#አፊያ #ሁሴን ክፍል 7
#ፀሀፊ #ማርያማዊት ገብረ መድሕን
#አንባቢ #ገብረ ሚካኤል
አፊያ ሁሴን (ክፍል ፯)
አሁንም ለተወሰኑ ደቂቃዎች ፀጥ አልኩ፡፡ በፀጥታዬ ውስጥ ግን ብዙ ነገሮች ተመላለሱ፡፡ ስለ ራሴ አሰብኩ፣ ውስጤ ተቀይዶ ስለተያዘበት ነፍሴንና ሥጋዬን ስለተቆጣጠረው የውዝግቦች ሁሉ መነሻ ስለሆነው ሃሳቤ አውጠነጠንኩ፣ ስለ ቀጣዩ ሕይወቴና ዕድል ፈንታዬ አወጣሁ አወረድኩ፣ ደግሞም ስለ ውጫዊና በዙሪያዬ ስላለው ነገር ሁሉ፣ ስለ ቤተሰቦቼ፣ ስለ አባቴ፣ በፊቴ ተቀምጦ "ላገባሽ እፈልጋለሁ" በማለት በመቅለስለስ ላይ ስላለው ሁመይድ አሰብኩ፡፡ አሁን ጋብቻን አስመልክቶ በውስጤ የሚሰማኝን ስሜትም ቃኘሁት፡፡ ነገሩ በማላውቀው ምክንያት ፈገግ አሰኘኝ፡፡ ራሴን ትዳር ውስጥ በመዶል ያሰብኩበት የቅርብ ጊዜ ምናብ የለኝም፡፡ ወጣት ብሆንም እንኳ ገና ሕጻን እንደሆንኩ ሳይሰማኝ አልቀረም፡፡ በዚያ ላይ ጋብቻን በእናቴና ባየኋቸው ሙስሊም ሚስቶች ስመዝነው ስለኖርኩ ለእስላማዊ ጋብቻ የሚሰቀጥጥ ግንዛቤ ማዳበር ከጀመርኩ ቆይቻለሁ፡፡ እናም ድንገት እንዲህ ያለው የጋብቻ ጥያቄ ከአንድ ቱጃር ሙስሊም ሲቀርብልኝ ፈገግ ማለቴ የሚገርም አልነበረም፡፡ ሁመይድ ግን ፈገግታዬን የአዎንታዊ ምላሽ ምልክት አድርጎ ወሰደውና ክልስ ፊቱ በፈግታ ባህር ተጥለቀለቀ፡፡ ትኩር ብዬ አየሁትና "የእኔና የዚህ ሰው ስነ-ልቡና፣ የነገሮች ምልከታና ግንዛቤ ምን ያህል ይራራቅ ይሆን?" ስል አሰብኩ፡፡ በደስታውና በተሳሳተ ትርጉሙ ረዥም ርቀት እንዳይጓዝ አልኩና "ይኸውልህ ሁመይድ" አልኩት ቅጭም ለማለት እየሞከርኩ፡፡ "ይኸውልህ ሁመይድ..እኔ አንተን በጣም ነው የማከብርህ፣ ባለውለታዬም ጭምር ነህ፡፡ ከፋይሰል (ታላቅ ወንድሜ) ምንም የማልለይህም ሰው ነህ፡፡ ስለ ጥያቄህም በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ነገር ግን እኔ አሁን ባለሁበት ሁኔታ እንኳን ስለ ትዳር ላስብ የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር እንኳን ዝግጁ አይደለሁም፡፡ ውስጤ ለእንዲህ ያለው ነገር መነቃቃቱ እንኳ የለም... መነቃቃት...ይገባሃል የምለው" አልኩት የምለውን ነገር ለመረዳቱ እየተጠራጠርኩ፡፡
እርሱ ግን አማርኛ በንግግር ያደናቅፈው እንጂ ለመስማት ሲሆን የሚያመልጠው ቃል አልነበረም፡፡ ስለሆነም ነገሩ እንደገባው ራሱን በአዎንታ እየነቀነቀ አሳየ፡፡ ከያዘውም መጠጥ ጎንጨት አለና "ይገባል ኤፊ ይገባል" አለ፣ እንግዲህ ሃሳብሽ ይገባኛል ማለቱ ነበር፡፡ ይበልጥ እንድረዳው አልፎ አልፎ እንግሊዝኛም እየተጠቀመ በዕድሜ ለአካለ መጠን አልደረስኩም ለማለት ፈልጌ ሳይሆን በተለያዩ ውስጣዊ ሃሳቦቼና በራሴ ችግሮች ምክንያት አሁን ለትዳር መነሳሳቱ እንደሌለኝና በስነ ልቡናም ዝግጁ እንዳልሆንኩ መናገሬን መልሶ ተረከልኝ፡፡ እንደ እኔ ሥጋት ሳይሆን ያልኩትን በደንብ ከመረዳት አልፎ አፍታቶም መናገሩ አስደነቀኝ፡፡ ይበልጥ ይግረምሽ ብሎ ነው መሰል "እንደዚህ እንደሚሰማሽና ይህንኑ መልስ እንደምትሰጪኝም አውቅ ነበር" አለኝ ፈገግ እንዳለ፡፡ በቀላሉ ስለተረዳኝ ደስ እያለኝ "እንዴት?" ብዬ ጠየኩት፡፡ እርሱም "ምክንያቱም በደንብ አጥንቼሻለሁ፣ በጣም ስለወደድኩሽ ብዙ ነገርሽን ሳጠና ነበር፡፡ ቀልብሽን ለመሳብ እንኳ የማደርገውን ብዙ ጥረት ከጉዳይ እንደማትፅፊያቸው አስተውያለሁ፡፡ እናም እንዲህ እንደምትመልሺ ገምቼ ነበር" አለ፡፡ ቀጠል አርጎም "ግን ኤፊ..