ዓርብ 8 ዲሴምበር 2017

አፊያ ሁሴን (ክፍል ፮)

#አፊያ #ሁሴን ክፍል 6

#ፀሀፊ #ማርያማዊት ገብረመድህን

#አንባቢ #ገብረ #ሚካኤል

አፊያ ሁሴን (ክፍል ፮)

ባልቻ ሆስፒታል እንደደረስን ሐኪሞቹ አባቴን ለማትረፍ እየተረባረቡ ስለነበር እርሱ ወዳለበት ክፍል መግባት አልቻልንም፡፡ ወንድሜ በጭንቀት ይንቆራጠጣል፣ እናቴና እህቴ ያለማቋረጥ ያለቅሳሉ፡፡ እኔ የማደርገውን እንኳ አላስታውስም ብቻ እንባዬ ዝም ብሎ እየፈሰሰ በአንድ ሥፍራ ተገትሬ ቆሜያለሁ፡፡ የኤሌክትሪክ ሰራተኞቹ ሁላችንንም ለማረጋጋት ይጥራሉ፡፡ ሐኪሞችና ነርሶች ግን አባቴ ወዳለበት ክፍል ይገባሉ ይወጣሉ፡፡ "ይህ ሐኪም ቤት ነው ከመጠን በላይ አትጩሁ፣ ሕሙማንን ትረብሻላችሁ" ከሚል የአንዲት ነርስ ተግሳፅ በቀር ሙሉ ትኩረታቸው አባቴ ላይ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ ጊዜው እየጨለመ ቢሄድም እማማ አፀደና ጥቂት ጎሮቤቶች መጡ፡፡ ከትንሽ ቆይታ በኋላ ደግሞ አባቴ ከሌሎች ሚስቶቹ የሚወልዳቸው ልጆቹ ከእናቶቻቸውና ከየጎረቤቶቻቸው ጋር ይግተለተሉ ጀመር፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኮሪደሩ በሰው ብዛት ተጨናነቀ፡፡ ያን ጊዜ ዋናዋ ነርስ ጥበቃዎች አስጠርታ አብዛኛውን ሰው ከፎቁና ከኮሪደሩ ላይ ወርደው ታች መሬት እንዲቆሙ አስደረገች፡፡ አባቴ የታወቀ ደም ግፊት ቢኖርበትም ምን አጋጥሞት ለስትሮክ እንደተጋለጠ በጥያቄ የሚያጣድፉን ሰዎች በዙ፡፡ ሁለቱ የአባቴ ሚስቶች እናቴን ቅንነት በጎደለው ሁኔታ ነገሩን እንድታስረዳ ይወተውቷታል፡፡ እርሷም ከእራሷ ሁኔታ እየተነሳች "እኔ ወጥ ቤት ነበርኩ፣ እርሳቸው ሳሎን ቁጭ ብለው ነበር፣ ሰዓዳ ድንገት ስትጮህ ተከታትለን ስንገባ ሰውነታቸው ተገታትሮ ወድቀዋል" እያለች ለማስረዳት ትጥራለች፡፡ ከልጆቹም አንዳንዶቹ ከታች እየሾለኩ በመምጣት "ምን ሆኖ ለዚህ እንደበቃ፣ ታሞ ከመውደቁ በፊትስ የት እንደዋለ፣ ከማንስ ጋር እንደነበረ" እኔንም ወንድሜንም ይጠይቁናል፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እንደፈራሁት በሌሎቹ ዘንድ አባቴ ለዚህ የበቃው በእኔ ምክንያት እንደሆነ የጋራ ግንዛቤ ተያዘ፡፡ ለካስ ትናንት ምሽት ደውሎ ቀጠሮ ሲያሲዘኝ የሰሙት ልጆች ከመኖራቸውም በተጨማሪ እናቴም ውትወታ ሲበዛባት ቀኑን ከእኔ ጋር ውሎ እንደመጣ ተናግራ ነበር፡፡

