ዓርብ 8 ዲሴምበር 2017

አፊያ ሁሴን ክፍል ፫

#አፊያ #ሁሴን

እውነተኛ ታሪክ

ክፍል 3

አፊያ ሁሴን (ክፍል ፫)

ራሴን ከሳትኩ በኋላ ምን እንደተፈጠረ አላወቅሁም፡፡ በኋላ እንደሰማሁት ግን ከሰመመኔ ስነቃ መሳቅ፣ መሳደብና፣ መጮህ አብዝቼ ነበር፡፡ በአዕምሮዬ ውስጥ ያሉ ነገሮችን ሁሉ እያወጣሁ ሳልለፈልፍ አልቀረሁም፡፡ ያንቺን ስም በተደጋጋሚ ጠርቻለሁ መሰለኝ እህቶቼ በነቃሁና በተረጋጋሁ ቁጥር "ሜሪ ማናት? የካምፓስ ጓደኛሽ ናት? ክርስቲያን ናት?" እያሉ በጥያቄ ያጣድፉኝ ጀመር፡፡ ሌሊቱን ሁሉ እኔም ስንገላታ እነርሱንም ሳንገላታ አደርኩና ሊነጋጋ ሲል እንቅልፍ ተኛሁ መሰለኝ፡፡ ነገሩ ሁሉ ከእንቅልፍ ጋር እንደሚያልፍ ተጠብቆ ነበር፡፡ የሆነው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለስምንት ወራት ያህል ታመምኩ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደህና ሆኜ እውላለሁ፡፡ ሆኖም ድንገት ራሴን ስቼ እወድቃለሁ፡፡ ከዚያ መለፍለፍ፣ መቀባጠር፣ መጮህ፣ መሳደብ እቀጥላለሁ፡፡ ራሴንና ሌሎችንም ላለመጉዳት ይታገሉኛል መሰለኝ ወደ አዕምሮዬ ስመለስ ሰውነቴ ድቅቅ ይልብኝና ረዥም ሰዓት እተኛለሁ፡፡ ይህ ነገር  ሲደጋገም ቤተሰቦቼ ክርስቲያን ጂኒ ነው የያዛት የሚል ፈሊጥ አመጡልሽና ከአሥር ለማያንሱ ቀናት ሼኮች እየተሰበሰቡ፣ ጫት እየተቃመና ቡና እየተፈላ፣ ማርና ጥቁር አዝሙድ ሌላም ሌላም ነገር አንዳንዴ እየቀቡኝ አንዳንዴም እየጋቱኝ ዱአ ማድረግ ጀመሩ፡፡ እንግዲህ ጸሎት መሆኑ ነው፡፡ እኔንም ታስቸግር ይሆናል በሚል ከሚይዙኝ ሰዎች ጋር በሚቅሙበት ክፍል አብሬ እንድሆን ያደርጉ ነበር፡፡ እንደተጠበቀውም አንዳንድ ጊዜ እንደ እብድ እያረገኝ ፍራሻቸውንና ዕቃውን ሁሉ ምንቅርቅሩን አወጣው ነበር፡፡ አንዳንዴም ፀጥ ብዬ እተኛለሁ፡፡ በጣም አልፎ አልፎም በአዕምሮዬ እሆንና የሆነውን ሁሉ እያሰብኩ ስቅስቅ ብዬ አለቅስ ነበር፡፡ እነርሱ ግን ለቅሶዬ የሕመሜ መገለጫ ይመስላቸው ነበር፡፡

