ዓርብ 8 ዲሴምበር 2017

አፊያ ሁሴን (ክፍል ፬)

#አፊያ #ሁሴን ክፍል 4

#ፀሀፊ ማርያማዊት ገብረ መድኅን

አንባቢ #ገብረ ሚካኤል

አፊያ ሁሴን (ክፍል ፬)

ቤተሰቦቼ መዳኔ ሳያስገርማቸው አልቀረም፡፡ ያን ሰሞን በጥንቃቄና በጥርጣሬ ነበር የሚከታተሉኝ፡፡ ነገር ግን የሚያውቁት እርጋታዬ ከብዙ ትሕትና ጋር መመለሱን ሲያስተውሉ ልባቸው እየተረጋጋ መጣ፡፡ አባቴ ዓይኑን ከአይኖቼ እንደሚያሸሽ ደጋግሜ አስተዋልኩኝ፡፡ በሙሉ ዓይኑ ሊያየኝ ስለምን ድፍረት እንዳጣ እየደነቀኝ ነበር፡፡ የሜሪ ጌታ ኢየሱስና የእማማ አፀደ መድኃኔዓለም እንዴት ያለውን ሞገስ አፍሶልኝ ይሆን? እያልኩ አስባለሁ፡፡ በኋላ ነገሮችን በወጉ ማስታወስ ጀመርኩና የእኔ የሆኑ ነገሮችን መጠየቅ ጀመርኩ፡፡ ስልኬ የት እንዳለ ስጠይቅ ገና ሊያመኝ እንደጀመረ አባቴ በንዴት ሰባብሮ እንዳስወገደው ነገሩኝ፡፡ የትምህርት ዶክሜንቶቼንም ስፈልግ ከሥፍራው አጣሁት፡፡ ዶክሜንቶቹ እንዳሉ ነገር ግን አባቴ እንዳስቀመጠው ተነገረኝ፡፡ በእንዲህ ያሉ ነገሮች የእናቴ ጭንቀት በግልፅ ስለሚታየኝ ስለ እርሷ እያልኩ ሁኔታዎችን በጸጥታ መከታተል ጀመርኩ፡፡ አንድ ቀን ግን ፈርጠም ብዬ አባቴን ትምህርት መቀጠል እንደምፈልግ ነገርኩት፡፡ እርሱም "አሁን ወሩ የዓመቱ አጋማሽ የካቲት ነው፡፡ መስከረም ላይ በአዲስ መንፈስ ትጀምሪያለሽ፡፡ እስከዚያ በቂ እረፍት አድርጊ፡፡ ከብዙ ጉዳት በኋላ ነው አሁን የተረጋጋሽው" በማለት ተረጋግቶ ተናገረኝ፡፡ ዲፕሎማት የአነጋገር ዘይቤውን በመቀጠልም "ዶክሜንቶችሽን እኔ ጋር ያረኳቸው በታመምሽ ጊዜ አውጥተሽ እንዳትቀዳድጅው በማሰብ ነው፡፡ እኔ አባትሽ ነኝ" አለና ተቆርቋሪነቱንና አርቆ አሳቢነቱን ሊያሳየኝ ጥረት አደረገ፡፡ ለምን እንደሆነ ባላውቅም አላመንኩትም፡፡ ተጨማሪ የቁጥጥር መረብ እየዘረጋ እንደሆነ ነው የተሰማኝ፡፡