ምሽት 4፡00 ሰዓት ሊሆን ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ከሚያድር ሁለት ሰው በቀር ሌላው ወደየቤቱ እንዲመለስ ግዳጅ ሆነ፡፡ ወንድሜና እህቴ እንዲያድሩ ሲደረግ እኔና እናቴ ወደ ቤት እንድንመለስ ተወሰነና ወጣን፡፡ ግቢው ውስጥ የነበሩት ሁሉ እንዲወጡ በመገደዳቸው ውጭ በሩ ላይ በርካታ ሰው እኛን እየጠበቀን ነበር፡፡ ሁኔታው ስላላማረኝ ወደ በሩ ገና እያመራን ሳለ ማን ማን እንዳለ በርቀት ቃኘኋቸው፡፡ እማማ አፀደን ሳይ የሆነ እፎይታ ነገር ተሰማኝ፡፡ ገና በሩ ጋር ስንደርስ ጸበል ሳለሁ ብርቱ አስታማሚዎቼ የነበሩት የእማማ አፀደ ልጅ አስቻለውና ጓደኛው ኤርምያስ ወደ በሩ ተጠግተው ተቀበሉንና እኔን  መሐላቸው አድርገው ይዞን ወደመጣው መኪና አመራን፡፡ ወዲያው ግን ከአባቴ ልጆች ውስጥ አንዷ ከኋላዬ ተንደርድራ መጥታ ፀጉሬን ጨምድዳ "አንቺ ካፊር ሸርሙጣ...የአባቴ ገዳይ  አንቺ ነሽ" ብላ ስታንቀኝ አስቻለው እጇን ጠምዝዞ ካስለቀቃት በኋላ በኃይል ሲገፈትራት ሄዳ በጀርባዋ ተዘረጋች፡፡ ያን ጊዜ ከባድ ግርግር ተነሳ፡፡ የአባቴ ልጆች ሊበሉኝ ደረሱ፡፡ የማይሰድቡኝ የስድብ ዓይነት አልነበረም፡፡ ሁለቱ የአባቴ ሚስቶችም ከእናቴ ጋር በነገር ይተጋተጋሉ፡፡ እናቴ "በሕግ አምላክ.." እያለች ትጮሃለች፡፡ እማማ አፀደና ሌሎች ሁለት ጎረቤቶቻችን እየለመኑም እየተቆጡም በግልግል ሥራ ተጠመዱ፡፡ እኔ የአስቻለውን ሸሚዝ ጨምድጄና በእርሱ ተከልዬ ቆሜያለሁ፡፡ ሱሌይማን የሚባል ሌላው የአባቴ ልጅ ግን ካልገደልኳት ብሎ ለያዥ ለገራዥ አስቸገረ፡፡ ሌላውን ገላጋይ አልፎ ከመጣ ከአስቻለው ጋር እንደሚተናነቁ ግልፅ ነበር፡፡ አስቻለው በቁመት ረዥም ከመሆኑም በላይ ሰውነቱም ፈርጣማ ነው፡፡ ስለሆነም በቀላሉ የሚደፈር አልነበረም፡፡ ሱሌይማን ለገላጋይ ሲያስቸግር ወገቡን ይዞ በንቀት ይመለከተው ነበር፡፡ ይህ መልዕክት የገባው ሱሌይማን አቧራ ማስነሳቱን ገፋበት፡፡