የእነርሱ ዱአ ፍሬ ቢስ መሆኑን ራሳቸውም ቤተሰቦቼም ተገነዘቡ መሰለኝ ተሥፋ ቆርጠው ተዉት፡፡ አንዳንድ እበላ ባይ ሼኪዎች ብቻ ከአባቴ ጋር እየመጡ ምኑንም ምኑንም ይቀበጣጥሩ ነበር፡፡ የእኔ ሕመም ግን እየባሰ ሄደ፡፡ አንዳንዴ አይምሮዬ ያለ ልክ እየተወጠረ ሊፈነዳ እስኪመስለኝ ድረስ እጨነቃለሁ፡፡ በማንኛውም ጊዜና ሥፍራ አዕምሮዬን ስቼ ስለምወድቅና ከዚያም በኋላ የሚሆነውን ስለማላውቅ በራስ መተማመኔ ጠፍቶ የእህቶቼ ጥገኛ ሆንኩ፡፡ ይህም የነበረኝን የሞራል ልዕልናና የስነ-ልቡና የበላይነት ቀስ በቀስ እያነካከተው መጣ፡፡ የምግብ ፍላጎቴ እየወረደ፣ ሰውነቴ እየከሳ፣ ጉስቁልናና መገርጣት በግልፅ ይታይብኝም ጀመር፡፡ ያልወሰዱኝ የሕክምና ሥፍራ አልነበረም፡፡ ሁሉም ግን የሚሉት ምንም ዓይነት የበሽታ ምልክት አይታይባትም ነው፡፡ ቢቸግራቸው አንድ የስነ-አዕምሮ ሐኪም ዘንድ ወሰዱኝ፡፡ ቀለል ያለ ጭንቀትና የአዕምሮ ውጥረት ነው ያለባት አለና በቂ እረፍት እንዳደርግ በመምከር አንድ አገር የእንቅልፍ ክኒን አሸከመኝ፡፡ ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን የሆነ የድብርት ስሜት ውስጥ ከመክተት ባለፈ ምንም የረባኝ ነገር አልነበረም፡፡

አንድ ቀን እንዲሁ ጮሄ ጮሄ ወደ ልቡናዬ እንደተመለስኩ በመንደሩና በሴት ዕድር ውስጥ የታወቁ ወ/ሮ አፀደ የሚባሉ አንዲት ጎምቱ ሴት መጡ፡፡ ተረብሸው የቆሙትን ቤተሰቦቼን እንደነገሩ ሰላም ብለው "እኔ የምለው እናንተ...ይህቺን የመሰለች አበባ አፍናችሁ ልትገሉ ነው እንዴ ሃሳባችሁ? ለምንድነው ጸበል የማትወስዷት?" ሲሉ በማፋጠጥ መልክ ጠየቁ፡፡ ቀና ብዬ ሳያቸው ፊታቸው በንዴት ቀልቶ እንደ እሳት ነበልባል የሚፋጅ ይመስላል፡፡ እናቴ ማልቀስ ጀመረች፡፡ የተፈራው አባቴ እንኳ የሚለው ጠፍቶት እንደ ሕጻን ልጅ መሬት መሬት እያየ ተቅለሰለሰ፡፡ "ሐኪሙንም ጸሎቱንም ሞክራችኋል፣ ብዙ እንደደከማችሁ እናውቃለን፡፡ ግን ለምን ጸበል አትወስዷትም? ጸበል አንወስድም የምትሉት የእናንተ እምነት የተለየ ነው እንዴ? ሥንቱ ሙስሊም አይደል እንዴ ጸበል ያለው፣ ለምን ሄዳችሁ አታዩም? ሥንቱስ ነው ተፈውሶ የሚመሰክረው" ሲሉ አከሉ፡፡ ሴትየዋ ምንም የተከበሩ ቢሆኑ ይህ ንግግራቸው ደግሞ ይበልጥ ባለ ግርማ መሰለ፡፡ ሁሉ በዝምታ በተዋጡ ጊዜ ከአባቴ ሥር ሥር ከሚሉ ሰዎች ውስጥ አንድ ቀሚስ የለበሰ ልጅ እግር ሙስሊም ወደ ሴትየዋ ጠጋ አለና "አይደለም እኮ እናታችን የእርሷ ሕመም የተለየ ነው" አለ፡፡ "ምኑ ነው የተለየው?" አሉ እስካሁን ድረስ በማልረሳው የግርምት አስተያየት እያዩት፡፡ "እርሷን የያዛት ክርስቲያን ጂኒ ነው" ብሎ ሲጀምር "ምን?" አሉት አይናቸውን አጉረጥርጠው፡፡ "አዎን ክርስቲያን ጂኒ አለ፣ ሙስሊምም ጂኒ አለ...እርሷን የያዛት ክርስቲያን ጂኒ ስለሆነ ጸበል ብትሄድ ይብስባታል" አለ፡፡ እማማ አፀደ በማበሻቀጥ መልክ እጃቸውን እያወናጨፉ "ኧረ ወደዚያ ዞር በልልኝ ይሄ ደግሞ ምን የሚሉት አማርኛ ነው? ሰይጣንን ደግሞ የምን ማሽሞንሞን ነው? አንተዬ...እናንተ ጂኒ ካላችሁ እናንተው ታውቃላችሁ፡፡ እኛን ግን ሲያልፍም አይነካን" አሉ በአይናቸው እየገረመሙት፡፡