በእርግጥ አባቴ አይወደኝም ልል አልችልም፡፡ ሊጨነቅልኝና ሊያስብልኝ እንደሚችልም አይጠፋኝም፡፡ ሌላ አባት የለኝም፡፡ የወለደኝ እርሱ ነው፡፡ በዚያም ላይ ተንከባክቦ አሳድጎኛል፣ ኢኮኖሚካል በሆነው ነገር ደግሞ አንቀባሮኛል ማለት ነው የሚቀለኝ፡፡ ካምፓስ እያለን የምመነዝረውን ብር ታውቂያለሽ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ፍቅርና እንክብካቤ ከእርሱና ሃይማኖቴ ከሚለው አስተሳሰብ ክበብ ውስጥ እስካላፈነገጥኩ ድረስ ብቻ ነው፡፡ የሕሊና እስረኛ አድርጎ የተሟላ ፍቅር አለኝ ማለት የማይዋጥ ነገር ነው፡፡ በዚህ በኩል ሂጂ፣ እንዲህ ልበሺ፣ ይህንን አድርጊ፣ ያኛውን አታድርጊ እየተባልሽ ወርቅ ቢያነጥፉልሽ ምን ይጠቅማል? ይህን የአባቴን አስተሳሰብና አቋሙንም ለማስጠበቅ የሚሄድበትን ርቀት ባሰብኩ ቁጥር ደግሞ መጻኢው ጊዜ ብሩህ ሆኖ አልታይ እያለኝ ያስጨንቀኛል፡፡ የእናቴ የዘወትር ጭንቀት ደግሞ ነገሮች ተካረው እኔ መልሼ እንዳልታመምባት ነው፡፡ እኔ በራሴ መንገድም ሆነ በአባቴ መንገድ ልሂድ ለእርሷ ግድ የላትም፡፡ የእርሷ ሥጋት ያለፈው የጭንቅ ወራት መልሶ እንዳይመጣ ብቻ ነው፡፡ ታናሽ እህቴ ከጸበሉ ሁኔታ በኋላ እኔን ከመደገፍ አልፋ ጥብቅና ወደ መቆምም ተሸጋግራለች፡፡ ቀሪዎቹ ወንድሞቼና እህቶቼ ደግሞ የነገሮች ውጥረት ምቾት እንደነሳቸው ያስታውቃሉ፡፡ አንዳንዴ በእኔ ችክታ ሌላ ጊዜ በአባቴ አምባገነንነት ይበሳጫሉ፡፡ የእኔ ተወዳጅ አባት ግን አንዳንዴ ሳስበው ያሳዝነኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን እንኳ የዘነጋው ይመስላል፡፡ በኡመርና አቡበከር ምናባዊ ሥርወ መንግሥት እንደሚተዳደር ሳይሰማው አልቀረም፡፡ ወይም ደግሞ የአልቃኢዳና የአይ ኤስ ሸሪያ ሕግ እዚም የሚሰራ መስሎታል መሰለኝ፡፡

ከአባቴ ጋር የአይጥና ድመት ፍጥጫችን ቀጠለ፡፡ ቁጭ ባልኩባቸው ወራት አባቴ ከቤት እንድወጣ የማይፈልግ እንደሆነ ተረዳሁ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ያለ ሂጃብና አባያ ከተማው ውስጥ ታይቼ የሁሴን ልጅ እንዲህ ሆነች ከሚባል ቤት ውስጥ በፈለገኝ አለባበስ ብቀመጥ የተሻለ እንደሆነ ገምቷል፡፡ ከአባቴ ሱቆች በአንዱ ውስጥ እንኳን ሥራ እንዳላግዝ ይኸው የአቋም ልዩነታችን ጋሬጣ ሆነ፡፡ ስለሆነም ቤት ውስጥ መጽሐፍ ሳነብና ቲቪ ስመለከት እንዲሁም የቤት ውስጥ ሥራን እናቴን በማገዝ አሳልፍ ጀመር፡፡ የተወሰኑ ሰዓታትንም እማማ አፀደ ቤት እየሄድኩ ከእርሳቸውና አብሮ አደጎቼ ከሆኑ ልጆቻቸው ጋር አሳልፍ ነበር፡፡ እማማ አፀደ ሃሳቤን፣ አቋሜን፣ ዕቅዴንና ተሥፋዬን እየሰሙ "የእኔ መድኃኔዓለም" ማለታቸውን አያቆሙም፡፡ አልፎ አልፎም በፈሊጥ "ብቻ ወዳጄ ከሆነው አባትሽ እንዳታቀያይሚኝ .." ይሉኛል፡፡ ወንድ ልጃቸው "በዚህ በሰለጠነ ዘመን እንዲህ ያለ ግግምና" በማለት ይገረማል፡፡ ሴቷ ደግሞ "አይዞሽ ኤፊ በደንብ ጸልዪ..እግዚአብሔር መንገድ አያጣም" ትለኛለች፡፡ በዚህ ዓይነቱ ድብብቆሽ ጥቂት ጊዜያቶች አለፉ፡፡ በኋላ ላይ ደግሞ አባቴ አንድ ሥልት መከተል ጀመረ፡፡ ይኸውም የተለያዩ ሙስሊም መምህራንን በተለይ ደግሞ ወጣቶቹን በግብዣና በእንግድነት ስም ወደ ቤት በማምጣት ከእኔ ጋር የሚወያዩበትን መንገድ ማመቻቸት ነበረ፡፡