ከወደ ልደታ ቤተ ክርስቲያን ዋናውን አስፓልት ይዘው የሚያልፉ ፖሊሶች ግርግሩን በርቀት አይተው እየሮጡ መጡ፡፡ ሁኔታውንም ከተቆጣጠሩት በኋላ አስቻለውንና ሱሌይማንን ይዘዋቸው ለመሄድ ቃጣቸው፡፡ ያቺ ፀጉሬን የጨመደደችኝ ልጅ አስቻለው እንደደበደባት ለፖሊሶቹ ስትለፈልፍ ፖሊስ ጣቢያ አብራ መጥታ ክስ መመስረት እንደምትችል ነገሯት፡፡ በኋላ እማማ አፀደ ከእናቴ ጋር ሆነው ነገሩን ከመነሻው ጀምረው አስረዱ፡፡ ሁሉም የአንድ አባት ልጆች መሆናቸውን፣ አባቴ የተከበረ ትልቅ ሰው እንደሆነና ዛሬ በደም ግፊት ምክንያት ያጋጠመውን ድንገተኛ ሕመም፣ የቀሩት ልጆቻቸው በዕለቱ አብራቸው የዋለችውን ልጃቸውን ለመታመማቸው ምክንያት አድርገው በማሰብ እርሷን ለማጥቃት መነሳታቸውን፣ እርሳቸውን፣ ልጃቸው አስቻለውንና የቀሩትን ገላጋዮች እየጠቆሙ ጎረቤት እንደሆኑና እኔን ከጥቃት ለመከላከል እንደሞከሩ አብራሩ፡፡ ፖሊሶቹ ነገሩ ተፍታቶ ሲገባቸው ማንም ሰው ማንም ላይ ጥቃት የመፈፀም መብት እንደሌለው ሱሌይማንን እያስጠነቀቁ ነገሩት፡፡ አያይዘውም "ይቺ ልጅም የገዛ አባቷን ለከፋ ጉዳት ዳረገች የሚባለው ሽጉጥ ተኩሳ፣ ወይም በስለት ወግታ ያጠቃች እንደሆነ እንጂ አናዳቸው ነው የሚለው ነገር ብዙም ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ከፈለጋችሁ ግን ማስረጃ አሰባስባችሁ ክስ ልትመሰርቱባት ትችላላችሁ" አሉ፡፡ በተጨማሪም "እነዚህ ሰዎች ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከላቸው ሕግ የሚፈቅደውን መፈፀማቸው ነውና ያስመሰግናቸዋል እንጂ አያስወቅሳቸውም" አሉ፡፡ ሲያጠቃልሉም "ስለ ሃይማኖት ያነሳችሁት ጉዳይ ግን ማንም ሰው የፈለገውን ሃይማኖት የመከተል ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው፡፡ እንደምናየው ግን ይህ የቤተሰብ ጉዳይ ስለሆነ በራሳችሁ ብትፈቱት የተሻለ ነው" አሉና የተሰበሰበውን ሰው ሁሉ "ተበተኑ" እያሉ አባረሩ፡፡ እኛም በየመኪኖቻችን ወደየቤታችን አመራን፡፡