ወ/ሮ አፀደ አንዳች የመፈራት ሞገስ ትከሻቸው ላይ የወደቀባቸው ደርባባ አዛውንት ናቸው፡፡  ያ ጥላ ቢስ ልጅ ግን "አይደለም እኮ.." ብሎ ንግግር ሊጀምር ሲል "ተወኝ ብዬሃለው አንተ፣ አምጣ የወለደች እርሷ አንተ ምን ቤት ነህ?" ብለው ተቆጡ ወደ እናቴ እያመለከቱ፡፡ አባቴም "ከድር" ሲል ልጁን እየተጣራ በአይኑም በእጁም ገሰፀው፡፡ ሴትየዋ ወደ አባቴ ዞረው እጃቸውን እያወዛወዙ "አንቱ ሰውዬ ይህቺን ቀንበጥ በገዛ እጅዎ እንዳይቀጥፏት ተጠንቀቁ፡፡ ጸበል ይላኳት ብዬዎታለሁ፡፡ የእኔ መድኃኔዓለም እንኳን ይሄን ምናምኑንና ልክስክሱን ይቅርና ሥንቱን እውር እንዳበራ፣ ሥንቱን ሽባ እንደተተረተረ፣ ሥንቱ በወሳንሳ መጥቶ እየቦረቀ እንደተመለሰ ባያችሁ፡፡ አንድ ሰባት በቂዋ ነው፣ ግፋ ቢል ሁለት ሰባት..ነቅሎ ባይጥልላት መልዐኩ ገብርኤል ይኸው ከምላሴ ጸጉር" አሉ በእጃቸው ከምላሳቸው አንዳች ነገር እንደሚነቅል ዓይነት እያሳዩ፡፡ እንደገናም ረጋ ብለው "እኔ ጎሮቤት ነን፣ ይህቺም ሴት ወዳጄ ናት፣ ልጅቱም ከልጆቼ የማልለያት ናት ብዬ ቆጭቶኝ ነው የመጣሁት፡፡ ደግሞም የሚበጀውን ነው የነገርኳችሁ... ለአፊያ ግን ይሄ አይገባትም፣ ፈፅሞ አይገባትም" አሉና ወደ መውጫው አመሩ፡፡ በሩ ጋር ሲደርሱ ለአፍታ መለስ አሉና "ምናልባት ይዞ መሄድ አፍራችሁ፣ ወይም አላደርሳችሁ ብሎም ከሆነ ለእኔ ስጡኝ፡፡ እኔ ከልጆቼ ጋር የሰፈሩን ሰው አስተባብሬ ይዘናት እንሄዳለን... ደግሞ ለአፊያ" ብለው በሩን ከፍተው ወጡ፡፡ ይሄኔ እናቴ እዬዬዋን አስነካችው፡፡ ለያዥም ለአባባይም አስቸገረች፡፡ አባቴ ቀስ ብሎ ወጣና ከወ/ሮ አፀደ ጋር ውጭ ላይ መነጋገር ጀመረ፡፡ የቤቱ ደረጃ ላይ ሆነን ባሻገር ይታዩናል፡፡ እርሳቸው እጃቸውን እያወናጨፉ ሲያወሩ እርሱ እጆቹን የኋሊት አነባብሮ አቀርቅሮ ይሰማቸዋል፡፡ ጥቂት ቆይቶ ተመለሰና እናቴን እንደማባበልም እንደመቆጣትም ካረገው በኋላ ለታላቅ ወንድሜ መመሪያ ነገር ሰጥቶ ከዚያ አቸፍቻፊ ልጅ ጋር ወጥቶ ሄደ፡፡