የሚመጡት ወጣት መምህራን ቤተሰብ በተሰበሰበበት ስለ ነብዩ መሐመድ መመረጥ፣ ለእስልምናው ማህበረሰብ ስለከፈሉት ዋጋ ትኩረት ሰጥተው ያብራራሉ፡፡ የእስልምና እምነት በአማኞቹ ልብ የተገነባውና ትልቅ ሥፍራ እንዲይዝ የተደረገው ለመሐመድ ጥልቅ ፍቅር እንዲኖራቸው በማድረግ ነው፡፡ እንደ ጠንካራ ምሽግ በሚያዩት በዚህ መስመር የእኔን ልብ ለመማረክ ጥረት ማድረጋቸውን ገፉበት፡፡ እኔ ሞባይሌን እየጎረጎርኩ በከፊል አዳምጣቸዋለሁ፡፡ በማስከተል ደግሞ ክርስትናን የሚያብጠለጥል ርዕስ ያነሳሉ፡፡ እንዲህ ሲያረጉ አንዳንዴ በዚያው ሁኔታዬ በመቀጠል ሰበካቸውን አጠናቅቃለሁ፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ ሁሉንም ባሉበት ጥያቸው እነሳና ወደ ክፍሌ እሄዳለሁ፡፡ ጥያቸው በሄድኩ ቁጥር ሁልጊዜም ውዝግብና አነስተኛ ግርግር ይነሳል፡፡ አባቴ "ይኸው ንቀቷን እዩ" እያለ ሊኮንነኝ ይጀምራል፡፡ ዛቻና ፉከራውንም ይቀጥላል፡፡ ቀሪው ቤተሰብ መጨነቁን የሚገነዘቡት አስተማሪዎች አባቴን ያረጋጉታል፡፡ "አይዞት ሐጂ ቀስ ብሎ ቃሉ ወደ ልቧ መስረጉ አይቀርም..አይበሳጩ፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ዱአ እናደርጋለን፡፡ ከአልራህማን ውዴታ ተሥፋ አይቆረጥም" ይሉታል፡፡ እርሱም ቀጣዮቹን ቀናት በድጋሚ ተሥፋ እያደረገ መምህራኑን ይሸኛቸዋል፡፡

በዚሁ ትምህርቱን አቋርጬ በመሄዴ ሰበብ አንድ ጊዜ የተፈጠረው ግርግርን አልረሳውም፡፡ ሁለት ወጣት ኡስታዞች የተለመደውን ትምህርት ሰጡና በመቀባበል ስልት የክርስትና አስተምህሮዎችን መተቸት ጀመሩ፡፡ ነቀፋቸው ስላስጠላኝ ተነስቼ መሄድ ጀመርኩ፡፡ አባቴ ለካ ትዕግሥቱ ተሟጦ ኖሯል፡፡ መድረፍ ብሎ ተነሳና "ነይ" ሲል አንባረቀ፡፡ ጩኸቱ ቢያስደነግጠኝም በእርጋታ ዞር አልኩ፡፡ "እነዚህ የተከበሩ ኡስታዞች ሊያስተምሩ የመጡት አንቺን ነው፣ ረግጠሻቸው ስትሄጂ ትንሽ አታፍሪም?" ሲል ጮኸ በሌባ ጣቱ ጭንቅላቱን እየደበደበ፡፡ "አንዴ ሁለቴ አይደለም፣ ሁልጊዜ የአላህን ቃልና አገልጋይ ዳኢዎቹን ጠቅጥቀሽ የምትሄጂው አንቺ ማን ስለሆንሽ ነው?" ሲል አከለ፡፡ እኔም ተረጋግቼ ደግሞም ቆፍጠን ብዬ "እኔ ማንም አይደለሁም፡፡ ደግሞም ትምህርት ያልከውን ነገር ተምሬያለሁ፣ የጥላቻ ስብከት ግን ለማዳመጥ አልገደድም" አልኩት፡፡ "እንዴት እንዴት ነው የምትመልሺልኝ አንቺ?" ብሎ በእልህ ወደ እኔ ሲንደረደር ከየት ሥርቻ እንደተፈናጠረች ማንም ልብ ያላላት ታናሽ እህቴ ተወርውራ እግሩ ሥር ተነጠፈችና እግሮቹን ግጥም አርጋ ይዛ "አባዬ...! እህቴን...!" እያለች እሪታዋን አቀለጠችው፡፡ በአንድ ጊዜ ቤቱ ድብልቅልቁ ወጣ፡፡ እናቴም "ይተዉ ሐጂ ይተዉ...ባለፈውም እርስዎ ደብደበዋት ነው እንዲያ የሆነችው" እያለች ማልቀሷን ቀጠለች፡፡ ኡስታዞቹ፣ ታላቅ ወንድሜ፣ ሰራተኞች፣ ቤት ውስጥ ያለው ሁሉ በየፊናቸው ተተረማመሱ፡፡ ግማሾቹ አባቴን ለማረጋጋት፣ ሌሎች እናቴን ለማባበል፣ የተቀሩትም እኔን ለመቆጣት ተጣደፉ፡፡ ወንድሜና አንዱ ኡስታዝ ወደ ክፍሌ እየወሰዱኝ አባቴን ማክበር እንዳለብኝና ይሄን ያህል ላበሳጨው እንደማይገባ ሲመክሩኝ ቆዩ፡፡ ኡስታዙ በማጠቃለያው  "እኛ ነገሮችን በንፅፅር እንድታዪው እንጂ አንቺ እንደመሰለሽ የጥላቻ ነገር አልተናገርንም፡፡ ደግሞም ሁሉ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን የሚመችሽ እስላማዊ ዳዕዋ ብቻ ከሆነ እርሱኑ እናስተምርሻለን" አለና ክፍሉን ለቆ ሄደ፡፡ ያ ምሽት በእንዲህ ያለው ግርግር ተጠናቀቀና ሁሉ ወደ መኝታው አመራ፡፡

ሌላ ቀን ደግሞ ፊቱ በፈገግታ የተሞላ አንድ አስተማሪ መጣ፡፡ ልጁን ቀደም ብዬ የማውቀው ከመሆኑም በላይ ለቤታችንም አዲስ አልነበረም፡፡ የእርሱ አመጣጥ በግዴታ ሳይሆን በፍቅርና በማግባባት፣ ዙሪያ ጥምጥም በመዞር ሳይሆን በቀጥታ ወደ ጉዳዩ በመግባት ሊያወያየኝ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ የመጣውም ምሽት ከአባቴ ጋር ሳይሆን ከሰዓት ላይ ብቻውን ነው፡፡ አመጣጡን ሳየው እምነት ተጥሎበትና አንድ ዓይነት ሃላፊነት ተሸክሞ እንደሆነ ተገነዘብኩ፡፡ ልጁን የማውቀው ስለሆነ ይሁን የደስ ደስ ያለው በመሆኑ ይሁን አላወኩም፣ ነገር ግን በጥሩ ተግባቦት ረዘም ላሉ ደቂቃዎች አወራን፡፡ ገና ቤት እንደደረሰ ፊቱን ሁሉ ጥርስ አድርጎ ሞቅ ያለ ሰላምታ አቀረበ፡፡ በቀጥታም "ኤፊ ካንቺ ጋር ብርቱ ጉዳይ አለኝ..ግን የወዳጅነት፣ የጓደኝነት ነው፡፡ ውጥረት፣ ድብብቆሽ፣ ጥላቻ ቦታ የላቸውም" አለና ሳቀ፡፡ የራሱን አስተያየት በራሱ ሳቅ የማጀብ ልማድን ያደበረ ይመስላል፡፡ ተረጋግተን ከተቀመጥን በኋላ "አፊያ እስልምናን ተወች፣ ክርስቲያን ሆናለች ተብሎ የሚወራው እውነት ነው?" ሲል ጠየቀኝ፡፡ "አሁን ክርስቲያንም ሙስሊምም አይደለሁም፡፡ የወደፊቱን ፈጣሪ ነው የሚያውቀው" አልኩት በቀጥታ ንግግር፡፡ ከዚያች ደቂቃ ጀምሮ ብዙ ነገር ስናወራ ቆየን፡፡

እንደተለመደው ነቢዩ መሐመድ ለኡማው የከፈሉትን መሥዋዕትነት በሰፊው አብራራና "እንዴት የረሱል ፍቅር ከውስጥሽ ሊጠፋ እንደቻለ አልገባኝም?" አለኝ፡፡ እኔም "እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህና ከሃይማኖት ወገንተኝነት ነፃ ሆነህ መልስልኝ" አልኩት፡፡ "እሺ" አለኝ ከፈገግታ ጋር፡፡ "የአላህ መልዕክተኛ ለራሳቸው ኡመትና እዝነት ሆነው ለተላኩለት መላው ዓለም የጠቀስከውን ያህል መከራ መቀበላቸውና ዋጋ መክፈላቸው በሙስሊሞች ዘንድ ከታመነ፣ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ መከራ ተቀበለ ለመላው ዓለምም ቤዛና መሥዋዕት ለመሆን ተሰቀለ ማለታቸው ምኑ ላይ ነው ጥፋቱ?" አልኩት፡፡ ትኩር ብሎ ሲያየኝ ቆየና "ከሎጂክ አንፃር ልክ ነሽ፡፡ የሁለቱም እምነት ተከታዮች አባባል በገለልተኛ ዓይን ሲታይ ትክክል ይመስላል፡፡ ችግሩ ወደ መረጃ ስንመጣ ነው" አለኝ፡፡ "ወደ መረጃ ስንመጣስ ምን የተለየ ነገር ይኖራል?" አልኩት ምን ሊል እንደሚችል በመጓጓት፡፡ "ወደ መረጃ ስንመጣማ የነቢዩ መሐመድ ሐቅ የኢየሱስ ደግሞ ሐሰት እንደሆነ እንገነዘባለን" አለ፡፡ "እውነት? ይሄን የሚያረጋግጥ መረጃ ይኖራል?" አልኩት ጉጉቴ ሳይበርድ፡፡ "አዎ" አለ ፈርጠም ብሎ፡፡ "መረጃውም የአላህ ቃል የሆነው ቅዱስ ቁርአን ነው፣ ኢሣ ማለትም ኢየሱስ፡- ክርስቲያኖች እንደሚሉት አልተሰቀለም አልሞተምም፡፡ አላህ ወደ ላይ እንዳነሳው በቃሉ ነግሮናል" ሲል አከለ፡፡  በጣም ግርም ስላለኝ ሳቅሁ፡፡ በሳቄ በጥቂቱ የተረበሸ መሰለና ወዲያው ያንኑ ፈግታውን ተላበሰና "ምንድነው የሚያስቅሽ?" ሲል ጠየቀኝ፡፡ "በገለልተኝነት አይን እንድታየው የጠየኩህን አሁን ባሁን መርሳትህ ገርሞኝ ነው" አልኩና ውይይቱን ለማቆም አመነታሁ፡፡ እርሱ ግን "ቁራን የአላህ ቃል መሆኑንና የተነገረው ሁሉ እውነት መሆኑን አታምኝም እንዴ?" አለኝ፡፡ "አንድ ምንም ዓይነት እምነት የሌለው ሰው ቢጠይቅህ እንዲህ ነው የምትመልሰው? ክርስቲያኖችም እኮ መጽሐፋቸው የፈጣሪ ቃል እንደሆነ ነው የሚያምኑት፡፡ እናንተ መጽሐፋችን እንዲህ ይላል ስትሉ እነርሱም መጽሐፋችን እንዲህ ይላል ይላሉ፡፡ አየህ ነገሩ ፉክክር ብቻ ሆኖ ይቀራል ማለት ነው፡፡ እስቲ ገለልተኛ ከሆነ የታሪክ ምንጭ ክርስቶስ እንዳልተሰቀለና እንዳልሞተ የሚናገር መረጃ ልታቀርብልኝ ትችላለህ?" አልኩት፡፡ ጥያቄው ከበደው መሰለኝ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መበረዝ ዘበዘበልኝ፡፡ እኔም ስልችት ሲለኝ "ተው ባክህ ከሚል፡- ያልጠየኩህን ነገር ነው እያወራህ ያለኸው፡፡ ክርስቲያኖች ግን ክርስቲያን ያልሆኑ የመጀመሪያውና የ2ኛው መቶ ዓመት ታሪክ ጸሐፊዎች የክርስቶስን ስቅለትና ሞት እውንነት አረጋግጠው ጽፈዋል የሚል መረጃ ያቀርባሉ" አልኩት፡፡ ምንም የሚመልስልኝ ስላልነበረው ለአፍታ ዝም አለ፡፡