ያ ሳምንት ለአባቴ ብቻ ሳይሆን ለእኔም ጭምር እጅግ ከባድ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ አባቴን እንደሚገባ ለመንከባከብና አጠገቡ ለመገኘት እንኳ ተሳነኝ፡፡ በማግስቱ ወደ ሆስፒታል ልሄድ ስነሳ እናቴ ከለከለችኝ፡፡ እናቴና በጠዋት ከቤቷ የመጣችው ታላቅ እህቴ በጣም ተማርረው ሲናገሩኝ እነርሱን ሸኝቼ ቤት ቀረሁ፡፡ በሦሥተኛው ቀን ከወንድሜ ጋር ብሄድም የአባቴ ልጆችን ዘለፋ መቋቋም አልቻልኩም፡፡ ግማሾቹ ይዝቱብኛል፣ አንዳንዶቹ ፀያፍ በሆነ ስድብ ሳይቀር ይሰድቡኛል፡፡ ዘመድ ነን የሚሉ ጭራሽ የማላውቃቸው ሰዎች ሳይቀሩ እኔን በማጥቃትና በማግለሉ ተባበሩብኝ፡፡ ወደ ቤት ከተመለስኩ በኋላ ያ ሱሌይማን የሚባል ልጅ ሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ ከወንድሜ ጋር ዱላ ቀረሽ ፀብ ማስነሳቱን ሰማሁ፡፡ እንዲያውም "እገልሀለው..እገልሀለው" እየተባባሉ መዛዛታቸውን ቀጠሉበት፡፡ በነጋታው ነገር እስኪበርድ በሚል እህቴ ቤት ሄጄ እንድሰነብት እናቴ ጠየቀችኝ፡፡ እናቴ በአባቴ፣ በእኔና እኔን በሚነቅፉ ሁሉ ከባድ ፈተና ውስጥ ስለገባች ላሳዝናት አልፈለኩም፡፡ ሰሚት አካባቢ ወደሚገኘው የእህቴ ቤት ሄድኩና ከሁለት ውጫጭ ልጆቿ ጋር ስዳረቅ ከረምኩ፡፡ እዚያ መሄዴን የሰሙት አስቻለውና ኤርምያስ የእማማ አፀደ ሴት ልጅ ሄለን እየደወሉ አፅናኑኝ፡፡ ኤርምያስ ስልኩን ከዘጋ በኋላ (2ጢሞ፡3÷12) የሚል ቴክስት ላከልኝ፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅሱን ፈልጌ ሳነበው "በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ" ይላል፡፡ ክፍሉ ስለተመቸኝ ዘለግ አድርጌ አነበብኩት፡፡ ኡፍ... ሥንት እረፍትና ሰላም የሚሰጡ ኃይለ ቃላት አገኘሁ፡፡ እህቴ ቤት ብዙ ትርፍ ሰዓት ከተሻለ ፀጥታ ጋር ስለነበረ በሞባይሌ የነበረውን መጽሐፍ ቅዱስ በደንብ ለማንበብ ዕድል ሰጠኝ፡፡ እውነት ለመናገር ሃሳቤ ግን የነበረው አባቴና ወንድሜ ጋር ነው፡፡ አባቴ በሕይወት የመትረፉን ነገር አስባለሁ፣ ከሰመመኑ ሲነቃ ምን እንደሚለኝ አስባለሁ፣ የቀድሞው ቤተሰባዊ ሕብረታችን መቀጠል አለመቀጠሉ ያስጨንቀኛል፡፡ በዚያ ላይ ወንድሜ ለእኔ ብሎ መጣላቱ ያሳስበኛል፡፡ ከእናቴ የሚወለድ ያለኝ ታላቅ ወንድም እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሱሌይማን ግን ለአቅመ ፀብ የደረሱ ሦሥት ተጨማሪ ወንድሞች አሉት፡፡ እናም ተባብረው ወንድሜን እንዳያጠቁብኝ እሰጋለሁ፡፡

አባቴ ሆስፒታል በገባ በ6ኛው ቀን መንቃቱን ሰማሁ፡፡ መናገር ግን ስላልሆነለት ዓይኖቹን እያንከራተተ ከቤተሰቦቹ ጋር ለመግባባት ይጥር ነበር፡፡ ከአራት ቀን በኋላ ደግሞ በዝግታም ቢሆን መናገር ጀመረ፡፡ ስትሮኩ ይበልጥ ያጠቃው አካል የግራ ጎኑ ከእግር እስከ ራሱ ማንቀሳቀስ አቃተው፡፡ የቀኝ እጁንና እግሩን ግን በደንብ ያንቀሳቀስ ነበር፡፡ ገና መናገር እንደጀመረ "አፊያ የታለች? ልጄን ጥሩልኝ" ብሏል ተብዬ በአጀብ ወደ ሆስፒታል ተወሰድኩ፡፡ የአባቴ ሁኔታና በዚያ መልኩ እኔን ማስጠራቱ አንጀቴን አላወሰው፡፡ ሳየው እንባዬን መግታት ስላቃተኝ በተኛበት አቅፌው ተንሰቀሰቅሁ፡፡ በነቃበት አራት ቀናት ውስጥ በዓይኑ ፈልጎ ስላጣኝ ሥጋት ሳይገባው አልቀረም፡፡ እኔ ግን "እታባ አንተ ጋር ስለምትውል ልጆቿን ለመጠበቅ እዚያ ሆኜ ነው" ብዬ ላረጋጋው ሞከርኩ፡፡ ከማንም ሰው በፊት፣ ከልጆቹ ሁሉ አስቀድሞ እኔን መፈለጉ ያሳደረብኝ ስሜት እጅግ በጣም የተለየ ነበረ፡፡ በገዛ ወንድሞቼና እህቶቼ በዘመድና ወዳጆች ሁሉ ያለ አግባብ ለመገፋቴ እንደ ማካካሻና ቅን ፍርድ አድርገው የወሰዱትም አልታጡም፡፡ እኔ ግን የአባቴ በተቃራኒ የስሜት ጫፎች ላይ የመገኘቱ ምሥጢር ሊገባኝ አልቻለም ነበር፡፡ ርኅራኄ የሞላበት አባት የሚመስል ፊትና ፀባይ ያሳይና ብዙም ሳይቆይ ደግሞ ወደ አውሬነት ይቀየራል፡፡ እሳት እንደሚሆን ሲጠበቅ ደግሞ ውሃ ሆኖ ይገኛል፡፡ ያም ሆኖ ኃይለኛውና ባለ ግርማው አባቴ የድካም ምልክት እየታየበት በአልጋ ላይ መዋሉ አንገብግቦኛል፡፡