ወንድሜ አንድ ፒክ ኣፕ መኪና ማዘጋጀት ጀመረ፡፡ ወ/ሮ አፀደ ሲደዋወሉ ቆዩና እንጦጦ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ለፍልሰታ ሱባዔ የሚይዙበት ቤት ዝግጁ መሆኑን ገልጠው የሚያስፈልገን አልባሳትና አንዳንድ ዕቃዎች ተጫነ፡፡ ማምሻውን በታናሽ እህቴ፣ በእማማ አፀደና አብሮ አደጎቼ በሆኑ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጆቻቸው፣ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን በሚያዘወትር አንድ ሌላ የሰፈራችን ልጅ ታጅቤ ወደ እንጦጦ ኪዳነ ምህረት አመራን፡፡ በጉዞው ላይ ጋቢና የተቀመጡትን እማማ አፀደ እየተመለከትኩ እደነቅ ነበር፡፡ በየደቂቃው ጣታቸውን ወደ ሰማይ አቅጣጫ እየጠቆሙ "የእኔ መድኃኔዓለም ..." ይላሉ፡፡ ሌላው ንግግራቸው ባይሰማም ዛቻም ማጉተምተምም የሚመስል ቃና አለው፡፡ ከአምላካቸው ጋር የሆነ ዓይነት ፉክክር ውስጥ የገቡ ይመስሉ ነበር፡፡ ልክ ሽሮ ሜዳን አልፈን የእንጦጦን ዳገት ስንጀምር እንደተለመደው ከአዕምሮዬ ውጭ ሆኛለሁ ኖሯል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ያለውን ሁኔታ ፈፅሞ ማስታወስ አልቻልኩም፡፡ በኋላ እንደሰማሁት ግን እማማ አፀደን ስሳደብ፣ ከኋላ ካላነቅኋቸው ብዬ ስታገል በወንዶቹ ብርታት ተይዤ ከሥፍራው ደርሰናል፡፡ በትክክል ራሴን ያወቅሁት በማግስቱ ማለዳ ላይ ጸበል እየተጠመቅሁ ሳለ ነው፡፡