አሁንም ስለ ተለያዩ ነገሮች ስናወራ ቆየንና በጨዋታ መሐል "ክርስቲያን ቦይ ፍሬንድ እንደያዝሽ እገምታለሁ" አለኝ፡፡ ለምን እንዲህ ሊል እንደቻለ ስጠይቀው "ሁኔታሽ ያስታውቃል" በማለት ድፍንፍን አደረገው፡፡ እኔም "ማንም የወደደውን ማሰብ መብቱ ነው፡፡ በዚህ ምድር ላይ አለቃ የሌለው ነገር ቢኖር ሃሳብ ብቻ ነው" አልኩት፡፡ በንግግሬ ትንሽ ሲመሰጥ ቆየና "ክርስቲያን ባል ብታገቢ ግን አስበሽዋል...?" ሲል ጠየቀኝ፡፡ እጅግ ተደንቄ "ምኑን ነው የማስበው? ክርስቲያን ወንድ ለባልነት አይበቃም እንዳትለኝና ዓመት እንዳልስቅ ብቻ" በማለት በጥያቄው መገረሜን በንግግሬም በፊቴም ገፅታ ላሳየው ሞከርኩ፡፡ እርሱ ግን ከረር ባለ ቃል "ክርስቲያን ባል ለትዳርሽ ዋስትናም ሆነ ፍቅር አይሰጥሽም፡፡ በላይሽ ላይ የተደበቁ ውሽሞች ይይዝብሻል፡፡ በስካርና በቁማር ገንዘቡን ያባክናል፡፡ ልጆችሽንም ተንከባክቦ አያሳድግልሽም፡፡ ሙስሊም ወንድ ግን ከዚህ ሁሉ የጠራ ነው" አለ፡፡ እኔ ከሙስሊም ቤተሰብ ተወልጄ በዚያው ማህበረሰብ ውስጥ ያደግሁ መሆኔን እያወቀ እንዲህ ያለውን ቅጥፈት መናገሩ አናደደኝ፡፡ ሦሥትና አራት ሚስት አልበቃ እያላቸው ተጨማሪ ቁባቶች የሚይዙ ሥንት ሀብታም ሙስሊሞች አውቃለሁ፡፡ እናቴን ጨምሮ ብዙ ሙስሊም ሴቶች በክርስቲያኖች የአንድ ለአንድ ጋብቻ እንደሚቀኑ ሳስተውል ኖሬያለሁ፡፡ ጥላቻና የሚያጠግብ ምክንያት እጦት የወለደውን ይህን አስተያየት ጠንከር ባሉ ቃላት ለመመለስ ፈለግሁ፡፡ ቢቀየምም ይቀየም አልኩና "አይ ከሚል...አዕምሮህ ፈገግታ እንደማይለየው ፊትህ ብሩህ መስሎኝ ነበር፡፡ አዝናለሁ" አልኩት፡፡ ቀይ ፊቱ በርበሬ መምሰል ሲጀምር አስተዋልኩት፡፡ "ደንቆሮ ነህ እያልሽኝ ነው?" ሲል ለመጀመሪያ ጊዜ ተኮሳትሮ ጠየቀኝ፡፡ ሳውቀው ጭራሽ መኮሳተር እንኳ የሚችል አይመስለኝም ነበር፡፡ እኔም ቅጭም ብዬ "ደንቆሮ ነህ አልወጣኝም፡፡ ነገር ግን ጨለምተኝነት አይብሀለው፣ ክርስትናንና ክርስቲያኖችን በጠቅላላ በጥቁር መነጽር ነው የምትመለከተው" አልኩት፡፡