አባቴ ለ2 ወራት ከ 15 ቀን ሆስፒታል ውስጥ ቆየ፡፡ የነርቭና የጡንቻ፣ የደም ሥርና የጅማት እንዲሁም ሌሎች ምርመራዎችና ሕክምናዎች ሲያደርግ፣ በፊዚዮቴራፒና የተለያዩ የነርቭ አነቃቂ የሆኑ እንቅስቃሴዎች ሲሰራ ሰነበተ፡፡ ለውጡ አዝጋሚ ቢሆንም ጥቂት በጥቂት ለውጥ እያሳየ በክራንች ድጋፍ መቆምና በትንሹ መንቀሳቀስ ቻለ፡፡ አባቴ ሆስፒታል በገባ አንድ ወር ከአሥራ አምስት ቀን ሲሆነው ሀገር ውስጥ ያልነበረው ሁመይድ መጣ፡፡ በስልክ ከእኔም ከሌላም ሰው ሰምቶ ስለነበር በቀጥታ ሆስፒታል በመሄድ አባቴን አገኘው፡፡ ለሦሥት ተከታታይ ቀናት ሆስፒታል ያለመምጣቴንና መኖሪያ ቤትም እንደሌለሁ ያረጋገጠው ሁመይድ ደውሎ ጠየቀኝ፡፡ እኔም ለአባቴ የሰጠሁትን ምክንያት ደገምኩለት፡፡ በማግስቱ ቅዳሜ ነበርና ከሰዓት ላይ ከዚያች ዕብድ ታናሽ እህቴ ጋር ያለሁበት ድረስ መጡ፡፡ ሰርፕራይዝ እናድርጋት ብሏት መሰለኝ ሳይነግሩኝ ነበር የመጡት፡፡ ከሰዓቱን ስንጫወትና ስንሳሳቅ ቆይተን መሐል ላይ "ቆይ አንዴ" ብሎ ወጣና ከመኪናው ላይ አውርዶ አንድ መካከለኛ ሻንጣ እየጎተተ መጣ፡፡ "ምንድነው?" ስለው "ይሄ ያንቺ ነው ኤፊ..ቲኒሽ ልብሶች ሥጦታ ኖ፡፡ እኔ አንቺ እወዳሎ፣ ሰዓዳ እወዳሎ፣ ሐጂ እወዳሎ፣ ሁሉ ቤተሰብ እወዳሎ...እና ፊኪር መግለቻ...ቲኒሽ ኖ...ለሰዓዳም ሰቲቻሎ" አለ የሰዓዳን ራስ እያሻሸ፡፡ ሁኔታው እየገረመኝ፣ ንግግሩም እያሳቀኝ የማደርገው ጠፍቶኝ ዝም ብዬ ቆምኩ፡፡ እኔ ያሉኝን ልብሶች በወጉ እንኳ ለብሼ ያልጨረስኳቸው ቢሆንም ሥራውና ሁኔታው አስገረመኝ፡፡ ሰዓዳም "ክፈቺው እንየው ኤፊ...ለእኔም አምጥቶልኛል...ብታዪ ቀሚስ፣ ቲሸርቶች፣ ሹራብ...ካፖርት ሳይቀር" እያለች ማጋነንና መገፋፋቱን ተያያዘችው፡፡