እዚያ በቆየሁባቸው ሃያ አንድ ቀናት ውስጥ የሚደረገው የጸሎትና ጸበል የመጠመቅ ሥርዓት ወጥና ተመሳሳይ መሆኑን አስተውያለሁ፡፡ ሁልጊዜ ከማለዳው 11፡00 ሰዓት ላይ እንነሳና ጸበል ለመጠመቅ እንወርዳለን፡፡ አንዳንዴ የሚበዛውን አንዳንዴም የሚያንሰውን ወረፋ ታግሰን እጠመቃለሁ፡፡ ከዚያም ጸበል ስጠጣ እቆያለሁ፡፡ ከዚያም ከ4፡00 ሰዓት ጀምሮ ደግሞ እዚያው ቤተክርስቲያን ውስጥ በአንዲት አነስተኛ ቤት ወዳሉ ታዋቂ መነኩሴ ዘንድ ይወስዱኛል፡፡ እዚያም የሚኖረውን ወረፋ ጠብቄ በቅብዐ ቅዱስና በመስቀል ጸሎት ያደርጉልኛል፡፡ በመነኩሴው ላይ ያለው ጸጋ የበረታ እንደሆነ ነገረ ሥራቸው ያስታውቃል፡፡ በክፉ መንፈስ የተያዙ ሰዎችን ገና ወደ እርሳቸው ቀረብ ሲያደርጓቸው ነበር መጮህና መንፈራፈር የሚጀምሩት፡፡ እኔንም ደጋግሞ እንደዚያ አድርጎኛል፡፡ መነኩሴው በእርጋታና በለሆሳስ እየፀለዩ፣ ቅባ ቅዱሱን በግንባር ላይ በመቀባት በመስቀል ሲነካኩ የሚፈጥረው የማስጨነቅ ስሜት ልነግርሽ አልችልም፡፡ እንዲያ ለያዥ ለገራዥ ያስቸግር የነበረ ሁሉ ልክ እሳቸው ጋር ሲገባ እንደ መንፈቅ ልጅ እግራቸው ሥር መርመስመስ ይጀምራል፡፡ መነኩሴው በዕድሜ የገፉ ቢሆንም ጽናታቸው ግን የጉድ ነው፡፡ ከርኩሳን መናፍስት ጋርም እልህ የተጋቡ ነው የሚመስሉት፡፡ አንድ በክፉ መንፈስ የተያዘ ሰው ገብቶ ክፉው መንፈስ ጮሆ ለቅቄያለሁ ካላለ በቀር ፈፅሞ አይለቁትም፡፡ ስለዚህም እርሳቸው ጋር ለመግባት ረዣዥም ሰልፎችንና ሰዓታትን መታገስ የግድ ነበር፡፡ የመነኩሴው አገልግሎት ለመድረስ እንጂ ለማዳረስ እንዳልሆነ በደንብ ያስታውቃል፡፡ "በመድኃኔዓለም ሕንጻ ላይ አንተ ምን ቤት ነህ?" በማለት ሰይጣንን የሚገስፁበት የተለመደ ቃላቸው ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ሁልጊዜ ከመነኩሴው ዘንድ የምንወጣው ከሰዓቱ ከተጋመሰ በኋላ ነው፡፡ ከዚያም ወደተከራየነው ቤት ተመልሰን እህል ውሃ እንቀምሳለን፣ ጥቂትም እረፍት እናደርጋለን፡፡ ወዲያው ደግሞ 10፡00 ሰዓት ሲሆን ለሕሙማን የሚደረግ የሰርክ ጸሎት ላይ ለመሳተፍ ወደ አዳራሽ እንሄዳለን፡፡ ከጸሎቱ በኋላ የዘወትሩን ስብከተ ወንጌል ተከታትለንና በየግላችንም ጸልየን ወደ ቤት እንመለሳለን፡፡ የየዕለቱ በጸሎት የመጠመድ ውሎአችን ይህን ሲመስል በእማማ አፀደ አገላለጥ ደግሞ ደጅ ጥናት ይባላል፡፡
እዚያ ያለውን ሁኔታ በጣም ነበር የወደድኩት፡፡ በቃ ልገልፀው የምችለው "በሕመም ውስጥ ሆኖ የደስታና የእርካታ ስሜት ውስጥ መግባት" በሚለው ሐረግ ብቻ ነው፡፡ አስታማሚዎቼ የሚያረጉልኝን እንክብካቤና የሚያሳዩኝን ፍቅር ለመግለፅ ይቸግረኛል፡፡ አዲስ ሕመምተኛ የሆንኩ ይመስል የሰፈራችን ሰዎች በቡድንና በተናጠል እየሆኑ ሲጠይቁኝ በጣም ይደንቀኝ ነበር፡፡ ለወራት ቤቴ ሆኜ ስታመም ከጥቂቶች በቀር የሚጎበኘኝ አልነበረም፡፡ እናም በጠያቂ ብዛት ስከበብ "ቤታችንና ቤተሰቦቼ ለመንደሩ ሰው ያን ያህል ዝግ ነበሩ ማለት ነው?" ስል ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ ከሙስሊም ዘመዶቻችንና ወዳጆቻችን ውስጥ ጥቂቶቹ መጥተው ቢጎበኙኝም የሚመስላቸው ነገሩ ወደ ከፋ ደረጃ እንንደደረሰና ጸበል መግባቴም የተሥፋ መቁረጥ ምልክት እንደሆነ አድርገው ነው፡፡ ከእነርሱ መሐል ግን በየቀኑ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ እየመጣ የሚጠይቀኝ አንድ ጎልማሳ ነበር፡፡ ይህን ሰው ቀደም ብሎ ጀምሮ አልፎ አልፎ ቤታችን ሲመጣ አውቀዋለሁ፡፡ አንድ ሁለት ቀን ከወንድሞቼ ጋር መጣና በኋላ ብቻውን ይመላለስ ጀመር፡፡ አማርኛ አጠር በሚለው ንግግሩ ሲያወራ ጨዋታው የሆነ የመዝናናት ስሜት ይፈጥራል፡፡ ጸበል ከሚያስጠምቁኝ ወንድሞች ጋር ሁሉ እስከ መግባባት ደርሶ ነበር፡፡ በዚያ ላይ በየቀኑ እዚያ ሥፍራ የማንጠቀምበትን ነገር ሁሉ እየተሸከመ ይመጣል፡፡ ይሄ ሁሉ ጠብ እርግፍ ለምን እንደሆነ የገባኝ ግን እጅግ ዘግይቶ ነበር፡፡

