሁ..ማሩኝ...በይ" አሉ፡፡ መመሪያቸው ላይ አንዳች ፊውዳላዊ ቅሪት ያለ ይመስላል፡፡ እኔም እንደ ኳስ ነጥሬ ድንገት ብድግ አልኩኝ፡፡ "ይቅርታ አርጉልኝ ሼኽ ጅብሪል፣ የምወድህ አባቴ፣ አጎቶቼ፣ ቤተሰቦቼ፣ እዚህ ያላችሁ ሁሉ በአይናችሁ ፊትና በእናንተ አስተያየት ጥፋት ሰርቼ አስቀይሜያችሁም ከሆነ ይቅርታ አድርጉልኝ" ብዬ ጎንበስ አልኩ፡፡ ቀጥዬም "የጋብቻውን ጥያቄ በተመለከተ ግን ሃሳብሽን ስጪን ብላችሁ የጠራችሁኝ እኮ እናንተው ናችሁ፡፡ የእኔ ሃሳብ፣ ምርጫና ፈቃድ ካላስፈለገ ለምን ጠራችሁኝ? እዚያው እናንተው መጨረስ ትችሉ አልነበር እንዴ?፡፡ ሃሳብሽን ንገሪን ብላችሁኝ ሃሳቤን ነግሬያችኋለው፡፡ ከዚህ ያለፈው ንግግር ግን እኔን ከማስገመት እናንተንም ከማናደድ የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በምታምኑት ፈጣሪ የምለምናችሁ ግን ይህን ውሳኔዬን ለአባቴ ካለኝ ውዴታ ጋር አታመዛዝኑት፡፡ ለአባቴ ያለኝን ፍቅር እርሱ ያውቀዋል፣ ቤተሰቦቼ ያውቁታል፣ የሦሥተኛ ወገን ምክርም ግሳፄም አያሻኝም፡፡ ትዳር ሕይወት ነው፣ የምኖረውም እኔ ነኝ፡፡ ለማንም ሰው የዕለት ወይም የሰሞን ብስጭት ብዬ ዕድሜ ልክ የሚያንገበግበኝን ውሳኔ አልወስንም" ብዬ ተቀመጥሁ፡፡

አባቴ ብድግ ብሎ በያዘው ከዘራ አናቴን ሊተረትረው ቃጣ፡፡ ነገር ግን ተረባርበው ያዙትና አስቀመጡት፡፡ ቤቱ በቅጽበት ተተረማመሰ፡፡ አባቴ ውስጡ መናደድ ሲጀምር የአሉታ የሚመስሉ ቃሎችን ብቻ እየመረጠ የሚሰማ ጆሮ ነው ያለው፡፡ እናም "ለእርሷ ክብር የመጡ ሰዎችን ታንጓጥጣለች እንዴ? ይቺ ወፍ ዘራሽ፣ ይቺ ከእኔ ሽንት ለመውጣቷም እጠራጠራለሁ፡፡ አያገባችሁም አትናገሩኝ ስትል እየሰማችኋት" እያለ ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል፡፡ እኔ ተስፈንጥሬ ሄጄ ወደ ውስጥ በሚወስደው በር ላይ በእናቴና በአክስቴ ተከልዬ ቆሜያለሁ፡፡ የአብዛኞቹ ትኩረት አባቴ ያለ ልክ ሲናደድ ደም ግፊቱ እንዳይነሳ በመስጋት እርሱን በማረጋጋት ተጠምዷል፡፡ ፋይሰል በውስጥ በኩል መጥቶ "በቃ ወደ ውስጥ ግቢ" እያለ ይጎተጉተኛል፡፡ የአባቴ ጓደኞች እርስ በርስ "እንዴት እንዴት ነው የምትናገረው? ጋዜጠኝነት ነበር እንዴ ታጠና የነበረው?" ይላሉ፡፡ አባቴም "ትምህርት ብላ ባህር ዳር ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ከርማ ነው የመጣችው፡፡ እዚያ ውሎዋም አዳሯም ከክርስቲያኖች ጋር ነበር፡፡ እነርሱ ናቸው እንደዚህ ክፉና ምላጭ አድርገው የላኳት" ይላል፡፡ ከብዙ ሽብርና ግርግር በኋላ ሼኽ ጅብሪል ተነስተው በሁኔታው እንዳዘኑ፣ እንዲህ ያለም ሽምግልና ገጥሟቸው እንደማያውቅ፣ እኔንም የወጣትነት ትዕቢትና ጠማማ የካፊር ሃሳብ ወደ ጥመት እየመራኝ እንደሆነ ገለፃ ሲያደርጉ ቆዩ፡፡ እኔን አክስቴ፣ እህቴና ፋይሰል እየገፋፉ ወደ መኝታ ክፍሌ ይዘውኝ ገቡ፡፡ ሼኽ ጅብሪል "እንግዲህ ልጅቷ በጄ አልልም ብላለች፣ ሌላ የምታሸንፉበት መንገድ ካላችሁ እናንተ ምከሩ፣ ቀስ ብሎ በእናቲቱ፣ በእህቶቿ በኩል ሃሳቧን ትለውጥ እንደው ሞክሩ፡፡ ካልሆነ የቀጠሮው ቀን ተገኝተን እንዳልተሳካ ለሽማግሎቹ መንገር ነው" አሉ እጃቸውን "መላም የለው" በሚል አኳኋን እያወናጨፉ፡፡ የዕለቱ ሽምግልናም በዚሁ ተጠናቀቀና ሁሉም ወደየመጡበት ተመለሱ፡፡