ልክ ነሽ፣ ሁሉም ነገር ልክ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ በውስጥሽ ያጣሽው ስሜት የሚነቃቃበት የሆነ (turning point) መነሻ ነጥብ ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ነጥብ ዛሬ ቢሆን በግሌ ደስ ይለኛል፡፡ ለእኔ አይደለም፣ ለራሴ ላመቻችሽ ፈልጌ አይደለም፡፡ በእርግጥ የእኔ ብትሆኚ ደስታውን አልችለውም፡፡ ይሁን እንጂ ይህን የምለው ከሁሉ በፊት ለራስሽ ነው፡፡ ወጣት ነሽ፣ ቆንጆ ነሽ፣ እንዲህ ያለውን ስሜት የምታጣጥሚበት፣ የወደፊት የትዳር አጋርሽን የምትመርጭበት፣ ቀጣዩን ሕይወትሽን የምትተልሚበት ትክክለኛው ጊዜ ላይ ነሽ፡፡ ይህን ስሜት በአግባቡ ማስተናገድ ጤናማነትና የተፈጥሮን ሥጦታ አለመጋፋት ጭምር ነው" አለኝ፡፡
በስሱም ቢሆን "ይህ ሰው ምሑርነትም ይቃጣዋል እንዴ?" ስል እንዳስብ አደረገኝ፡፡ ሙስሊም ቢሆንም እንኳ ብዙ ሀገር መዞሩና የሚከተለው አውሮፓዊ የአኗኗር ዘይቤ እንደዚህ አስተሳሰቡን ሳይቀርፀው አልቀረም፡፡ ለሰጠኝ አስተያየት ማመስገን እንዳለብኝ ተሰማኝና "አመሰግናለሁ ሁመይድ፣ ያልጠበኩትና የሚገርም አስተሳሰብ ነው ያለህ" አልኩት፡፡ ከዚያም ፈራ ተባ እያልኩ "ግን..." ብዬ አየሁት፡፡ ሃሳቤ እንደገባው በሚያስታውቅ ሁኔታ "ጠይቂኝ..ጠይቂኝ፣ የፈለግሽውን ጠይቂኝ" አለ እጁን በሚጋብዝ ሁኔታ እያርገፈገፈ፡፡ እኔም "እስካሁን አላገባህም እንዴ?" ስል ጠየኩት፡፡ ቤታችን በጨዋታ በሚያመሽባቸው ጊዜያት ስለዞረባቸው ሀገሮች እያነሳ ፓስፖርቱ ላይ የተመታለትን ቪዛዎች ብዛት ሲያሳየን እንደዋዛ የትውልድ ዘመኑን ተመልክቼው ነበር፡፡ እናም ምቾት ያልተለየው አኗኗሩ የ30 ዓመት ወጣት ያስመስለው እንጂ ዕድሜው አርባዎቹ አጋማሽ ላይ እንደሚገኝ አውቃለሁ፡፡ እርሱ ግን አሁንም የሚጠብቀውን ጥያቄ እንደጠየኩት ከፈገግታ ጋር ተናገረና እንዲህ ሲል ቀጠለ "አባቴ ገና በአፍላ ወጣትነቴ በ16 ዓመቴ ነው በአውሮፕላን አደጋ የሞተው፡፡ እናም በዚያ ዕድሜዬ ከወንድሞቼ ጋር ተካፍዬ የደረሰኝ ሀብት በጣም ብዙ ነበር፡፡ በእናት በኩል ወንድም፣ እህት ወይም ዘመድ ስላልነበረኝ ብቸኝነት ይሰማኝ ነበር፡፡ ያለኝን ሀብት የተገነዘቡ ብዙ ሰዎች በተለያየ ነገር ላይ ኢንቨስት እንዳደርግ፣ አክሲዮኖች እንድገዛ፣ አብሬያቸው እንድሰራ ያግባቡኝ ነበር፡፡ የአረቡ ዓለም ስነ-ልቡና ተካፋይ በመሆኔ በሥራም፣ በሥልጣኔም የተሻሉ እንደሆኑ አድርጌ የማስባቸውን አውሮፓውያን ምርጫዬ አደረግሁ፡፡ በእርግጥ እድለኛም ነበርኩ፡፡ ከእንግሊዞች ጋር ተቆራኝቼ መስራት ጀመርኩ፡፡ እነርሱም ከእኔ የሚጠቀሙት ብዙ ነው፡፡ ነገር ግን የጥቅማቸውን ያህል ብዙ ነገር አስተማሩኝ፡፡ አስተዳደርን፣ የሥራ ዲሲፕሊንን፣ ቋንቋን፣ አዋጭ የሥራ ዘርፍ አመራረጥን...