ጸበል በገባሁ በአሥራ ሁለተኛ ቀኔ እጅግ የሚያስገርም አንድ ሕልም አየሁ፡፡ ሕልሜን አሁን እንኳን ትናንት ሌሊት ያየሁት እስኪመስለኝ ድረስ በጣም በግልፅና በዝርዝር አስታውሰዋለሁ፡፡ ጢስ አባይ የሄድን ጊዜ ታስታውሻለሽ አይደል? ወደ ፏፏቴው ስንመለከት የውኃው ፍንጥርጣሪ ጉም የሚመስል ነገር ይፈጥር ነበር፡፡ እናም በዚያ ዓይነቱ ጉም መሳይ ነገር ተከብቤ ወይም ተውጬ ያለሁ ይመስለኛል፡፡ የሚሰማኝ ስሜት መጀመሪያ ሰዎች የነበሩና በኋላ ግን በድንገት ብቻዬን በዚያ ሁኔታ እንዳለሁ ዓይነት ነው፡፡ ከጉሙ ውስጥ ለመውጣት ስታገል እጆቼም ሆኑ እግሮቼ እንደልብ መንቀሳቀስ ይሳናቸዋል፡፡ ልክ በሸረሪት ድር እንደተያዘች ነፍሳት ከየአቅጣጫው በጉሙ ተወጥሬ እንደተያዝኩ ሆኖ ነው የሚታየኝ፡፡ ዙሪያዬን ቃኝቼ ሳሳ ወዳለው የጉሙ ሽፋን ለመንቀሳቀስ ብሞክር እንኳ እንቅስቃሴዬ ዓመታት የሚፈጅ ያህል እጅግ በዝግታ ይሆንብኛል፡፡ ጠፈር ላይ የሄዱ ሰዎች እንደሚሆኑት ዓይነት በጣም በቀስታና በትግል የምንቀሳቀስ ይመስለኛል፡፡ በዚያ ላይ የተበተበኝ ጉም ወደሆነ አቅጣጫ ይዞኝ እየሄደ እንዳለም ይሰማኛል፡፡ ራሴን ለማዳንና ከጉሙ ለመውጣት ብታገልም የማይሞከር ሲሆንብኝ በከፍተኛ ድምፅ እጮሃለው፡፡ ነገር ግን የገዛ ጩኸቴ እንደ ገደል ማሚቶ እያስተጋባ፣ እየተመሳቀለና አስፈሪ እየሆነ በገዛ ጆሮዬ ላይ ሲደውልብኝ የምሆነው ይጠፋኛል፡፡ እየጮህኩ፣ ለመወራጨት እየጣርኩ ነፍስና ሥጋዬ በሰቀቀን ተይዛ ሳለ ከወደላይ በኩል በጣም ረዥም፣ ቀይ፣ እንደ ጥንታውያን የሮማ ወታደሮች ደረቱን፣ ክንዱንና ቅልጥሙን በወርቅ ጥሩር የታጠቀ፣ ራሱ ላይ እክሊል መሳይ ነገር የደፋ ጎልማሳ በጥልቅ ሀዘኔታ ቁልቁል ሲመለከተኝ አየሁት፡፡ ወዲያው ልክ ከሄሌኮፕተር ላይ በምድር ላሉ ወታደሮች መወጣጫ ገመድ እንደሚዘረጋ የሆነ ገመድ መሳይ ነገር ይወረውርልኝና ወደ ላይ ይስበኛል፡፡ በሳበኝ ቁጥር ጉሙ ላለመልቀቅ እንደመታገልም፣ በሰውነቴ ተጣብቆ እንደመከተልም ይለኝና ነገር ግን እየተበጣጠሰ ወደታች ይወድቃል፡፡ ወዲያውም በኃይል መንጭቆ ይስበኝና ልክ እንደ ጅምናስቲክ ስፖርተኛ እግሩ ሥር ቁጢጥ ብዬ አርፋለሁ፡፡ ጉሙ ውስጥ ሆኜ ከዚያ ስቃይ ያወጣኝን  ጎልማሳ ሳየው ረዥም እንደሆነ አስተውዬ ነበር፡፡ አሁን እግሩ ሥር እንዳለሁ ቀና ብዬ ላየው ስሞክር ጭራሽ ቁመቱ ያለልክ ረዝሞ ፊቱና ራሱ ሰማያትን ነክቶ አያለሁ፡፡ በሁኔታው እጅግ በመደነቅ ላይ ሳለሁ ድንገት ብንን እላለሁ፡፡ ከእንቅልፌ ስባንን ሰውነቴ በላብ ተዘፍቆ ነበር፡፡