ከብዙ ንትርክ በኋላ ሻንጣውን ስከፍተው በተለያዩ ልብሶች፣ ሽቶዎች፣ ብትን ጨርቆች...ታጭቋል፡፡ ብዛቱን ሳየው እንደገና ዘግቼ "እኔ ይሄን መቀበል አልችልም" ብዬ ፈርጠም ለማለት ሞከርኩ፡፡ ሁመይድ እየሳቀ "እንግዲ መጣ መጣ ኖ..መልሶ አይወስድም" አለ፡፡ ሰዓዳም ሻንጣውን እየከፈተች "ኤፊ ደሞ..የተወሰኑትን እስቲ ሞክሪያቸው" እያለች ወደ መኝታ ክፍል ጎተተችኝ፡፡ እጅግ ያስደነቀኝ ያመጣቸው ቀሚሶች የተሰፉ ያህል እላዬ ላይ ልክክ ማለታቸው ነው፡፡ ሳስበው የሆነ ነገር ብልጭ አለልኝና ታናሽ እህቴን በደህና ኩርኩም ነደልኳት፡፡ ራሷን እያሻሸች "ምነው እህቴ...ምን አጠፋሁ?" ብላ ወገቤ ላይ ተጠመጠመች፡፡ "እነዚህ ቀሚሶች እንዴት ልኬ ሊሆኑ ቻሉ? አንቺ ነሽ አይደል...ምናባሽ ነው ያደረግሽው?" ብዬ አፈጠጥኩባት፡፡ "አዎ እህቴ አዎ" ብላ ወደ ውጭ ሊሄድ ስል መጥቶ ትንሽ ሥጦታ ሊያመጣልን እንደሚፈልግ ነግሯት የእኔንና የእርሷን ልብሶች መጠን ለክቶና ቁጥር አይቶ እንዲሄድ እንደረዳችው አመነችና አንገቴንና ጉንጬን ትስመኝ ጀመር፡፡ የተወሰኑ ልብሶችንና ጫማዎችን እየቀያየርኩ ለሁለቱም አሳየኋቸው፡፡ የልብሶቹን ጥራትም አደነቅሁለት፡፡ ሻንጣው ውስጥ የዋና ልብስ ሳይቀር ነበርና ነገሩ ጥሎሽ ነው እንዴ ብዬ እስከመገረም አደረሰኝ፡፡ ሁመይድ ስነ-ልቡናዬን ደህና አድርጎ እንዳጠና የተገነዘብኩት ካመጣቸው ልብሶች መሐል አንድ እንኳ እስላማዊ ልብስ ያለማካተቱ ነው፡፡ በሁኔታው ላይ ሰሞኑን በደንብ አነጋግረዋለሁ ብዬ አሰብኩና "ለማንኛውም በጣም አመሰግናለሁ ሁመይድ" አልኩት፡፡ ስንስቅና ስንጫወት ቆየን፡፡ አመሻሽ ላይ ሰዓዳን ቤት አድርሷት አባቴ ጋር ብቅ እንደሚል ተናግሮ ተመልሰው ሄዱ፡፡