በጣም ብዙ ነገር ከእነርሱ ተማርኩ፡፡ ከአሜሪካ እስከ ጃፓን ብዙ ሀገር ተዟዟርኩ፡፡ በኮርስፖንደንስ የሚሰጡ የተለያዩ ትምህርቶችን ተማርኩ፡፡ በዕድሜ እየበሰልኩ በሄድኩ ቁጥር በልምድ ያካበትኩት ትምህርት እየጠቀመኝ መጣ፡፡ በተለያዩ የንግድና የማምረቻ ሴክተሮች በመሳተፍ ስኬታማ ሆንኩ፡፡ ከአውሮፓውያኑ ንግድና ሥራ፣ አስተዳደርና የሥራ ስነ-ምግባር ብቻ አልነበረም የተማርኩት፡፡ የአኗኗር ዘይቤያቸውን ጭምር ወሰድኩ፡፡ በእርግጥ የእነርሱ ዘይቤ በጣም የወጣና መጠን ያለፈ ነው፡፡ የእስልምናው በተለይ የአረቡ ዓለም ደግሞ በጣም የታሰረና ለጭቆና የቀረበ ነው፡፡ በእኔ እምነት ልከኛውና አማካዩ የአኗኗር ዘይቤ ያለው እዚህ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ይህን የተረዳሁት ግን በጣም ዘግይቼ ነው፡፡ እናም ገንዘብና ወጣትነት ብዙ አባለጉኝ፡፡ ብዙ ነገር አሳልፌያለሁ፣ በእስልምናም በክርስትናም የማይፈቀዱ በርካታ ተግባራትን ፈፅሜያለሁ፡፡ እርግጥ አሁን አሁን ይፀፅተኝ ጀምሯል፡፡ ሁሉን ነገር ማየት ሁሉ ነገር ባዶ መስሎ እንዲታይሽ ያደርጋል፡፡ ገንዘብ ስላለኝ በማንኛውም ጊዜ ማግባት እንደምችል እያሰብኩ ስንዘላዘል አረፈድኩ፡፡ አንድ ሁለቴ ለማግባት ሞክሬ ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ እነርሱን ስፈልግ እነርሱ ደግሞ ገንዘቤን የሚፈልጉ ነበሩ የገጠሙኝ፡፡ በጣም ብዙ ሴቶች አሉ፣ ሚስት ግን የለም፡፡ አሁን በጣም ስለተሰላቸሁ ማረፍ፣ መረጋጋት፣ መስከን እፈልጋለሁ፡፡ የራሴ የምለው ቤተሰብ እንዲኖረኝ እሻለሁ፡፡ ከፍተኛ የሆነ ብቸኝነት ይሰማኛል፡፡ የሚከበኝ ሰው ብዙ ነው፣ ነገር ግን ሁሉ አንድ ነገር ከእኔ ፈልገው የሚመጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ ጓደኛ ወይም የሥራ አጋር እንጂ ቤተሰብ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ እኔ ብዙ ጓደኛና አጋር አለኝ፡፡ ቤተሰብ ግን የለኝም፡፡ እናንተ ቤት ማታ ማታ መጥቼ የማመሸው በጥቂቱም ቢሆን ይህን ጥማቴን ለመቁረጥ ነው፡፡ አንቺ ብቻ ሳትሆኚ ፋይሰል፣ ሰዓዳ፣ ሙኒር፣ ሐጂና እማማ ሳይቀር የሆነ ትናንሽ ክፍተቶቼን የሚሞሉልኝ ይመስለኛል፡፡ አንቺ ከማውቃቸው ሴቶች ሁሉ የተለየሽ ነሽ፣ የእኔ ሚስት ብትሆኚ እንዴት ያለ ገነት የሆነ ሕይወት እንደሚኖረኝ፣ እንዴት ዓይነት ድንቅ ቤተሰብ እንደምመሰርት ሳስበው..." አለና ትክዝ አለ፡፡ እንደገና ቀና አለና "ይቅርታ ኤፊ ስሜታዊ ሆንኩብሽ፡፡ ብቻ አሁን የተረዳሁት ነገር የገንዘብ ብዛት ብዙ ሴቶች ያመጣ ይሆናል እንጂ ሚስት ግን እንደማያመጣ ነው፡፡ ለአንቺ አንዳንድ ነገር ሳደርግልሽ ምንም ግድ አይሰጥሽም፣ ጭራሽ እንደውም የሚያበሳጭሽ ነው የሚመስለኝ፣ ባደረኩልሽ ነገር የምትጨምሪልኝ ፊት የለም፡፡ ይሄን ሁሉ ሳይ ይበልጥ እየወደድኩሽ መጣሁ፡፡ የእኔ ትክክለኛ ሚስት አፊያ ናት እያልኩ ለውስጤ ደጋግሜ ስነግረው ቆይቻለሁ፡፡ ሆኖም ግን ፈጣሪ አንቺን ካልሰጠኝ በቀር በራሴ የእኔ ላደርግሽ እንደማልችል አውቄያለሁ" አለና በመስኮቱ አሻግሮ መመልከት ጀመረ፡፡