በነገሩ እንዲሁ እንደተደነቅሁ ነጋና ወደ ጸበል አመራን፡፡ የዚያን ዕለት እማማ አፀደ ቤታቸው ነበርና ያደሩት ከጸበል እንደወጣሁ ደወልኩላቸው፡፡ "ምነው ልጄ ችግር አለ እንዴ?" አሉኝ፡፡ "ኧረ ምንም ችግር የለም፣ አንድ ሕልም አይቼ ለእርስዎ እስክነግር ቸኩዬ ነው፡፡ በዚያውም ይፈቱልኛል" አልኳቸው፡፡ "እመጣለሁ ልጄ እመጣለሁ፣ ነገ እመቤታችንም አይደለች? አዳሬን ነው የምመጣው" አሉ፡፡ ማምሻውን መጡና ያየሁትን ሕልም ነገርኳቸው፡፡ እንደተለመደው በየመሐሉ እጃቸውን ወደ ላይ እየዘረጉ "አይ የእኔ መድኃኔዓለም" ሲሉ ቆዩና "ምን ፍቺ ያስፈልገዋል ይሄ? ግልፅ አድርጎ አይደል እንዴ ያሳየሽ፣ ነይ ሳሚኝ..ነይ ሳሚኝ" አሉና አገላብጠው ሳሙኝ፡፡ በማግስቱ የማርያም ዕለት ስለነበር ፀበልተኛም ተሳላሚም በዝቶ ነበር፡፡ እኔ ስጠመቅ በጣም ብዙ ደቂቃዎች ሳልወስድ አልቀረሁም፡፡ ክፉው መንፈስ የሚለፈልፈውን ሲሰሙ የነበሩ በጣም ብዙ ሰዎች እንደ ትንግርት ሲመለከቱኝ ቆዩ፡፡ የቅብዐ ቅዱስ ጸሎቱም ላይ ተመሳሳይ ሁኔታ ነበር፡፡ መነኩሴው ለበርካታ ደቂቃዎች ሲጸልዩልኝ ቆይተው ወደ ሕሊናዬ ስመለስ እንደ እንፋሎት ያለ ነገር ከወደ ጭንቅላቴ ተኖ ሲወጣ ተሰምቶኛል፡፡ ለካስ ያቺ ቅጽበት ክፉው መንፈስ ጮሆ ምሎና ተገዝቶ ለቅቄያለሁ ያለበት ነበር፡፡ በአስታማሚዎቼና በበርካታ ሰዎች ታጅቤ ወደተከራየነው ቤት ስንሄድ ሰውነቴ ለራሴ ቅልል ብሎኝ መሬቱን ሳልረግጥ በአየር ላይ እየተንሳፈፍኩ የምሄድ ነበር የሚመስለኝ፡፡ ውስጤን የሚፈነቅል እጅግም የሚያስፈነድቅ ደስታ ውጦኛል፡፡ ሌላ ነገር ይመስላቸዋል ብዬና አፍሬ እንጂ ዙሪያውን ብሮጥ፣ ቤተክርስቲያኑ ግቢ ውስጥ ባለው መሬት ላይ ብንከባለል፣ እየጮህኩ ደስታዬን ብገልጥ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ለወራት ማጅራቴን ይጨመድደኝና ትከሻዬን ይከብደኝ የነበረው ነገር ጠፍቶ መላ ሰውነቴ የላባ ያህል የቀለለ መስሎ ነበር የሚሰማኝ፡፡