ከዚህ በኋላ ጥቂት ነገር አወራን፡፡ ውይይታችን ግን የመግባባት ወዝ የራቀው መቆራቆስ መሰለ፡፡ በመጨረሻ ይለይለት ብዬ "አላህ ለወንዶች እስከ አራት ሚስቶች እንዲያገቡ ሲፈቅድ ለሴቷ ተመሳሳይ መብት ለምን እንደከለከላት እስቲ ንገረኝ?" አልኩት፡፡ እንደበሸቀ ያስታውቃል፡፡ ቢሆንም ሳቅ እያለ "መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሰለሞን 700 ሚስቶች ማግባቱ ተገልጿል፣ ሌሎችም ሁለት፣ ሶስትና ከዚያ በላይ ያገቡ አሉ፡፡ በክርስትና ብዙ ሚስት ማግባት አልተከለከለም" አለኝ፡፡ "መጽሐፍ ቅዱስ እንደተበረዘ እኮ ነግረኸኝ ነበር፡፡ ክርስትናም ፍፁም ስህተት እንደሆነና ቁራን ይህን ስህተት ሊያርም መውረዱን ነው ስትሰብከኝ የቆየኸው፡፡ አሁን ለዚህ ጥያቄ የመጽሐፍ ቅዱስ መረጃ መጥቀስ ምን ማለት ነው? ደግሞስ ስህተት ነው የምትሉትን ክርስቲያናዊ ልምምድ በቁሙ መውረስ ተገቢ ነው እያልከኝ ነው?" አልኩት ትክ ብዬ እያየሁት፡፡ ውስጡ እርር እያለ ተፈጥሯዊ ባልሆነ ፈገግታ ስሜቱን ለመደበቅ ይታገላል፡፡ አንገቱን በአሉታ ደጋግሞ እየወዘወዘ ከመቀመጫው ተነሳ፡፡ "እንደምንግባባ ተሥፋ አድርጌ ነበር፣ ፈፅሞ እንዲህ ትሆኛለሽ ብዬም አልጠበኩም... አዝናለሁ" አለና ለመሰናበቻ ሰላምታ እጁን ዘረጋልኝ፡፡ እጁን ጨብጬ ጥቂት ያዝኩት "ከሚል...እባክህ አትቀየመኝ፡፡ በውስጤ ያለውን ነገር በግልፅ ነው የተወያየሁህ፡፡ ከቻልክ ደግሞ ፀልዪልኝ" አልኩት፡፡ እጄን ቀስ ብሎ አስለቀቀና "አላህ ቅኑን መንገድ ይምራሽ" ሲል መርቆኝ እናቴን እንኳን ሳይሰናበት ሄደ፡፡ ከሄደ በኋላ ጥቂት አሰብኩ፣ የሆነ ሥጋትም ገባኝ፡፡ በጣም እንደተጋፈጥኩትና ያልተለመደ ድፍረት እንዳሳየሁ ታውቆኛል፡፡ ውይይታችንን ቃል በቃል ለአባቴ ከነገረው የሚፈጠረው ነገር ታሰበኝና "ኡፍ..." ብዬ በረዥሙ ተነፈስኩ፡፡

ያን ቀን ምሽት አባቴ ወደቤት አልተመለሰም፡፡ ዘንግቼው እንጂ መመለሱ የማይጠበቅ ነበር፡፡ ትናንት እኛ ቤት ስላደረ ዛሬና ነገ ቀሪዎቹ ሚስቶቹ ጋር ነው የሚያድረው፡፡ ይህንን ባስተዋልኩ ጊዜ ትልቅ እፎይታ ተሰማኝ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አባቴ እኛ ጋር በሚያድርበት ጊዜ ሁሉ ደስ የማይል ውጥረት ሲነግስ እርሱ በማይመጣባቸው ምሽቶች ደግሞ ቀለል ያለ ድባብ ከሳቅና ሁካታ ጋር ይሰፍናል፡፡ ሁሉ ሰው የዕለት ገጠመኙን በነፃነት እያነሳ ያወራል፡፡ ሌሎች ብዙ ቤተሰባዊ ጨዋታዎችም የምሽቱ ማድመቂያዎች ናቸው፡፡ ጸበል ሳለሁ ተመላልሶ ሲጠይቀኝ የነበረውና የአባቴ የንግድ አጋር የሆነው ሁመይድ አልፎ አልፎ እየመጣ አምሽቶ ይሄዳል፡፡ አባቴ ሲኖር የሚፈጠረውን ውጥረት ተገንዝቧል መሰለኝ የሚመጣው አባቴ በማይኖርበት ምሽቶች ነው፡፡ በሚያነቅፈው አማርኛው የተለያዩ ጨዋታዎችን በማንሳት ያስቀናል፡፡ ብዙ ሀገሮች ዞሮ ከማየቱም ሌላ በትውልድም ሆነ በዜግነት የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ሰው በመሆኑ ከሀገሩና ከተለያዩ ሀገሮች ያየውንና ያጋጠመውን በመተረክ ሲያስቀን ያመሻል፡፡ ታናሽ እህቴና ትንሹ ወንድሜ በጥያቄ ልቡን ዝቅ ያረጉታል፡፡ እርሱም ሳይሰለች በመመለስ የጨዋታው ማዕከል ይሆናል፡፡ ተነስቶ ሲሄድ እስከ በርም ቢሆን የመሸኘቱ ሃላፊነት የእኔ ነው፡፡ ይህን ሃላፊነት ማን እንደሰጠኝ አላውቅም፡፡ ምናልባት ጸበል ሳለሁ ተመላልሶ ስለጠየቀኝ የሆነ የይሉኝታ ወይም የውለታ ስሜት አሳድሮብኝ ይሆን ስል ራሴን እጠይቃለሁ፡፡

ከሁለት ቀን በኋላ ምሽት ላይ ገና ቤተሰቡ ሳይሰበሰብ ሳሎን  ቁጭ ብዬ መጽሐፍ እያነበብኩ ሳለ አባቴ ድንገት መሰስ ብሎ ገባ፡፡ የዚያን ሰዓት እንዴት እንደደነገጥኩ አትጠይቂኝ፡፡ ብቻ ልቤ ለሁለት ስንጥቅ አለ፡፡ እንደ መቆምም እንደመቀመጥም አደረገኝ፡፡ ለብሼው የነበረው ትልቅ ፎጣ ከላዬ ተንሸራትቶ ሲወድቅ እንኳ ልብ አላልኩም፡፡ የሞት ሞቴን ሶፋው ላይ የተቀመጠውን አባቴን ሰረቅ አድርጌ ሳየው አተኩሮ እየተመለከተኝ ነበር፡፡

                                (ይቀጥላል)

         ---------- ማርያማዊት ገብረመድኅን ----------
saramareyama.890@gmail.com

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የምዕራፍ አምስት(፭)የ46 የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ

✝በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡ አሜን! ↪️የምዕራፍ አምስት(፭) 46ኛ ዙር የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ⤵️ 1⃣ ቅዱስ ያሬድ ከመላዕክት የተማራቸው ሦስቱ የዜማ ዓይነቶች ምን ምን ናቸው?ሞገር...