ለምን እንደሆነ ባላውቅም አሳዘነኝ፡፡ እኛ ቤት በሚመጣበት ሰዓት እንዲህ ያለውን ትልቅ ክፍተት ይዞ እንደሚመጣ አላውቅም ነበር፡፡ እንዳለው በሚያደርጋቸው አንዳንድ ነገሮች አልፎ አልፎም ቢሆን እሰላች ነበር፡፡ ሲያዩት የሀዘንና የመከፋት ፍንጥርጣሪውም የሚነካው አይመስልም፡፡ ነገር ግን ሰው ካላወራ በቀር ለካ ውስጡ አይታወቅም፣ ሆድ እንዴት ያለ ከሀገር የሚሰፋ ነገር ነው ስል በሃሳቤ እንደመፈላሰፍ ቃጣኝ፡፡ ብቻ እንጃ ዝም ማለት እንደማይገባኝ ተሰማኝና "አይዞን ሁመይድ ጌታ ለአንተ ያላትን፣ የግራ ጎንህን ከየትም ቢሆን ያመጣታል፡፡ ሰጪው ፈጣሪ ነው ብለህ የለ? ጠብቀው፡፡ እርሱ ቢዘገይም ለጥቅም ነው፣ ደግሞም ዘግይቶ ተነስቶ ቀድሞ የሚደርስ ጌታ ነው" አልኩና ላበረታታው ብዬ በወዳጅነት ስሜት በሁለት እጆቼ ጠረጴዛው ላይ ያሉትን እጆቹን ያዝኩት፡፡ በድንገት ብድግ ብሎ ሁለት እጆቼን እያፈራረቀ ሳመና "አመሰግናለሁ ኤፊ..ስለሰማሽኝ ራሱ ከልብ አመሰግናለሁ" አለና ተቀመጠ፡፡ አሁን ቢበቃንና ወደ ቤት ብንሄድ የተሻለ ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ በር በር እያየሁ እንደ መቁነጥነጥ ሲያረገኝ አስተዋለና "እንሂድ ኤፊ...?" ሲል ጠየቀኝ፡፡ አዎም አይም ማለቱ ችግር ሆነብኝና ስንተባተብ ያስተናገደንን ወጣት ቢል እንዲያመጣለት ጠቀሰው፡፡ ሂሳብ ከፋፍሎ ከመነሳታችን በፊት የማጠቃለያ የሚመስል ነገር ተናገረ፡፡ ከፊቱ ይልቅ ኋለኛው ይብሳል እንደሚባለው ይህን ንግግሩን ፈፅሞ ከውስጤ ማውጣት ተሳነኝ፡፡ ሲናገር እጄን ለመያዝ ጥረት አድርጎ የነበረ ቢሆንም እንዳላስተዋልኩ አስመስዬ እጄን ወደ ራሴ ሸሸት አደረግሁ፡፡ እርሱ ግን ቀጠለ..
"ኤፊ..በውስጥሽ የማግባት ፍላጎት ከተቀሰቀሰ፣ ሰው ያስፈልገኛል ብለሽ ካመንሽ ለፈጣሪ ብለሽ አስቢኝ፡፡ አንቺ ራስሽን ለእኔ ብትሰጪ ቤት እገዛለሁ፣ መኪና እሰጣለሁ፣ ሱቅ እከፍታለሁ አልልሽም፡፡ ይሄ ለአንቺ አይደለም ለአንድ የቅርብ ጓደኛ ላደርገው የምችለው ነገር ነው፡፡ ለአንቺ የምሰጥሽ የሕሊና ነፃነት ነው፡፡ አስበሽዋል ኤፊ አንቺ እዚህ እስካለሽ ድረስ በሐጂ ቁጥጥርና በቤተሰብ ተፅዕኖ ውስጥ ነሽ፡፡ ስለዚህ እንደፈለግሽ መሆን አትችይም፡፡ ባለፉት ወራት የሆነውን ተመልከች፡፡ ከአንቺ ሕመም እስከ ሐጂ ሕመም ስንት ምስቅልቅል ተፈጠረ? ይህ ሕይወት መቼ የሚያበቃ ይመስልሻል? ቀጣዩ ሕይወትሽንስ እንዴት ነው የምትመሪው? ባል ብታገቢ ግን የአንቺ ዋና ተጠሪ እርሱ ነው፡፡ የሐጂ ዓይነት ሰው ካገባሽ ይኸው ሕይወትሽ ይቀጥላል፡፡ ሌላ የፈለኩትን አገባለሁ ካልሽ ምናልባት የፈለግሽውን ነፃ ሕሊና ታገኚ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለውን ሰው ለማግባት የምትሻገሪያቸውን ድልድዮች አስቢያቸው፡፡ ክርስቲያን ባል ብታገቢ ሐጂ ምን የሚሆኑ ይመስልሻል? የአሁኑ ሁኔታ በአንቺ የተነሳ እንዲደገም ትፈቅጃለሽ?? ለሐጂና ለተቃዋሚዎችሽ ሁሉ ምንም ዓይነት ሃላፊነት የማይሰማሽ ሆነሽ በጭካኔ መገለጡ ይሆንልሻል? እንጃ.! ከአንቺ ተፈጥሮ ጋር የሚሄድ አይመስለኝም፡፡ እኔ ግን በማንም ዘንድ የምታወቀው በሙስሊምነቴ ነው፡፡ እኔን ብታገቢኝ ከሐጂ ጋር ፀብና የሚፈራው ነገር ቀርቶ መርቀው የሚሸኙሽ ነው የሚመስለኝ፡፡ ቀሪውም ቤተሰብ ደስተኛ ይሆናል፣ የተፈጠሩ ልዩነቶች ይጠፋሉ፡፡ በአንፃሩ እኔ ግን በሕሊና ነፃነትሽ ላይ ፈፅሞ ጣልቃ አልገባም፡፡ ከፈለግሽ ሰርጋችን በእስላማዊ ሥርዓት ሳይሆን በሀገር ወግና ልማድ ይሆናል፡፡ ክርስቲያን የመሆን ፍላጎት ካለሽ፣ ትምህርታቸውን መማር ካሰኘሽ ነፃ ነሽ፡፡ that is no my business. በእርግጥ እኔ ዜግነቴ ኢምሬት ሃይማኖቴም እስልምና ነው፡፡ ነገር ግን በሁለቱም አልኖርኩበትም፡፡ የማደላው ለኢትዮጵያዊ ዘሬ ነው፣ ስለ እስልምናም ብዙ አላውቅም፡፡ አኗኗሬን እንደምታዪው ምዕራባዊ ነው፡፡ ስለሆነም በሃሳብ ነፃነት ስለማምን ከሕሊናዊ ችግሮችሽ ነፃ አደርግሻለሁ፡፡ በእርግጥ እኔ ክርስቲያን እሆናለሁ ብዬ አሁን ቃል አልገባም፡፡ ነገር ግን የወደፊቱን አላውቅም፡፡ አንቺን ያሸነፈ፣ መሰረትሽን የነቀለ መንፈስ ካገኘኝ ያኔ የማየው ነገር ይሆናል፡፡ አሁን የማውቀው ግን አንቺን በእንዲህ ያለ ነገር ልጋፋሽ ይቅርና አነስተኛ እንቅፋት እንኳን እንደማልሆንብሽ ነው፡፡ እኔ የምፈልገው ሚስቴ እንድትሆኝ፣ ከአንቺ ጋር ቤተሰብ እንድመሰርት ብቻ ነው"
የሚናገረውን ነገር እንደጨረሰ ምንም አስተያየት ሳልሰጥ ከመቀመጫዬ ተነሳሁ፡፡ እርሱም ተነሳና ወደ መኪናው አመራን፡፡ የመኪናውን በር እየከፈተ "የት ነው የማደርስሽ ኤፊ? ቤት ነው ወይስ ሲስተር ጋር?" አለኝ፡፡ ትንሽ ግራ ተጋባሁና "እታባ ጋር" ብዬ ያልታሰበበት መልስ ሰጠሁት፡፡ ረዥሙን መንገድ ብዙም ሳንነጋገር ተያያዝነው፡፡ አልፎ አልፎ ብቻ መንገድ ላይ በሚገጥመን ነገር እየተንተራሰ አንዳንድ ቃላት ይወረውራል፡፡ እኔም እንደ ምንም ፈገግ በማለት ወይም ቃል አልባ ድምፅ በማውጣት ምላሽ ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡ በቀረው ግን ሁለታችንም የየራሳችንን ሃሳብ ስናመነዥግ እህቴ ቤት ደረስን፡፡ ስለ ግብዣው አመስግኜው ተሰነባበትን፡፡ ከመኪናው ወርጄ መንገድ ስጀምር "ኤፊ" ብሎ ጠራኝ፡፡ መለስ ብዬ በመስኮቱ በኩል ጠጋ ስል " እባክሽ ኤፊ አስከፍቼሽ ከሆነ ይቅርታ አርጊልኝ" አለኝ፡፡ የመኪና ውስጥ ዝምታዬ እንዳስጨነቀው ያስታውቃል፡፡ ነገሩን ቀለል ለማድረግ እየጣርኩ "ኧረ የምን ማስከፋት.. ምን አደረከኝ? የተሰማህን ነው የነገርከኝ" አልኩና በስሱ ፈገግ ብዬ "አትጨነቅ" አልኩትና የግቢውን በር ማንኳኳት ጀመርኩ፡፡ እርሱም መኪናውን አዙሮ አቆመና ቤት መግባቴን ለማረጋገጥ በሚመስል መልኩ ቆም አለ፡፡ በሩ ሲከፈትልኝ አይቶ የግራ እጁን ለሰላምታ በመስኮቱ በኩል ከፍ አደረገና በመጣበት መንገድ ተፈተለከ፡፡
አባቴ ለ15 ቀናት ያህል እኛ ቤት እንደማይመጣ ግምታዊ ስሌት ወስጄ ነበር፡፡ ቢያንስ ሁለቱ ሚስቶቹ ጋር አንድ አንድ ሳምንት ይቆያል፡፡ ከራሴ ጋር ተማክሬ እርሱ እስኪመጣ ድረስ እህቴ ቤት ለመቆየት ወሰንኩ፡፡ የእህቴ ቤት ለማሰብም፣ ለንባብም፣ አንዳንድ ቦታ ወጣ ለማለትም የተሻለ ነፃነት ይሰጣል፡፡ ለጨዋታም ቢሆን ክፉና ደጉን ከማያውቁ የእህቴ ልጆች ጋር መዳረቁ የተሻለ ነው፡፡ ከእነርሱ ጋር መዋል ልክ ከተፈጥሮ ጋር የመጫወት ያህል ነው፡፡ አንድን ዛፍ ቅጠሉን ብትቆርጪው ለምን ቆረጥሽኝ አይልሽም፣ ወደ አንድ ፏፏቴም ድንጋይ ብትወረውሪ እንዴት ተደፈርኩ አይልም፣ በዙሪያሽ ያለው መልክዓ ምድር በራስሽ ስሜትና ሃሳብ ሥጋትና ተሥፋ ብትዋጪ "ምን ሆንሽ? ለምን? እንዴት?" እያለ በጥያቄ ብዛት አይነተርክሽም፡፡ ሕጻናትም እንዲሁ ናቸው፡፡ ለእነርሱ ሰው መሆንሽ ብቻ በቂ ነው፡፡ ከራሳቸው ደመ ነፍሳዊ ስሜትና ፍፁም ከሆነው ቅንነታቸው ጋር ያዋሩሻል፣ ያሳስቁሻል፣ ይላፉሻል፡፡ ከእነርሱ ጋር ስትሆኚ "ይቀየሙኛል፣ ምን ይሉኛል፣ በዚህ መንገድ ይተረጉሙብኛል" ከሚል የአዋቂዎች ሥጋትና ጥንቃቄ ሁሉ ነፃ ነሽ፡፡ ስለዚህም እዚያ መሰንበቴን ወድጄው ነበር፡፡ በዚያ ላይ ሁለት ጊዜ ያህል የተፈወስኩበት ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ሄጃለሁ፡፡ በአቅራቢያው ባሉ ቤተክርስቲያኖችም አልፎ አልፎ ጎራ ለማለትም ዕድል ሰጥቶኛል፡፡ አሁን በቅርቡ ወደ ወላጆቼ ቤት መመለሴ ስለማይቀርና ደግሞም ሰቅዞ ስለያዘኝ ሃሳብ ለመፀለይ ለሦሥተኛ ጊዜ ወደ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን የመሄድ ሃሳብ ወደ አዕምሮዬ ገባ፡፡ የአባቴን ከሆስፒታል መውጣት ተከትሎ አሁን እህቴ ቤት መዋል ስለጀመረች እንደ ልብ መውጣት ትንሽ ይቸግራል፡፡ ቢሆንም እርሷን እንደ አባቴ የማየትም ሆነ የመፍራት ልማዱም ተገቢነቱም ስለሌለኝ አንድ ቀን ጠዋት ደፈር ብዬ ለመውጣት ተነሳሁ፡፡ ገና በማለዳ ስዘገጃጅ አይታ "የት ልትሄጂ ነው?" ብላ ጠየቀችኝ፡፡ "አንድ ቦታ ደርሼ እመጣለሁ" አልኳት እየሳቅሁ፡፡ "ከምሬ ነው የት ልትሄጂ ነው?" አለች ኮስተር ብላ፡፡ "እሺ ሐጂ ሁሴን..እርሶም የመዘዋወር ማዕቀብ ሊጥሉብኝ ነው?" ብያት ወደ በሩ ሳመራ ቁርጥ መሆኑን ተረዳችና ከተል እያለችኝ "እሺ ኤፊ ራስሽን ጠብቂ..ደግሞ ቶሎ ተመለሽ" ብላ ወደ ልጆቿ ተመለሰች፡፡
ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ስሄድ የሚሰማኝን ስሜት ሳስበው በጣም ነው የሚገርመኝ፡፡ ለወግ እንኳን የማይመች በጣም የሚያስደንቅ መንፈስ ይከበኛል፡፡ ያውም እኔ እንደ ሌላው ሰው ረዥም ጸሎት አላደርግም፡፡ የሰዉን ጎንበስ ቀና፣ ተመስጦና ጸሎት እያየሁ እቀናለሁ እንጂ፡፡ ጸሎት ለማድረግ ስቆም ከጸሎቴ ጋር ቀጠሮ ያላቸው ይመስል እንባዬ በምን ፍጥነት ከች እንደሚል ይገርመኛል፡፡ እናም ብዙ ነገሮቼን እያሰብኩ እንባዬን ከማፍሰስ በቀር በቃላት የተሰካካ ጸሎት ማድረግ አይሆንልኝም፡፡ ብቻ ከለቅሶዬ ጋር እራሴንና የእኔ የሆኑ ነገሮችን አስባቸዋለሁ፡፡ በቃ ጸሎት ማለት ለእኔ ይሄ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ረዥም ሰዓት እዚያው ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ አንዱ ጥግ ላይ ቁጭ እላለሁ፡፡ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ያሉ ዛፎች በንፋስ ኃይል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ የአዕዋፋቱ መመላለስ፣ የተሳላሚዎች መግባትና መውጣት፣ ሌላም ጥቃቅኑ ነገር ሁሉ ትርጉም ያለው፣ በሥልት የሚንቀሳቀስ፣ በምሥጢራዊ ተልዕኮ የታጀበ መስሎ ነው የሚሰማኝ፡፡ የግቢው ጸጥታ ራሱ ከባዶ ቤት ጸጥታ በሥንት ሺህ እጥፍ የሚበልጥ ረቂቅ ትርጉም እንዳለው በእኔ ሕይወትና መንፈስ ውስጥ ያልገባ ሰው ፈፅሞ ሊገነዘበው አይችልም፡፡ እንዲህ በተፈጥሮና ብዙ ሰው በማያስተውለው ነገር ስደነቅ ልቤ በማላውቀው የደስታ ስሜት ሲሞላ ገፅታዬም ይህንኑ የሚያንፀባርቅ ብሩኅነትን ይላበሳል፡፡ ችግር የሚፈጠረው ስለ ራሴ፣ ወደ ወላጆቼ ቤት ስመለስ ስለሚሆነው ቀጣይ ነገርና አጠቃላይ ስለ ወደፊት ዕጣዬ ማሰብ ስጀምር ነው፡፡ ሁመይድ ደግሞ እግዚአብሔር ይስጠውና አንድ ትልቅ ሐሳብ ጨምሮልኛል፡፡ "ይህ ነገር መቼና እንዴት ነው የሚያበቃው?" የሚል፡፡