ዕለቱን ሲያስታምሙኝ የሰነበቱትን ሁሉ እያቀፍሁ ስስም፣ በደስታ ብዛት ሳለቅስ ውዬ አመሸሁ፡፡ በእማማ አፀደ ውሳኔ ተጨማሪ አንድ ሳምንት እዚያው እንድንቆይ ሆነ፡፡ ሳምንቱን ሙሉ ጸበል መጠመቄን ሳላቋርጥ፣ ጸሎቱንና ቅዳሴውን በብዙ ፍቅር ስሳተፍ ሰነበትኩ፡፡ አንድም ቀን ያልተለየችኝ ታናሽ እህቴ ባየችው ነገር ሁሉ እየተደነቀች ወደ መጨረሻ አካባቢ በጸሎቱ እስከ መሳተፍ ደረሰች፡፡ ከ21 ቀናት የጸበል ቆይታ በኋላ ያን የበረከት ሥፍራ ከተሟላ ጤንነትና ከነፃነቴ ጋር በእምባ ተሰናበትኩት፡፡ እዚያ የተዋወቅናቸውን ሁሉ አመስግኜ ዕቃዎቻችንን ጭነን ጉዞ ወደ መኖሪያ ቤት ሆነ፡፡ እማማ አፀደ እንደዛቱት፣ እንደፎከሩት በድል ተመልሰዋልና በቤታችን ውስጥ ያላቸው ክብር ጨመረ፡፡ እናቴም መግባታችንን ስታይ ግቢውን በእልልታ ቀውጢ አደረገችው፡፡ እኔንም አንቃ ይዛ ስንላቀስ ቆይተን በእማማ አፀደ ተግሳፅ ዝም አልን፡፡ "የምን ለቅሶ ነው ደሞ አሁን? ምሥጋናና እልልታ እንጂ፡፡ የለቅሶው ጊዜማ አለፈ፣ የእኔ መድኃኔዓለም ምን ይሳነዋል" አሉና ምሳ እየተበላ ስንጫወት ቆየን፡፡ አባቴ ከሁለት ሰዎች ጋር መጥቶ አቅፎ ራሴን ሳመኝ፡፡ እማማ አፀደንና ሲያስታምሙኝ የነበሩትን ሁሉ አደግድጎ ሲያመሰግን ቆየ፡፡ በኋላ ላይ እማማ አፀደ ለመሄድ እየተነሱ "ሐጂ ሁሴን ያው እንግዲህ ልጅዎ፣ መድኃኔዓለም ይመስገን ነፃ ሆናልዎት መጥታለች፡፡ እንግዲህ ይወቁበት... የዘንድሮን ልጅ በፍቅርና በማግባባት እንጂ በኃይል ምንም ልናደርጋቸው አንችልም፡፡ በብርቱ ያስቡበት" ብለው ወደ በሩ አመሩ፡፡ የአባቴን ስሜት ለማጥናት ቀና ስል ዓይኖቹን አጨንቁሮ በሴረኛ አስተያየት ሲመለከታቸው አስተዋልኩት፡፡

                              (ይቀጥላል)

       ----------- ማርያማዊት ገብረመድኅን -----------
saramareyama.890@gmail.com

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የምዕራፍ አምስት(፭)የ46 የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ

✝በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡ አሜን! ↪️የምዕራፍ አምስት(፭) 46ኛ ዙር የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ⤵️ 1⃣ ቅዱስ ያሬድ ከመላዕክት የተማራቸው ሦስቱ የዜማ ዓይነቶች ምን ምን ናቸው?ሞገር...