አልፎ አልፎ አባቴ ጋር ሄጄ ጥቂት ቆያይቼ ወደ እህቴ ቤት እመለሳለሁ፡፡ አባቴ ጋር ውሎ ለማደር ፍላጎቱ ቢኖረኝም ከአባቴ ልጆች ጋር የሚፈጠረው ደስ የማይል መፋጠጥና አለፍ ሲልም የሚከተለው ስድብና ዝልፊያ ይህን ሁኔታ አልፈቀደልኝም፡፡ አባቴ ማገገም ሲገባው በዚህ ነገር እንዲጨናነቅም አልፈልግም፡፡ በዚያ ላይ አባቴ በንግዱ እንቅስቃሴም ሆነ በእስልምናው ማህበረሰብ ትልቅ ስም ያለው ስለነበር ጠያቂዎቹ በርካቶች ናቸው፡፡ በተለይ በእኔ ምክንያት ለዚህ እንደተዳረገ በመወራቱ እዚያ ብዙ ደቂቃ መገኘቱን አልወደውም፡፡ ይበልጥ ደግሞ የእስልምናው መምህራን በሚኖሩበት ሰዓት እዚያ ባልኖር እመርጣለሁ፡፡ ምቾት ተሰምቶኝ ጥቂት የምቆየው የእኔ ቤተሰቦች፣ ጎረቤቶቻችንና እነ ሁመይድ በሚኖሩበት ጊዜ ነው፡፡ ያም ሆኖ ቀናቶች እያለፉ ሄደው አባቴ ከሆስፒታል የሚወጣበት ጊዜ ደረሰ፡፡ ያን ቀን ብዙ ሰው ሆስፒታል ተገኘ፡፡ እናቴን ጨምሮ ሦሥቱም ሚስቶቹ በሥፍራው ከልጆቻቸው ጋር ነበሩ፡፡ ሁሉም አባቴ ወደ እነርሱ ቤት ሄዶ እንዲያገግም እንደሚፈልጉ አውቃለሁ፡፡ የእኔም ፍላጎት ተመሳሳይ ነው፡፡ እኛ ቤት ሆኖ ሆስፒታል ውስጥ ለመንከባከብ ያላገኘሁትን ዕድል ባገኝ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ሆኖም ወሳኙ እራሱ ነበርና አስቀድሞ እነ ሱሌይማን ቤት እንደሚሆን ተናግሮ በብዙ አጀብ ወደዚያው አመራ፡፡ እህቶቼና እናቴ አብረው ሲሄዱ እኔና ታላቅ ወንድሜ አሻፈረኝ አልን፡፡ አብሮን የነበረው ሁመይድ አጋጣሚውን ተጠቅሞ የደስ ደስ ምሳ ልጋብዛችሁ አለና አንድ ትልቅ ሆቴል ውስጥ ስንመገብ ቆየን፡፡ ከምግቡም በኋላ ጥቂት አወራንና ወንድሜ ደጋግሞ የጠራውን ስልኩን ሲያወራ ቆይቶ  መሄድ አለብኝ ብሎ የግድ አለን፡፡ በቀልድ መልክም "ሁመይድ እህቴን አደራ" ብሎት ተነስቶ ሄደ፡፡

ሁመይድ እንዲህ ያለውን አጋጣሚ ሲፈልግ እንደቆየ በሚያሳብቅ ሁኔታ ፊቱ ሁሉ ጥርስ ሆነ፡፡ እኔም ብሆን ቅሬታ አልተሰማኝም፡፡ እንዲያውም ያን ሁሉ ሥጦታ ያመጣበትን ምክንያት ልጠይቀው አጋጣሚውን ስጠብቅ ነበር፡፡ ይህ ሰው የአባቴ የንግድ አጋር ከመሆኑ በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከቤተሰባችን በተለይ ደግሞ ከእኔ ጋር ቅርበቱን አጠናክሯል፡፡ ከስሙና ከአንዳንድ ሁኔታዎቹ፣ ከራሱና ከአባቴም ገለፃ እንደተረዳሁት ሙስሊም እንደሆነ ብገነዘብም የአኗኗር ዘይቤውን ላስተዋለው ግን አውሮፓዊ ጠባይ ይታይበታል፡፡ ራሱ እንደነገረኝ ከሆነ ወላጅ እናቱ ዱባይ ውስጥ ትኖር የበረች ኢትዮጵያዊት ስትሆን አባቱ የዚያው ሀገር ተወላጅ የሆነ ከበርቴ ነበረ፡፡ ሆኖም ገና በለጋ ዕድሜው እናቱ በሞት ስትለየው በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለ ደግሞ አባቱንም በአውሮፕላን አደጋ ያጣል፡፡ እናቱ የአባቱ ሕጋዊ ሚስት ባትሆንም እንኳ አባቱ በጣም እንደሚወዳት ይነግረው እንደነበር፣ ካደገ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ዘመዶቿን ለማግኘት ብዙ ሞክሮ እንዳልተሳካለት፣ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ላለፉት 15 ዓመታት እዚህ ሀገር እንደሚመላለስና በርካታ የቢዝነስ ፓርትነሮችን እንዳፈራ ተረከልኝ፡፡ በተጨማሪም ከአባቱ በወረሰው ከፍተኛ ሀብትና እርሱም በንግዱ እንቅስቃሴ ስኬታማ በመሆኑ ቱጃር እንደሆነ ገለፀልኝ፡፡ ካለው ሀብት ዋና ዋናውን ለመጥቀስ እዚያው ዱባይ ውስጥ አባቴ የሚያከፋፍላቸው የአረቢያ መጅሊስና የተለያዩ ምንጣፎች ማምረቻ ግዙፍ ኢንዱስትሪ አለው፡፡ ዋና መቀመጫውን እንግሊዝ ሀገር ያደረገና በተለያዩ ሀገሮች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችና የሽያጭ ማዕከላት ያሉት ግዙፍ የኬሚካል ማምረቻና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ 20% ባለድርሻ ነው፡፡ ኩዌት ውስጥ በሚገኝ የነዳጅ ማውጫ ኢንዱስትሪም የ10% ባለ አክሲዮን ነው፡፡ ሌሎች የተለያዩ የግልና የአክሲዮን ቢዝነሶች በተለያዩ ሀገሮችም አሉት፡፡ 