እኔ ግን መኝታ ክፍሌ ገብቼ እየጮህኩ ማልቀስ ጀመርኩ፡፡ በእርግጥም እጅግ በጣም ተከፍቼ ነበር፡፡ አባቴ እኔ ከእርሱ ለመወለዴ እንደሚጠራጠር በአደባባይና ሰው በተሰበሰበበት ተናግሯል፡፡ ሁልጊዜም ለቤቱ መታወክና ለእርሱ ጤንነት መቃወስ ተጠያቂ የመሆኔ ነገር አንገሽግሾኛል፡፡ ማንም ሰው የገዛ ክብሩና የአባቴ ጤንነት እንጂ የእኔ ሕይወትና ዕጣ ፈንታ እንደማያሳስበው ተሰምቶኛል፡፡ ስለዚህም ከዚያ ቤትና ቤተሰብ የቀረኝ ነገር የለም፣ የዝምድና ገመዴም ተቆርጧል እያልኩ በማሰብ መንሰቅሰቄን አበዛሁ፡፡ ቤቱን ጥዬ እንደምሄድ አሊያም ራሴን እንደማጠፋ እየዛትኩ በመናገር ከፍተኛ ግርግር አስነሳሁ፡፡ እናቴ እኔን ተከትላ ማልቀስ ጀመረች፣ ታላቅ እህቴ፣ አክስቴ፣ ሰዎቹን ሸኝቶ የተመለሰው ፋይሰል፣ ቤቱ ውስጥ ያሉት ሁሉ እኔን ለማባበል መከራቸውን ሲያዩ ቆዩ፡፡ አክስቴ እንዲህ አይነት ሽምግልና አይታ እንደማታውቅና ከልጅቷ ፍላጎት ውጪ በወላጅ ፈቃድ ካልተዳረች ማለት ያረጀና ያፈጀ ሥርዓት እንደሆነ እየተማረረች ትናገር ነበር፡፡ ታናሽ እህቴ ሰዓዳና ትንሹ ወንድሜ ሙኒር ከአንዲት ዘመዳችን ጋር ማምሻውን ሲመጡ እኔ እዬዬውን እያስነካሁት ነበር፡፡ ሰዓዳ የደረሳት መረጃ እኔ ከአባቴ ጋር ተጣልቼ ቤቱን ለቅቄ ካልሄድኩ እያልኩ በማስቸገር ላይ እንደሆንኩ ነበር፡፡ ስትበር እንደመጣች ከእኔ ብሳ እዬዬዋን ታቀልጠው ጀመር፡፡ ወገቤን ይዛ "እህቴ አትሂጂብኝ፣ እኔም አብሬሽ እሄዳለሁ" እያለች ለግልግል አስቸገረች፡፡ ሁኔታውን አልፎ ሳስበው እንደ መሳቅም ይቃጣኛል፡፡ አባቴ ከእንግዶቹ ጋር እንደወጣ ሳይመለስ ቀረ እንጂ ምሽቱ ምን እንደሚመስል ለመገመት ይከብድ ነበር፡፡ ብቻ ቆራጥ ውሳኔዬ፣ በሽማግሌዎች ፊት ያደረግሁት ንግግርና የለቅሶዬ ብዛት በቀሩት ዘንድ ተጨማሪ ሞገስ ያተረፈልኝ መሰለ፡፡ በአባቴ ላይ ግን ከፍተኛ ቂም ያዝኩበት፡፡ ልጅነቴን እስከ መካድ ያደረሰው ነገር ፈፅሞ ከሆዴ ሊወጣልኝ አልቻለም፡፡ በዚህ ሁኔታ ሳለ አንዷ ሰራተኛችን ብቅ ብላ "አፊያ ሁመይድ መጥቷል ሳሎን ነው" አለችን፡፡

                        (ይቀጥላል)

     ------- ማርያማዊት ገብረመድኅን -------

saramareyama.890@gmail.com

1 አስተያየት:

የምዕራፍ አምስት(፭)የ46 የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ

✝በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡ አሜን! ↪️የምዕራፍ አምስት(፭) 46ኛ ዙር የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ⤵️ 1⃣ ቅዱስ ያሬድ ከመላዕክት የተማራቸው ሦስቱ የዜማ ዓይነቶች ምን ምን ናቸው?ሞገር...