ይህን የመፃኢው ዕጣዬ ጥያቄ ሁመይድ ካነሳልኝ ቀን ጀምሮ ፦ሌሊትና ቀን ሲያብሰለስለኝ ቆይቷል፡፡ አሁን አባቴ ጤናው ይበልጥ እየተሻሻለ በመሄዱ ቤተሰባዊ መስተጋብራችን እንደ ወትሮው መቀጠሉ አይቀርም፡፡ የእኔና የአባቴን ድብብቆሽ ገና ሳስበው ድክም ይለኝ ጀምሯል፡፡ በዚያ ላይ ሁልጊዜ ለቤተሰባዊ ትርምስ ምክንያት መሆን ሲበዛ ደስ የማይል ስሜት ይፈጥራል፡፡ እህቶቼ፣ ወንድሞቼና እናቴ ባስተሳሰረን ሥጋ የተነሳ ያዝኑልኝ ይሆናል እንጂ ውስጣዊ ነገሬን አይረዱትም፡፡ የእነርሱም ሀዘኔታ በእኔ ጽናትና ጠንክሬ በመጋፈጤ ምክንያት የምከፍለውን መሥዋዕትነት ተከትሎ የሚመጣ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን ከአባቴ ቁጣ፣ ከማያወላውል አቋሙና በዙሪያው ካለው ግዙፍ ተፅዕኖ የሚበልጥም የሚያስጥልም አልነበረም፡፡ ቆራጥነት የተሞላባቸውና ልወስዳቸው የምችላቸውን ግላዊ ውሳኔዎችን ተራ በተራ አሰብኳቸው፡፡ ሁሉም ዋስትናቸው በፈጣሪ እጅ የተያዙ ከመሆናቸው ባሻገር መላ ቤተሰቤን የሚያሳዝኑ፣ የአባቴን ሕይወት፣ ክብርና ስም አደጋ ላይ የሚጥሉ ነበሩ፡፡ ሁመይድ ያቀረበልኝን አማራጭም አጤንኩት፡፡ አማራጩ የራስን አጀንዳ ከማሳካት ጋር የተያያዘ ቢሆንም ሊወስደው የተዘጋጀውን ሃላፊነት አስቤ እንደ መደነቅም እንደ ማድነቅም አደረገኝ፡፡ ነገር ግን እኔ ለትዳር የተዘጋጀሁ ሰው አይደለሁም፡፡ ሃላፊነቱንም ለመቀበል ብቁ ለመሆኔ እርግጠኛ አልነበርኩም፡፡ ከሁሉ በላይ የትዳር መሥፈርቶች አድርጌ በሕሊናዬ የሳልኳቸውን ነገሮች ሩቡን እንኳ ከሁመይድ አላገኝም፡፡ ስለሆነም መፍትሄ አልባ ሕይወቴ ከእነ ውዝግቡ ይቀጥላል ማለት ነው ብዬ እንደመተከዝ ሲያደርገኝ አንድ ሃሳብ ብልጭ አለልኝ፡፡ እማማ አፀደ፡፡ "ለምን እማማ አፀደን አላማክርም?" ስል አሰብኩ፡፡ ሌላም ጊዜ አንዳንድ ነገር የማማክራቸው እርሳቸውን ነው፡፡ ብዙ ከመቀመጤ የተነሳ ድካም ሁሉ ተሰማኝ፡፡ የመጣልኝ ሃሳብ እንግዳ ባይሆንም ከቤተክርስቲያን አወጣጤን አሳመረልኝ፡፡ ደስታና የመጽናናት መንፈስ ሃሳቤን ተከትሎ በውስጤ ሲሰርፅ ይታወቀኛል፡፡ በረዥሙ ከተነፈስኩ በኋላ ቤተክርስቲያኑን ተሳልሜ ስወጣ ዘጠኝ ሰዓት ሊሆን ምንም አልቀረውም ነበር፡፡
ቤት ስገባ 11፡15 ሆኖ ነበር፡፡ እህቴ "ሙሉ ቀን የት ሄደሽ ነው? በዚያ ላይ ስልክሽን እዚሁ ጥለሽ ነው የሄድሽው፣ ምንድነው እንዲህ ሰው ማስጨነቅ?" ስትል ተነጫነጨችብኝ፡፡ እህቴን አቀፍ እያረኩና ነገሩን ወደ ቀልድ እየቀየርኩ "እታባ...እኔ እኮ ትልቅ ሰው ነኝ፣ ከፈጣሪ ጋር ራሴን መጠበቅ እችላለሁ፡፡ የእህትነትሽን ትንሽ ማሰብ እንጂ መጨነቅ አያስፈልግሽም" አልኳት፡፡ እንዲሁ ስንሳሳቅና አባቴ ሆስፒታል ሳለ የነበሩ በርካታ ገጠመኞችን እያነሳን ስንጫወት አመሸን፡፡ እንደገመትኩት ከ15 ቀናት በኋላ አባቴ እኛ ቤት መጣ፡፡ እናቴ መጠነኛ የሚባል ድግስ አዘጋጀች፡፡ ከዚያ አስፈሪ መሳይ ሕመሙ ከሞላ ጎደል አገግሞ ታሞ ከወጣበት ቤት በመመለሱ ዝግጅቱ ተገቢ ይመስል ነበር፡፡ እኔም ከእህቴና ከባሏ ጋር ወደ ቤታችን መጣሁ፡፡ የተጠሩ ጥቂት እንግዶችና "እንኳን ለቤትዎ አበቃዎ" የሚሉ በርካታ ጎረቤቶች ተገኙ፡፡ ሁመይድም እንደ ቤተኛም እንደ ክብር እንግዳም የሚመስል ሚና ይዞ ከአባቴ ጎን ተኮፍሷል፡፡ አባቴ ከሆስፒታል የወጣ ጊዜ በዚያ ሆቴል ውስጥ ያን ረዥም ውይይት ከተወያየን በኋላ ገና ዛሬ መተያየታችን ነው፡፡ ሌላ ጊዜ ቢሆን ችሎ ከሳምንት በላይ አይቆይም ነበር፡፡ አሁን እንዲህ የጠፋው ባለፈው የሰጠሁት ምላሽ ጠንካራና የማያወላውል ስለሆነ ይሆን ብዬ አሰብኩ፡፡ ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ለመስተንግዶ ገባ ወጣ ስል ለሳምንት ያህል ኬንያና ሲሸልስ የሚባል ሀገር ቆይቶ እንደመጣ ለአባቴ ሲያወራ ጆሮዬ ጥልቅ አለ፡፡
ያ ዕለት ቀለል ባለና ደስ በሚል ሁኔታ ተጠናቀቀ፡፡ ሳምንቱን ሙሉ ከአባቴ ጋር የማሳለፍ ዕድል አገኘሁ፡፡ አባቴም ከቤት ስለማይወጣ ሌሎቹ ወደ ሥራና ሱቆቻችን ሲያመሩ እርሱን የመንከባከቡ ሃላፊነት የእኔ ነበር፡፡ ጠያቂዎች ይበዙ ስለነበር ከአባቴ ጋር ሰፊ ነገር የማውራት ዕድል አልገጠመኝም፡፡ ቢሆንም የሚያሳየኝ ፊት ብሩኅ ከመሆኑም በላይ በየምክንያቱ እየጠራኝ እንግዶች እንዳስተናግድ ስለሚያዘኝ ምንም ቂም እንዳልያዘብኝ እንዲሰማኝ አደረገ፡፡ በእርግጥ በዚህ ጉዳይ የአባቴን ጽንፍ የሚረግጡ ተለዋዋጭ ባህርያት በሚገባ ተለማምጄያቼዋለሁ፡፡ ስለሆነም ነገሮች በቅጽበት ሊለወጡ እንደሚችሉ አልዘነጋም፡፡ ከሳምንቱ መጠናቀቅ በኋላ አባቴ ወደሌላኛው ቤቱ ሄደ፡፡ እንደገና 15 ቀን ቆይቶም ተመለሰ፡፡ በዚህ ሁኔታ ጊዜያትም ቀስ እያሉ ሲያልፉ አባቴ ከሆስፒታል ከወጣ 2 ወራት ተቆጠሩ፡፡ ጤናውም በጣም እየተሻሻለ መጥቶ በከዘራ እየተመረኮዘ መሄድ ቻለ፡፡ ግራ እግሩን በጥቂቱ ጎተት ማድረግና ግራ እጁ እንደ ልብ አልታዘዝ ማለቱ ግን እንዳሉ ነበሩ፡፡ አንድ ቅዳሜ ምሽት ለአነስተኛ ፕሮግራም የሚሆን ዝግጅት ለማድረግ እናቴ እኔና ሰዓዳን ከሰራተኞቻችን ጋር በማዕድ ቤት ሥራ ወጥራን አመሸች፡፡ "ምንድነው?" ስላት "ሐጂ አዘውኝ ነው፣ እንግዶች አሉባቸው" አለችኝ፡፡ እንዲህ ያለው ነገር በቤታችን የተለመደ በመሆኑ ነገሩን ችላ ብዬ ተውኩት፡፡ በማግስቱ ጠዋት ፋይሰል አንድ ቦታ ደርሰን እንድንመጣ ጠየቀኝ፡፡ እንዲህ ያለው ልማድ ከተፈጠረው ችግር ወዲህ አባቴ የከለከለው ነገር በመሆኑ "እህ... አባቴስ፣ እያወቅህ" አልኩት፡፡ እርሱ ግን "እኔ እነግረዋለሁ" ብሎ ወደ ሳሎን ሄዶ ወዲያው ተመለሰና "አላልኩሽም" በሚል ሁኔታ እጆቹን ዘርግቶ ትከሻውን ሰበቀ፡፡ እየተቅለሰለስኩ ወደ ሳሎን ብቅ ስል "ሂዱ ደርሳችሁ ኑ" አለኝ አባቴ፡፡ ፋይሰል ያለ ወትሮው ሲያጣድፈኝ ቆየና ተያይዘን ወጣን፡፡ ልክ እኛ እየወጣን እያለ ሁለት መኪኖች ለእኛ በተከፈተው በር ሲገቡ አየሁ፡፡ የአባቴ እንግዶች ከሰዓት እንደሚመጡ የገመትኩ ቢሆንም ገና በ4፡00 ሰዓት ምን ዓይነት እንግዳ ነው የሚመጣው ብዬ አሰብኩና አንገቴን አጠማዝዤ ተመለከትኩ፡፡ የማታው የእናቴ ሽር ጉድ፣ የአባቴ ከወንድሜ ጋር እንድወጣ መፍቀድ፣ የፋይሰል የማለዳ ጥድፊያ፣ የእንግዶቹ በጠዋት መምጣት የሆነ ለየት ያለ ነገር እንዲሸተኝ አደረገ፡፡
(ይቀጥላል)
------ ማርያማዊት ገብረመድኅን ------
saramareyama.890@gmail.com

ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