በዚህ መልኩ ገብስ ገብሱን ስንጫወት ቆየንና "አፊያ አንቺን በተመለከተ አንድ ሃሳብ አለ፣ ማለት ጥያቄ ማለቴ ነው፡፡ ሃሳብ..ጥያቄ..ያው አንድ መሰለ፡፡ እንጊዲ አማርኛ ቺግር አለ ታውቃለሽ አደል?" አለ በተለመደው የተሰባበረ አማርኛ፡፡ "ምን?" በሚል አስተያየት ትኩር ብዬ አየሁት፡፡ አንዳንድ ሁኔታዎች ከቃል ይልቅ የመግለጥ ብቃት አላቸውና ፊቴን በትኩረት አጥንቶ ጥቂት ሲቅለሰለስ ቆየ፡፡ ትላልቅ የሚባሉ ሰዎች ሳይቀሩ በአንዳንድ ሁኔታዎች ላይ እንደ ልጃገረድ ሲሽኮረመሙ ማየት የሆነ የሚያዝናና ነገር አለው፡፡ በሁኔታው ላለመሳቅ እንደምንም ታግዬ ተቆጣጠርኩት፡፡ እርሱም ትንሽ ከታሸ በኋላ "እኔ ቋንቋ ቺጊር ስላለ ስሜት መግለፅ ይከብዳል" አለ፡፡ ምንም አለማለቴን ስላየ ቀጠለ፡፡ "እኔ አንቺን በጣም እወዳሎ፣ ወላሂ በጣም ኖ የምወዶ፣ እና የእኔ ምሽት ብትሆኝ በጣም ደስ ይላል፣ ደሞ በጣም ደስተኛ አረጋሎ" አለ፡፡ መሬት መሬት እያየሁ ጥቂት ዝም አልኩ፡፡ ፀጥታዬ ያሰጨነቀው ሁመይድ "ሚነው ዚም አልሽ?" አለኝ፡፡ ቀና ብዬ "እና..የጋብቻ ጥያቄ እያቀረብክልኝ ነው ማለት ነው?" አልኩት፡፡ እርሱ ግን ለሃሳቡ የተሻለ የመግለጫ ቃል በማግኘቱ እንደ ሕጻን እየፈነጠዘ "የጋብቻ ጥያቄ...የጋብቻ ጥያቄ..ሊክ ብለሻል፣ እንደዛ ኖ" አለኝ፡፡

                             (ይቀጥላል)

            ----- ማርያማዊት ገብረመድኅን -----
saramareyama.890@gmai.com

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